1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አውሮጳ እና የስደተኞች ቀውስ

ማክሰኞ፣ መስከረም 17 2009

ባለፈው ዓመት የበርካታ ስደተኞች መተላለፊያ እና መድረሻ የነበሩ የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት የህብረቱ ድንበር ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግበት ተስማምተዋል ። የሀገራቱ መሪዎች ባለፈው ቅዳሜ ቭየና ኦስትርያ ውስጥ ባካሄዱት ጉባኤ ወደፊት ሊከሰት የሚችል ሌላ የስደተኛ ቀውስን ለመከላከል ያስችላሉ ባሏቸው ሌሎች እርምጃዎችም ላይ ተስማምተዋል

https://p.dw.com/p/2QfR5
Wien  Angela Merkel  Donald Tusk EU Gipfel Balkan Route
ምስል picture-alliance/dpa/C.Bruna

አውሮጳ እና የስደተኞች ቀውስ

 የተመ ስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በምህፃሩ ዩ ኤን ኤች ሲ አር በበኩሉ ድንበር መዝጋት ለችግሩ መፍትሄ አይሆንም ሲል አሳስቧል ።
«የአውሮጳ ህብረት የጋራ ድንበራችንን እንደገና መቆጣጠር አለብን ። ማን ወደ አውሮጳ እንደሚመጣ መወሰን ያለብን እኛ እንጂ ህገ ወጥ ድንበር አሻጋሪዎች አይደሉም ። ይህ ካልሆነ በርካታ ሀገራት የራሳቸውን ብሔራዊ እርምጃዎች መውሰድ ይጀምራሉ ። ኦስትሪያም ከመካከላቸው አንዷ ትሆናለች »
የኦስትሪያ መራሄ መንግሥት ክርስቲያን ኬርን ባለፈው ቅዳሜ ቭየና ኦስትሪያ ውስጥ ጀርመን ኦስትሪያ ግሪክ እና የባልካን ሀገራት በስደተኞች ቀውስ ላይ ያካሄዱት ጉባኤ ሲጠናቀቅ የሰጡት አስተያየት ነበር ።በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ በተለይም ከሶሪያው ጦርነት የሸሹ ስደተኞች በግሪክ በኩል በምዕራብ ባልካን ሀገራት አድርገው ወደ ሰሜን አውሮጳ ሀገራት ከገቡ ዓመት አለፋቸው ። ባለፈው ዓመት የስደተኞች መድረሻ እና መተላለፊያ የነበሩት የአውሮጳ ሀገራት ባለፈው ቅዳሜ ቭየና ኦስትርያ ውስጥ ያካሄዱት ጉባኤ በዋነኛነት ያተኮረው ያለፈው ዓመቱ የስደተኞች ቀውስ ዳግም እንዳይከሰት መከላከል በሚቻልበት መንገድ ላይ ነበር ። በዚሁ መሠረት ጉባኤተኞቹ በአውሮጳ ድንበር ላይ የሚካሄደው ቁጥጥር ከአሁኑ ይበልጥ እንዲጠብቅ ተስማምተዋል ። ከዚሁ ጋር የህብረቱ ድንበር ተቆጣጣሪ ድርጅት የፍሮንቴክስን ተልዕኮ ለማስፋትም ቃል ገብተዋል ። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እንደተናገሩት ሀገራቱ ፍሮንቴክስ ይበልጥ እንዲጠናከር ይፈልጋሉ ።
«አባል ሀገራት በሙሉ የአውሮጳ ህብረት ድንበር ጠባቂ ድርጅት Frontex ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግለት እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል ።በዚህ ላይ የህብረቱ ኮሚሽን እና አባል ሃገራት መሥራት አለባቸው ።»
የተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በምህጻሩ UNHCR የአውሮጳ ሀገራት ስለ ስደተኞች ጉዳይ ማሰባቸው እና መነጋገርም መቀጠላቸው በጣም አስፈላጊ ነው ይላል ። ሆኖም የድርጅቱ የቭየና ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት የህዝብ ግንኙነት ባልደረባ ሩት ሸርፈል ባለፉት ጥቂት ዓመታት እና ወራት ተባብረው አለመሥራታቸው መፍትሄውን አርቆታል ብለዋል ።ሸፍል እንዳሉት በUNHCR እምነት ድንበር መዝጋት ችግሩን አይፈታም ።
«አሁን መንግሥታት ስለ ህብረቱ ድንበር ቁጥጥር እና አያያዝ ብዙ በተደጋጋሚ ጊዜያት ንግግሮች በማካሄድ ላይ መሆናቸውን እናያለን ። በርግጥ ሀገራት ሁሉ ድንበሮቻቸውን የመቆጣጠር መብት አላቸው ። ሆኖም መንግሥታት የስደተኞች ዝውውርን መሠረታዊ ችግሮች የመፍታት ሃላፊነት ሲወስዱ ማየት እንፈልጋለን ።ምክንያቱም ስደተኞች ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚንቀሳቀሱት ክትትል ስለሚደረግባቸው እና ጦርነትን በመሸሽ ነው ። በመሠረቱ ለሰደተኞች ትክክለኛ መፍትሄ ካልተፈለገ ድንበር መዝጋት የስደተኞችን ዝውውር አይገታም ።»
 በኦስትርያ ግፊት የስደተኞች መተላለፊያ የነበሩት የባልካን ሀገራት ባለፈው መጋቢት  ድንበሮቻቸውን ከዘጉ በኋላ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የተባለው ወደ ሰሜን አውሮጳ የሚገባው ስደተኛ ቁጥር  እጅግ ቀንሷል ።ያም ሆኖ ቭየና እንደምትለው አሁንም  ከ100 እስከ 150 የሚደርሱ ስደተኞች በየቀኑ ኦስትሪያ መግባታቸው አልቀረም ። በዚሁ ባለፈው መጋቢት የአውሮፓ ህብረት  ወደ አውሮጳ ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞችን በሀገርዋ እንድታቆይ ከቱርክ ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል ።  ለቱርክ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እና እርዳታ የሚያስገኘው ይኽው ስምምነት ተግባራዊ መሆን ቢጀምርም ቱርክ ያቀረበቻቸው አንዳንድ ተጨማሪ ጥያቄዎች  መልስ ባለማግኘታቸው ሂደቱ እየተጓተተ ነው ።በሌላ በኩል የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ፣ የባልካን ሀገራት ድንበራቸውን በመዝጋታቸው ምክንያት ግሪክ የተከማቹን ስደተኞች ለመከፋፈል ቢጠየቁም ይህም ፈጣን ምላሽ አላገኘም ። የቅዳሜው  ጉባኤ ግሪክ የሚገኙ ተገን ጠያቂዎችን ጉዳይ በማፋጠን ወደ ምዕራብ አውሮጳ የሚመጡ ስደተኞችን ቁጥር  እንዲቀንስ ግሪክን መርዳት በሚቻልበት መንገድ ላይም መክሯል ። ከዚህ ሌላ የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ፣ከቱርክ ጋር ከተደረሰው ውል ጋር የሚመሳሰሉ ስደተኞችን ወደ ኒዠር፣ማሊ ሴኔጋል እና ግብጽ መጠረዝ የሚቻልባቸውን ስምምነቶች ተግባራዊነት እንዲያፋጥን ግፊትእንደሚያደርጉም መሪዎቹ ተናግረዋል ።ዩኤን ኤች ሲ አር ግሪክ የሚገኙ ስደተኞችን ጉዳይ ለማፋጠን መታሰቡ መልካም ነው ይላል
«እንደ UNHCR ተገን የሚጠይቅ ግለሰብ ሁሉ ጉዳዩ የመታየት መብት አለው ።በዚሁ መሠረት የተገን ጠያቂዎች ጉዳይ እንዲፋጠን እንደሚፈልጉ ማሳወቃቸው በጣም ጥሩ ምልክት ነው ።ምክንያቱም ግሪክን በመሳሰሉ ሀገራት ሰዎች ማመልከቻቸው ተቀባይነት ማግኘቱን ወይም ውድቅ መደረጉን ሳያውቁ ለረዥም ጊዜ ይጠብቃሉ ።በርግጥ ከለላ የሚያስፈልጋቸው ከለላ ማግኘት አለባቸው ። በኛ እምነት ቢጀመርም ሂደቱ አዝጋሚ የሆነው ስደተኞችን መከፋፈሉ ወይም ሌላ ሀገር ማዛወሩ በአውሮጳ የስደተኝነት መብት ላገኙ መፍትሄ ይመስለናል ።ከዚህ በተጨማሪ ስደተኞች ስላይደሉ ከለላ አያስፈልጋቸውም የተባሉም ጉዳያቸው በቂ ጊዜ ተወስዶ ሊታይላቸው ውሳኔ ሊያገኝ ይገባል ።የስደተኝነት መብት ሊሰጣቸው የማይችል ከሆነ በክብር ወደ መጡበት መመለስ ይገባል ።»
ባለፈው መጋቢት የባልካን የጉዞ መስመር እንዲዘጋ የአካባቢው ሀገራት ሲወስኑ ጀርመን እና ግሪክ ተቃውመው ነበር ።የአውሮጳ ህብረትም ውሳኔውን ሲተች ነበር ።ይሁን እና ባለፈው ቅዳሜ የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ቱስክ የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ከባልካን ሀገራት እና ከቱርክ ጋር በቅርበት መሥራት እንዳለባቸው ተናግረው ህገ ወጥ ያሉት የምዕራባዊ ባልካን የጉዞ መስመር እስከወዲያኛው መዘጋቱን  አስታውቀዋል ።ድንበር መዝጋት ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም የሚለው ዩኤን ኤች ሲ አር በበኩሉ ለስደተኞች ቀውስ ይበጃሉ ያላቸውን መፍትሄዎች  በሦስት ከፍሏቿዋል እንደገና ሩት ሸፍል
 «አብዛኛው ስደተኛ በሶሪያ አጎራባች ሀገራት ነው የሚገኙት ።አብዛኛዎቹ ሊባኖስ ፣ዮርዳኖስ እና ቱርክ ነው ያሉት ።እነዚህ ሀገሮች ብዙ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ። ከአውሮጳ ሀገራት ተጨማሪ እርዳታ ይሻሉ ። ይህ ከመፍትሄዎቹ አንዱ ነው ። ሁለተኛው አሁን ከሚደረገው በላይ ወደ አውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት እንዲገቡ የተፈቀደላቸውን የሌሎች ሀገራት ስደተኞችን የማስፈር ሥራ መከናወን አለበት ። የቤተሰብ አባላትን ማገናኘት እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ ። የአውሮጳ ህብረት ከአሁኑ በበለጠ ሰዎችን በህጋዊ መንገድ ለመውሰድ ቃል መግባት አለባቸው ። በሦስተኛ ደረጃ የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ስደተኞችን ለመከፋፈል ተስማምተው ነበር ።አሁን ሰዉ ወደነዚህ ሀገራት በአስቸኳይ መወሰድ አለበት ።በርካታ ሰዎች ግሪክ ሆነው ወደ ሌሎች ሀገራት እስኪወሰዱ እየጠበቁ ነው ።ሆኖም እያንዳንዱ ሀገር የድርሻውን በመፈፀም ሃላፊነት መውሰድ እና ተባባሪነቱን ማሳየት አለበት ።»
የቭየናው ጉባኤ ዓላማ ህገ ወጥ ስደትን ማስቆም መሆኑ ነው የተገለፀው ።  በሸፍል አስተያየት  አማራጭ መተላለፊያ መንገድ ቢኖር ሰዎች ወደ ህገ ወጥ አሻጋሪዎች ባልሄዱ ነበር ። በዚህ ጉባኤ ጀርመን ዋነኛ የስደተኞች መድረሻ ከሆኑት ከህብረቱ ድንበሮች ከኢጣልያ እና ከግሪክ በወር በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ለመውሰድ ተስማማታለች ። ግሪክ በበኩሏ ስደተኞች ወደ ሀገርዋ እንዳይገቡ ለመከላከል ፍሮንቴክስ ከመቄዶንያ እና ከአልባንያ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር እንዲጠብቅ ጠይቃለች ። ጀርመን ኦስትሪያ እና የምዕራባዊ ባልካን ሀገራት ባለፈው ቅዳሜ የደረሱባቸው ስምምነቶች ሀገራቱ ሰብዓዊነትን ወደ ጎን ማለታቸውን  የሚያሳዩ ፣ በቀኝ ፅንፈኞች ግፊትም ህብረቱ ልዩ የሚያደርገውን መሠረታዊ መርሆች እንዳያከብሩ የሚያደርጉ ናቸው የሚሉ ትችቶች እየተሰነዘሩባቸው ነው ።

EU Gipfel Wien Balkan Route
ምስል picture alliance/APA/ picturedesk.com/H. Neubauer
Wien EU Gipfel Östereich Balkan Route Angela Merkel  Christian Kern
ምስል picture-alliance/dpa/C.Bruna
Wien EU Gipfel Balkan Route
ምስል picture-alliance/dpa/C.Bruna

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ