1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ ተዛማች ጉንፋን መሰል ህመም እና ኮሮና

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 26 2014

ኢትዮጵያ ውስጥ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በፍጥነት የሚተላለፍ ጉንፋን መሰል ህመም ከብዙዎች ጓዳ መግባቱ እየተነገረ ነው። የጤና ሚኒስቴር በየ24 ሰዓቱ የሚያወጣው የኮሮና ተሐዋሲ ምርመራ ያደረጉ ሰዎች መረጃ በተሐዋሲው የተየዙት ቁጥራቸው በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መሆኑን ያሳያል።

https://p.dw.com/p/45634
New Corona Virus Omikron
ምስል picture alliance / Zoonar

አዲሱ ተዛማች ጉንፋን መሰል ህመም እና ኮሮና

 

ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ በኮቪድ 19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን መጨመሩን የኅብረተሰብ ጤና ተቋም ይፋ አድርጓል። እንደ ተቋሙ መግለጫም ከሳምንታት በፊት አምስት በመቶ የነበረው በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች ብዛት በመቶኛ ሲሰላ ባለፉት ቀናት ግን ወደ 36 በመቶ አድጓል። በዚህም ኢትዮጵያውስጥ አዲስ የኮቪድ 19 ተሐዋሲ ወጀብ መከሰቱን ጠቅሶ ኅብረተሰቡ ያለመሰላቸት ጥንቃቄ ያድርግ ሲል አሳስቧል። ዶክተር አስቻለው ወርቁ የውስጥ ደዌ የሳንባ እና ጽኑ ህክምና ባለሙያ ናቸው። ኮቪድ 19 በመላው ዓለም ወረርሽኝ መሆኑ ይፋ ከተደረገ ሁለት ዓመት ሊሞላ መሆኑን በማመላከት ኢትዮጵያ ውስጥ ተሐዋሲው ከተከሰተ ወዲህ በተለያዩ ጊዜያት በወጀብነት መቀስቀሱን አስታውሰው የኢትዮጵያ የማኅበረሰብ ጤና ተቋም እንዳለው አዲስ የኮሮና ተሐዋሲ ወጀብ መቀስቀሱን  ያረጋግጣሉ። በአሁኑ ወቅት ብዙዎችን እያዳረሰ መሆኑ በሚነገርለት ጉንፋን መሰል ተላላፊ ህመም ከተያዙ እና ከተመረመሩት መካከል አብዛኞቹ በኮቪድ 19 መያዛቸው መረጋገጡንም አንስተዋል። እሳቸው እንደሚሉትም የህመም ምልክቶቹ ቀደም ሲል ከነበረ ጋር ሲነጻጸር እጅግ ጠንካራ ባለመሆናቸው ነው ኅብረተሰቡ ጉንፋን ነው ብሎ እንዲገምት ያስቻለው እንጂ ኮቪድ 19ኝነቱ ከተመረመሩት ላይ በተገኘው ውጤት ተረጋግጧል። ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙውን ጊዜ ሰው ህመሙ ካልጠና በቀር ወደ ሀኪም ዘንድ ሄዶ የመመርመር ልማድ የለውም። የሚፈልግ ቢኖርም የአቅም ጉዳይም ሌላው ጥያቄ ነው። በኮቪድ 19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ይፋ የሚሆነው የመመርመር ዕድል ያላቸውን ሰዎች ውጤት መሠረት ያደረገ ነው። በብዛት የመመርመር ዕድሉ ቢመቻች ቁጥሩ ከሚገለጸው ሊበልጥ እንደሚችል የሚገምቱ አሉ። ዶክተር አስቻለውም በዚህ ይስማማሉ። ኅብረተሰቡ መዘናጋት ትቶ በመጀመሪያ ተሐዋሲው ሀገር ውስጥ መግባቱ ይፋ ሲሆን የታየው አይነት ጥንቃቄ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አጽንኦት ይሰጣሉ።

Äthiopien Addis Ababa | Maßnahmen gegen die Ausbreitung des Coronavirus
ምስል Solomon Muche/DW
Äthiopien Hidar Beshita | Addis Abeba im Smog
ምስል Yared Shumete

የተሐዋሲው በፍጥነት መዛመት ከግለሰብ አልፎ በሀገር ደረጃ ተጽዕኖ ማምጣቱ ስለማይቀር ከዚህ ባለፈ ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ ሰዎች ሊያደርጉ የሚገባው የተደነገገ ደንብ በመኖሩ ያንን በሕግ አግባብ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም አስታውሰዋል። መከተብም ሌላው ሊዘነጋ የማይገባ ነውም ብለዋል። ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ የውስጥ ደዌ፣ የሳንባ እና ጽኑ ህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር አስቻለው ወርቁ እናመሰግናለን። ሙሉ ቅንብሩን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ