1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አውሽቪትዝ፤ የጀርመናውያን ዘግናኝ ቃል

ሐሙስ፣ ጥር 21 2007

ከ 2 ቀናት በፊት ፣ አያሌ መገናኛ ብዙኀን በሰፊው ያወሱት ርእሰ ጉዳይ ቢኖር ፤ ከ 70 ዓመት በፊት በዛሬዋ ፖላንድ የምትገኘው አውሽቪትዝ የተባለችው ፣የህዝብ ማጎሪያና፣ ሰው በሰው ላይ በዓለም ታሪክ ታይቶ ያልታወቀ ግፍ የሠራባት ቦታ ነጻ የወጣችበትን ዕለት ነው።

https://p.dw.com/p/1ET9X
ምስል picture-alliance/dpa

ወደር ያልተገኘለት የግፍ ተግባር ፤ በፊልም በትረካ ፤ በፎቶግራፍ ፣ በሥነ ጽሑፍ ተደግፎ፤ ለቀጣዩ ትውልድ ጥብቅ ማሳሰቢያ ሆኖ በመቅረቡ በጀርመን ፖለቲካዊ ና ማሕበረሰባዊ ኑሮ ፤ ፍጹም ችላ የሚባል ወይም የሚረሳ አይደለም። በዛሬው የባህል መድረክ ምትክ ፤ ስለአውሽቪትዝና ስለጀርመናውያን የጋራ ኀላፊነት የተጠናቀረ ሰፋ ያለ ዘገባ ይቀርባል ።

Konzentrationslager Auschwitz-Birkenau
ምስል DW/D.Bryantseva

በጀርመን ግፈኛው የናዚዎች አገዛዝ እ ጎ አ ከ 1933 እስከ 1945 ፣ ማለትም እስከ 2ኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የጨፈጨፈበት ድርጊት በአንዲት ቃል ይገለጣል። አውሽቪትዝ በሚሰኘው!። አውሽቪትዝ ማለት 6 ሚሊዮን አይሁድ የተጨፈጨፉበት ማለት ነው። ጥሬ ዕቃም ሆነ አላባ ፋብሪካ ውስጥ ገብቶ በልዩ ልዩ ደረጃዎች አልፎ የመጨረሻ የፋብሪካ ምርት ሆኖ እንደሚወጣ ሁሉ ፣ ከሕዝብ ማጎሪያው ቦታ ፤ ሰዎች ካንድ ክፍል ወደሌላው በጅምላ እየተነዱ በሚያስጨንቅና የመተንፈሻ ሕዋሳትን ከጥቅም ውጭ አድርጎ እያስጓጎረ እንዲያልቁ ያበቃ የምድር ሲዖል ነው አውሽቪትዝ ማለት! ሰው በቁመናው ወደ ግዙፍ ምድጃ እየተወረወረ በእሳት እየተቃጠለ ያረረበት ነው ይላሉ ፣ ማግዳ ሆላንደር ላፎን የተባሉት በሕይወት ተርፈው በመመሥከር ላይ የሚገኙት የ 87 ዓመቷ ባልቴት። ሆላንደር ላፎን፤ እ ጎ አ በ 1944 የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ሊቆም አንድ ዓመት ሲቀረው፤ አባታቸው በሃንጋሪ ፋሺስቶች ተሠቃይተው ተገደሉ። እርሳቸው፣ ታናሽ እኅታቸው አይሪንና እናታቸው ኤስተር ፤ ከብቶች በሚቻኑበት ፉርጎ ታጉረው ወደ አውሽቪትዝ ተጋዙ። እኅታቸውና እናታቸው ወዲያውኑ በጋዝ ታፍነው መገደላቸውን ማግዳ ይናገራሉ። ወንዶች ፣ ሴቶች፤ ልጆች ፤ ወጣቶች ፣ ጎልማሶች፣ ሳምንት ድረስ በሚወስደ የባቡር ጉዞ፤ ያለ ውሃና ምግብ ተዳክመው ቀቢጸ-ተስፋ አድሮባቸው ነበረ እማጎሪያው ጣቢያ የሚደርሱት። በዚያም ከግድያም ሆነ ሞት ጋር ስሙ የተያያዘው ዶ/ር ዮሰፍ መንገለ ነበረ የሚጠብቃቸው። ከዚያ የምድር ገሐነም ከተረፉት ጥቂት ሰዎች መካከል ከማግዳ ሆላንደር ላፎን ሌላ፣ አሁን የ 90 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት ሙዚቀኛይቱ ኤስተር ቤጃራኖም ይገኙበታል።

KZ Auschwitz-Birkenau Eisenbahnwagen
ምስል DW/R.Romaniec

1, «ዶ/ር መንገለ ወደ እኛ ጠጋ አለና ተዋወቀን፣ ከዚያም ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ለሚሄዱት በእጁ አመላከተ። ወደ ግራ የተባሉት ጥቂት የምሕረት ጊዜ የሚሰጣቸው ሲሆኑ፤ ወደ ቀኝ የሚሄዱት ወዲያው በጋዝ እንዲያልቁ የተበየነባቸው ናቸው።»

ከቅጽበታዊ ግድያ የተረፉት መልአከ -ሞት የሚል ተቀጥላ ሥም በተሰጠው፤ ዶ/ር ዮሰፍ ሜንገለ በተባለው ግፈኛ ሀኪም ውሳኔ ነው። ከጦርነቱ ፍጻሜ በኋላ የልጆች የሥነ ልቡና ጉዳይ ባለሙያ የሆኑት ማግዳ ሆላንደር ላፎን የሚኖሩት በፈረንሳይ ሲሆን ፣ ስለአሠቃቂው አውሽቪትዝ መጽሓፍትም ጽፈዋል።

በአውሽቪትዝ -ቢርከናው፣ ሰው በጋዝና እሳትና የተንጨረጨረበት ፤ የተለያዩ ሰው መውሰድ የሚችለው የግፍ ዓይነቶች የተፈጸሙበት ታሪክ፣ በተለያዩ ዘጋቢና መደበኛ ፊልሞች ሕያው ሆኖ እንዲዘልቅ ተደርጓል። ራሱ ቦታው አውሽቪትዝ ፣ የአውሽቪትዝ ምርመራና ብይን፤ «ሆሎኮስት» ፣« ሾዋ» እንዲሁም «ሺንድረስ ሊስት» እና የመሳሰሉ ፊልሞች፤ ሰው ከዚያ ዓይነቱ አረመኔያዊ ተግባሩ እንዲታቀብ ትምህርት ይሰጣሉ ተብሎ ነው የሚታሰበው። እዚህም ላይ የክሎድ ላንትዝማን ና የአልፍረድ ሂችኮክ ፊልሞች በዋቢነት የሚጠቀሱ ናቸው። በመሆኑም የአሽዊትዝ ግፍ የሚታሰብበት ሁኔታ በጀርመናውያን ዘንድ ለዘለዓለም የሚኖር እንጂ ችላ ይባላል ተብሎ ፈጽሞ አይታሰብም።

በአውሽቪትዝ፤ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ነው ሆን ተብሎ በተቀነባበረ የግድያ ስልት ሕይወቱን ያጣው። ወደ ጋዝ ምድጃ እየተወረወሩ ያለቁት አብዛኞቹ ይሁዲዎች ነበሩ። የፖላንድ ተወላጆች፤ እንዲሁም ሲንቲ ሮማ የተባሉትም ወንዶች፤ ሴቶች፤ እንዲሁም ልጆች በብዛት ከመላይቱ አውሮፓ እየተዳኑ እንዲጠፉ ተደረገ።በተዓምር የተረፉ ጥቂቶችና የዕድሜ ጸጋም ያገኙ እስከዛሬ ድረስ የዚያን ወቅት ዝግናኝ የሰው ተግባር እየተረኩ ዓለም በመላ ዳግም ያን ዓይነቱ ድርጊት እንዳይፈጽም ያስጠነቅቃሉ። እ ጎ አ በ 1933 በሩሜንያ የተወለዱት ሞርደሻይ ሮነን ፤ እንዲህ ይላሉ።

«ድል አድራጊ ነኝ፤ ዓለም በመላ ከዚህ ድርጊት ትምህርት መቅሰምና በሰላም መኖር ይጠበቅታል። ነገር ግን በዓለም ሰላም የለም ፤ ገና አልሰፈነም።»

እ ጎ አ በ 1929 በቀድሞዋ ቼኮዝሎቫኪያ የተወለዱት ሮዝ ሺንድለር ከአውሽቪትዝ እንዴት እንደተረፉ ሲያብራሩ---

«አባቴን በአንድ መሥመር ከወንድሜ ጋር አሰለፉት እናቴና 4 እኅቶቼ በሌላ መሥመር መሰለፍ ግድ ሆነባቸው። ሁለቱ እኅቶቼም በሌላ መሥመር ነበርንና ዕድሜሽ ስንት ነው? አለኝ። 18 አልኩት። እYeቴ ሄለን አይደለም ገና 14 ናት አለች። እኔም ትክክል አይደለም ፣ 18 ነኝ አልሁ --ደግሜ። እርሱም ከዚያ ከእህቶቼ ጋር እንድንመለስ ፈቀደ። እንደዚያ ባይሆን ኖሮ ፤ ዛሬ በሕይወት አልገኝም ነበር።ከእናቴ ከታናሽ እኅቶቼና ወንድሜ ጋር በጋዝ ወደመግደያው ክፍል እወረወር ነበር።»

Merkel bei der zentralen Auftaktveranstaltung 70 Jahre Auschwitz Befreiung 26.01.2015 Berlin
ምስል picture-alliance/dpa/B. von Jutrczenka

ወ/ሮ ማግዳ ሆላንደር ላፎን፣ በአሽዊትዝ -ቢርከናው፣ እርሳቸውና ባልደረቦቻቸው በናዚዎች እየተገረፉ ድንጋይ መሸከም ፤ የተገደሉ ሰዎችን የተቃጠለ አስከሬን ጉድጓድ ውስጥ መጣል ሥራቸው እንደነበረ ገልጸዋል። እንደ ጥላቻና ፍርኀት፤ ሞት ከቅርብ በየዕለቱ የሚታይ ስልነበረ፤ ለመሞት ምንጊዜም ዝግጁ እንደነበሩም ነው እውነተኛውን ታሪክ የሚናገሩት። ማግዳ ሆላንደር ላፎን፤ ከቤተሰብ የተረፉ እርሳቸው ብቻ ናቸው። ጀርመናዊ ናዚዎችና የሃንጋሪ ረዳቶቻቸው፤ ያኔ በሃንጋሪ ይኖሩ የነበሩ 437,402 ይሁዲዎችን ወደ አውሽቪትዝ ማጋዛቸው ይነገራል፤ አብዛኞቹ እዚያው ያ እንደደረሱ ነበረ በጋዝ ሕይወታቸውን ያጡት። Zyklon B በተባለው ናዚዎች በቀመሙት ጋዝ ያለቁት ብዙዎች ናቸው። ግድያውና ማቃጠሉ ፤ ቀንም ሌትም ነበረ የሚካሄደው። ከ 70 ዓመት በፊት ፣ በሶቭየት ሕብረት ቀይ ጦር ሠራዊት በተሰኘው ኃይል ዘመቻ አውሽቪትዝ ነጻ ከመውጣቱ በፊት ፤ ስለተፈጸሙ ድርጊቶች እንዴት መረጃ ስዕሎችና የመሳሰለ ሊገኝ ቻለ?

ከጦርነቱ ፍጻሜ በኋላ፣ በጀርመን ሃገር ማንኛውም ሰው ፣ ስለጭፍጨፋው ምንም አላየሁም ፤ አልሰማኹም ነበረ የሚለው። በርገን ቤልዘን የተባለውን የሕዝብ ማጎሪያ ጣቢያ፣ ነጻ ያወጡት እንግሊዞች ፣ የሬሳ ክምር፤ እንዲሁም በአጥንትና ጅማት የቀሩ ሰዎችን የአካባቢውን ኑዋሪ ሕዝብ አስገድደው እንዲመለከት ማድረጋቸው የታወቀ ነው። በዚያ የነበረው ሁኔታም በፊልም ተቀርጾ በማስረጃነት ቀርቧል። እርግጥ ነው ፊልሙ ለተወሰነ ጊዜ ለሕዝብ እንዳይታይ፣ በእንግሊዞችና በአሜሪካውያን ታግዶ መቆየቱ አልታበለም ፣ ይህም የሆነው በቀዝቃዛው ጦርነት ሳቢያ መሆኑን የቅርብ ጊዜው የታሪክ ዓምድ ያስረዳል። በአውሽቪትዝ ስለተፈጸመው ወደረ የሌለው የግፍ ተግባርና ስለጥፋተኛው ፣ ውይይት ተከፍቶ በይፋ ከመገለጡ በፊት ዐሠርተ-ዓመታት ነበሩ ያለፉት። እ ጎ አ ከ 1963-1965 ነበረ በፍርንከፈርት የአውሽቪትዝ የግፍ ተግባር ምርመራ የተከፈተው። በሕይወት የተረፉ ሰዎች ስለአሠቃቂው የግፍ ተግባር ምሥክርነታቸውን እንዲሰጡ ተደረገ። ከዚያ በኋላ አውሽቪትዝ ከጀርመናውያን የቅርብ ጊዜ ታሪክ ፈጽሞ የማይፋቅ፣ ምንጊዜም ኀላፊነትን የሚያሸክም ዐቢይ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል።

Konzentrationslager Auschwitz-Birkenau
ምስል DW/D.Bryantseva

በዚያ የአውሽቪትዝ የግፍ ተግባር እጃቸውን ያስገቡ ፤ በገቢ ረግድ ትርፍም ያገኙ I,G Farbenን የመሳሰሉ ኩባንያዎች ለኃላፊነቱ ከግንባር ቀደም ተጠያቂዎቹ መካከል ይገኙበታል።ከተጨፈጨፉት ሰዎች የጸጉር ክምር ፤ የዓይን መነጽርና ጫማ በመሰበሰብ ራሳቸውን ተጠቃሚዎች አድርገዋልና! ጸሐፌ ተውኔት ፔተር ቫይስ እ ጎ አ በ 1965 ከምርመራና ብይን በኋላም ውይይቱ እንዲቀጥል ነበረ ያበቁት።

እ ጎ አ በ 1070ኛዎቹ ማለቂያ ላይ በዩናይትድ ስቴትስ የተሠራው ፣ ሜሪል ስትሪፕ ዋና ተዋናይት የሆነችበት «ሆሎኮስት» የተሰኘው ተከታታይ፣ በአንድ « ቫይስ » በሚባል የ ይሁዲ ቤተሰብ ላይ የደረሰውን ዕጣ ፈንታ የሚያሳይ ፊልም ቀረበ። እ ጎ አ በ 1985 በክሎድ ላንትዝማን ፤ ተከታታይነት ያለው «ሾዋ» የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ተደገመ።

እ ጎ አ ጥቅምት 11 ቀን 1998 የጀርመንን የመጽሐፍት ማሕበር ሽልማት ያሸነፉት ማርቲን ቫልዘር በፍራንክፈረት የቅዱስ ፓውሎስ ቤተክርስቲያን ፤ የጦፈ ክርክር ያስነሳ እንዲህ የሚል ንግግር ማሰማታቸው የሚታወስ ነው።

«በየዕለቱ በመገናኛ ብዙኀን ፣ ያለፈውን «ሆሎኮስት»ን የሚመለከት ዝግጅት ማቅረቡ ፤ ከመንዛዛቱ የተነሣ አሳፋሪውን ተግባራችንን አልነበረም ብለን እንድንክድ ሳይገፋፋን አይቀርም ፣ ስለአሣፋሪው ድርጊታችን ፣ እሰየው እንኳን እውነቱን ዐወቅን ከማለት ፤ ሲበዛ ፤ በበኩሌ ዞር ብየ ሌላ ነገር መመልከት ነው የሚቃጣኝ። »

ናዚዎች ፤ በአውሽቪትዝ ብቻ አልነበረም ግድያ ያካሄዱት፤ ማይዳኔክ፤ ትሬብሊንካ፤ ቤልዜክ፤ ሶቢቦር ፣ እነዚህ ሁሉ የህዝብ ማጎሪያና መጨፍጨፊያ ነበሩ። ራቨንስብሩዑክ፣ ዳክሃው፤ ቡኸንቫልድ ማውትሐውዘን እና ሌሎች የህዝብ ማጎሪያ ጣቢያዎችም ፤ በግርፋት ፤ በግፍ ርምጃ ቁም ሥቅል በማየት፣ በካባድ ሥራና ለረሃብ በመዳረግ የብዙ ሰዎች ሕይወት የጠፋባቸው ቦታዎች ናቸው።በዩክሬይን ፤ ኪቭ ፤ አጠገብ ፣ ባቢን ያር በተሰኘው ሸለቆ ፤ ወይም ቪልኑስ አቅራቢያ በፖናር ጫካ የሚገኝ ጣቢያም ለተጠቀሰው እኩይ ተግባር የዋለ ነበረ።

የ 90 ኦመቷ ኤስተር ቤጃራኖ ፤ በአውሽቪትዝ ይከሠት ስለነበረው ዘግናኝ ሁኔታ እንዲህ ብለዋል።

Konzentrationslager Auschwitz-Birkenau
ምስል DW/D.Bryantseva

«ተንቀጠቀጥን፣ አለቀስን፤ እንባችን እንደ ጎርፍ ፈሰሰ፣ ፍጹም የሚዘገንን ነበር ፤ በሕይወቴ የተመለከትኳቸው የተለያዩ አሳዛኝ ሁኔታዎች አሉ ፤ ያ በአውሽቪትዝ የተመለከትኩት ግን በሕይወቴ ከቶውንም አጋጥሞኝ የማያውቅ ነው። ምክንያቱም ፣ አቅመ -የለሽ ያደርጋል። ሰዎቹን በምንም ዓይነት መርዳት አይቻልም፤ ግን እናውቀዋለን፣ በጋዝ ታፍነው ወደሚገደሉበት ክፍል እንደሚወሰዱ!። ዝም ብለን ፤ ምንም እንዳልሆነ እንጫወታለን። እጅግ አሳዛኝ መጥፎ ነገር!»

ስለ አውሮፓውያን አይሁድ መጨፍጨፍ ከፈረንሳይ ይልቅ በጀርመን በሰፊው እንደሚወሳ የጠቀሱት ማግዳ ሆላንደር ላፎን ፤ ጀርመናውያን እጠላ እንደሁ የሚጠይቁኝ ወጣቶች አሉ ፣ ብለዋል። መልሳቸው ታዲያ ፣ በጀርመናውያንና በናዚዎች መካከል ልዩነት አለ የሚል ነው። ጀርመናውያን ሁሉ ናዚዎች አልነበሩም። ፈረንሳውያን ሁሉም ከናዚዎች ጋር የተባበሩ አልነበሩም» ሲሉ ከአውሽቪትዝ የጅምላ ጭፍጨፋ የተረፉት የ 87 ዓመቷ ባልቴት አስረድተዋል።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ