1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አውሮጳ፣ የስደተኞች ቀውስ፣ መፍትሄውና ትችቱ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 30 2008

አውሮጳውያንን ላስጨነቀው የስደተኞች ቀውስ መፍትሄ ፍለጋው ቀጥሏል ። የአውሮጳ ሕብረት አባል ሃገራት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትናንት ብራሰልስ ቤልጅየም ባካሄዱት ልዩ ስብሰባ ችግሩን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሊቀርፍ ይችላል ያሉትን መፍትሄ አቅርበዋል ።

https://p.dw.com/p/1H3d5
Slowenien Dobova Flüchtlinge Balkanroute Menschenmenge
ምስል Reuters/S. Zivulovic

አውሮጳና የስደተኞች ቀውስ

ወደ አውሮጳ የሚገባው ስደተኛ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ እየጨመረ መሄድ የአውሮጳ ሕብረት አባል ሃገራት ራስ ምታት ሆኖ እንደቀጠለ ነው ። ከዚህ ቀደም ያልተጠበቀውን ይህን የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ለመወጣት አባል ሃገራት ልዩ ልዩ ድጋፎችን ለመስጠትና ስደተኞችንም ለመከፋፈል በተለያዩ ጊዜያት ቃል ገብተው ነበር ። ሆኖም ለዚህ ማስፈፀሚያ የሚያስፈልጉ የገንዘብም ሆነ የሰው ኃይል ድጋፎች መዘገይት የታሰበውን ለማሳካት እንቅፋት ሆኗል። ገባሁ ገባሁ የሚለው የአውሮጳ ክረምት ሳይበረታ ቃል የተገቡት እርምጃዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ተማፅኖው ቀጥሏል። የሕብረቱ የፍልሰት ጉዳዮች ኮሚሽነር ዲሚትሪስ አቭራሞፖሉስ አባል ሃገራት ድንበራቸው ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ለማድረግ ኢጣልያና ግሪክ የሚገኙ ስደተኞችን ለመከፋፈል እና ከግሪክ ወደ ሰሜን አውሮፓ ሃገራት በሚወስደው ዋነኛው የባልካን መስመር የመቀበያ ማዕከላትን ለማዘጋጀት የተገባው ቃል ተግባራዊ እንዲሆን ትናንት የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባካሄዱት ስብሰባ ላይ ጠይቀዋል ። በዙር የሚደርሰው የወቅቱ የአውሮጳ ሕብረት ፕሬዝዳንት ላክዘንበርግ ናት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዦን አሰልቦርን ክረምቱ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ለመከላከል በባልካን ሃገራት ብርድ ሰበብ ሰዎች እንዳይሞቱ ህብረቱ የሚችለውን ሁሉ እንዲያደርግ ነው ጥሪ ያስተላለፉት ።ይሁን ከእስካሁኑ የሕብረቱ አባል ሃገራት እንቅስቃሴ በመነሳት አውሮጳውያን ማድረግ የሚችሉትን አላደረጉም ሲሉ የሚከራከሩ ጥቂት አይደሉም። ዶክተር አልጋነሽ ፍስሃ የኢጣልያ ነዋሪና ሴቶችና ህጻናትን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ስደተኞችን የሚረዳው ጋንዲ የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ፕሬዝዳንት ናቸው። በርሳቸው አስተያየት አውሮጳውያን የስደተኞችን ጉዳይ አጋኖ ከማቅረብ ውጭ ለመፍትሄ ፍለጋው ፈጥነው አልተንቀሳቀሱም። «አውሮጳ በስደተኞች ቀውስ እየነገደ ነው። ሁሌም የሚናገሩት ስለ መብዛታቸው ነው ። እናም ኢጣልያም ሆነች ሌሎቹ ሃገራት ይህን ያህል ቁጥር ያለውን ስደተኛ ምን እናድርገው ከማለት ውጭ ምንም ዓይነት መፍትሄ አላገኙም። ስደተኞች ኢጣልያ ከገቡ በኋላ ወደ ሰሜን አውሮጳ ማለትም ወደ ጀርመን ዴንማርክና ስዊድን እንዲሁም ሌሎች ሃገራት ያቀናሉ። አውሮጳውያን ይህን እያወቁ ለነዚህ ሰዎች ምን እናድርግላቸው ብለው አልተዘጋጁም። ለዚህ እንደ አብነት በቱርክ ድንበር ላይ ያለውን ሁኔታ መመልከት ይበቃል ።»

Karte Balkan Fluchtroute 20.10.2015 Englisch

በዶክተር አልጋነሽ አስተያየት አሁን ስደተኞችን በብዛት በተቀበለችው በጀርመንም ሆነ በግሪክ የስደተኞች መጠለያዎች መሥራት ነው የሚፈገለው። የአውሮጳ ሕብረት በአሁኑ ጊዜ ከግሪክ በባልካን ሃገራት በኩል ወደ ሰሜን አውሮጳ የሚተሙት በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች አውሮጳ ሳይደርሱ የሚቆዩባቸው ማዕከላት ለማዘጋጀት አቅዷል። በባልካን ሃገራት በሚቋቋሙት በእነዚህ ማዕከላት የተገን ጠያቂዎች ማመልከቻዎች እንዲመረመሩ ይደረጋል። ሕብረቱ በዚህ ጉዳይ ላይ አባል ካልሆኑ የባልካን ሃገራት ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል። የአውሮጳ ሕብረት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትናንት ባካሄዱት ስብሰባም ከተተኮረባቸው ውስጥ ውስጥ አንዱ ይኽው ጉዳይ ነበር። ሕብረቱ በባልካን ሃገራት የስደተኞች ማቆያ ማዕከላት ሊገነባ መነሳቱን ዶክተር አልጋነሽ ይቃወማሉ ።

Ungarn Transitzone (Symbolbild)
ምስል picture alliance/JOKER

«ይህ መፍትሄ አይደለም። የዳርፉር ልምድ አለን። እዚያ ወስደው ምን እደረጉላቸው ? ልጆች ትምህርት ቤት መሄድ አለባቸው ። አዋቂዎች ደግሞ መሥራት ይፈልጋሉ ። ወደ አውሮጳ የመጣው ስደተናኛ ቁጥር ስናስብ እጅግ እጅግ በጣም ትንሽ ነው ። ይህ ሁሉ ግን ከዕውነት የራቀ ነው ።»

ከዚህ ሌላ ሕብረቱ አሁን ላስጨነቀው የስደተኞች ችግር እንድ መፍትሄ የሚጠብቀው ነገ ና ከነገ ወዲያ ከአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች ጋር በማልታ የሚያካሂደውን ጉባዔ ነው ። ይኽው ከ50 በላይ የአውሮጳ ሕብረትና የአፍሪቃ ሕብረት አባል ሃገራት መሪዎች የሚሳተፉበት ጉባኤ አውሮጳ የኤኮኖሚ ስደተኞች የሚላቸውን አፍሪቃ መልሶ እንዲወስድ ጥሪ ያቀርባል ። በምትኩም የአውሮጳ ሕ የስደት መሠረታዊ ምክንያቶች ናቸው የሚባሉትን ጦርነትና ድህነት ለመዋጋት ለአፍሪቃ ሃገራት የ3.6 ቢሊዮን ዩሮ የልማት እርዳታ ለመስጠት ቃል ገብቷል። ለዶክተር አልጋነሽ ለስደት ምክንያት ከሆኑ መንግሥታት ጋር ይህን መሰሉን ስምምነት ማድረግ ተቀባይነትም የለውም

«ይህ ጉባኤ ከሌሎች ጉባኤዎች የተለየ አይመስለኝም ገንዘብ እንሰጣችኋለን ፣ እናንተ ስደቱን አስቁሙልን ነው የሚሏቸው ህዝቦቻችሁ ወደኛ እንዳይመጡ ያዙልን ነው የሚሏቸው ። ይህ ግን መፍትሄ ይሆናል ? በዚህ ጉባዔ የሚሳተፉ የአፍሪቃ መንግስታት ገንዘቡን ይቀበላሉ። ገንዘቡን ግን የህዝባቸውን ሰብዓዊ መብት ለማስጠበቅ አይውልም። እነዚህ መንግሥታት ሰብዓዊ መብቶችን አክብረው ቢሆን ኖሮ ጦርነት አይኖርም ነበር ከኤርትራም ሰዎች አይሰደዱም ነበር ።ምክንያቱም ለህዝቦቻቸው መሰደድ ምክንያቶቹ እነርሱው ናቸው። »

Kroatien Serbien Flüchtlinge bei Tovarnik
ምስል Getty Images/J. J. Mitchell

እርሳቸው እንደሚሉት የበእርዳታ የሚሰጠው ገንዘብም ለታሰበለት አላማ አይውልም

«በዚህ ዓይነት መንገድ ይጠበቃል አይሆንም ይልቁንም ገንዘቡ ሰብዓዊ መብትን ለመጨቆን ነው የሚውለው። አውሮጳ ለቱርክ ለግሪክ ለሱዳን ለኤርትራ እና ለሌሎችም ሃገራት ገንዘብ ሊሰጥ ያሰበው ስደትን ለማስቆም ነው ። ከዚህ የቀድሞው የኢጣልያው የቤርሎስኮኒ መንግሥት ከቀድሞው የሊቢያ መሪ ጋዳፊ ጋር ተስማምተው ጋዳፊ ስደተኞችን በሙሉ እንድትገድብ ተደርጎ ነበር ። አሁን ደግሞ እነዚህ ሃገሮች ተመሳሳይ ስምምነት እያደረጉ ነው ።»

ይህ እርምጃ ስደትን ለማስቆም ምንም አይፈይድም የሚሉት ዶክተር አልጋነሽ በበኩላቸው መፍትሄ የሚሉትን ሃሳብም ሰንዝረዋል ።

«አውሮጳውያን የስደተኞችን ችግር ለመፍታት ከፈለጉ የሽብር ስጋታቸውንም ለማስቀረት ሰብዓዊ መተላለፊያ ስፍራ ማቋቋም አለባቸው ። ይህም ለአውሮጳውያንም ሆነ ለስደተኞች አመቺ ይሆናል። ለምሳሌ ለሶርያዎቹ ሞሮኮ ወይም ሊባኖስ ሊሆን ይችላል ለሶማሊያውያንና ለኤርትራውያን ከሌሎች የአፍሪቃ ቀንድ ሃገራት ለሚሰደዱ በአንድ የአፍሪቃ ቀንድ ሃገር ውስጥ ይህን መሰሉን ሰብዓዊ ማቆያ ማዘጋጀት።ስለዚህ ሰሰዎቹ ደላሎች ሳያገኟቸው ሳይሰቃዩና ሳይንገላቱ ለረሃብና ለሌሎችም አደጋዎች ሳይጋለጡ በህጋዊ ቪዛ አውሮጳ ሊገቡ ይችላሉ ።»

Türkei Griechenland Flüchtlinge bei Edirne
ምስል Reuters/O. Orsal

ይህ ደግሞ በዶክተር አልጋነሽ አስተያየት አውሮጳ ለችግሩ ትክክለኛ መፍትሄ መፈለግ አልቻለም ማለት ነው ።እርሳቸው እንደሚሉት አውሮጳውያን በህገ መንግሥታቸው የሰፈረውን ሰብዓዊ መብቶችን የማስከበር ሃላፊነታቸውን ወደ ጎን እየተዉ ነው ። ሁሉም በጎርጎሮሳዊው 1948 የወጣውን የተመ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነት ፈርመዋል። ሆኖም አንዳቸውም ይህን ህግ አላከበሩም የሚይዙት የሚጨብጡትም ቸፍቷቸዋል ይላሉ ።

«በኔ አመለካከት አውሮጳውያን ግራ ተጋብተዋል ። በጉዳዩ ላይ ርስ በርስ ተከፋፍለው ምንም ዓይነት መፍትሄ እየፈለጉ አይደለም። መፍትሄው ሰብዓዊ የመተላለፊያ መስመር ማበጀት ነው። ይህ የሰው ህይወት እንዳይጠፋ ያደርጋል ከሃገራቸው የሚሰደዱ ሰዎች ሰብዓዊ ቪዛ ወይም የፖለቲካ ጥገኝነት ቪዛ ለማግኘት የሚያመለክቱባቸው ማዕከላት ሊያቋቁሙ ይችላሉ። ከአፍሪቃ ቀንድ ከሶሪያ ለሚመጡት በነዚህ ማዕከላት በሚቋቋም ኮሚሽን የስደተኞች ጉዳይ እየተጣራና እየተመረመረ በሳምንት ጊዜ ውስጥ መልስ እንዲያገኙ ይደረጋል ።»

ሊገባደድ ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ በቀረው በጎርጎሮሳዊው 2015 በባህር ወደ አውሮጳ የገባው ስደተኛ ቁጥር 777ሺህ አልፏል። ከመካከላቸው አብዛኛዎቹ በእግር ጀርመን ወይም ስዊድንን የመሳሰሉ ሃገራት ገብተዋል። ይህን ያልታሰበ የስደተኞች ፍልሰት ለመቆጣጠር አውሮጳውያን ኃይላቸውን አሰባስበው እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ቀርቧል ።

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ