1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የሶማሊያ ካቢኔ

ረቡዕ፣ የካቲት 4 2007

አዲሱ የሶማሊያ ካቢኔ ሃገሪቱን ከሁከትና አመፅ ነፃ አድርጎ የመምራት ሃላፊነት ተረክቧል ። 25 አባላት ያሉት አዲሱ ካቢኔ ከትናንት በስተያ ነበር በሶማሊያ ፓርላማ የፀደቀው ። የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦማር አብዱረሺድ አሊ ሻርማርኬ ለፓርላማው ያቀረቡት ካቢኔ የጸደቀው ከ3 ሙከራ በኋላ ነው ።

https://p.dw.com/p/1EZja
Somalias Premierminister Omar Abdirashid Ali Sharmarke
ምስል M. Abdiwahab/AFP/Getty Images

የካቢኔው መጽደቅ በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓም በአዲሱ ህገ መንግሥት ላይ ለሚሰጠው ህዝበ ውሳኔና በዚሁ ዓመት ለሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም ዝግጅት ወሳኝ እርምጃ መሆኑ ተነግሯል ።

ከዓለማችን እጅግ አደገኛ የምትባለዋን ሃገር ሶማሊያን እንዴት ማስተዳደር ይቻላል ለሚለው ጥያቄ ባለፈው ሰኞ ሃላፊነት የተረከቡት 25 የሶማሊያ ካቢኔ አባላት በተቻለ ፍጥነት አሳማኝ መልስ ሊፈልጉለት ይገባል ትላለች ዩልያ ሃን ዘገባዋን ስትጀምር ። ሚኒስትሮቹ የተረከቧት ሶማሊያ የሥልጣን ሽኩቻ የቀጠለባት ደፈጣ ተዋጊው ቡድን አሸባብ በተለያየ ጊዜ ጥቃት የሚያደርስባት ሃገር ናት መቀመጫውን ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ ባደረገው ዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም የሶማሊያ ጉዳዮች ተንታኝ አንድሪው አታ አሳሞዋ እንዳሉት ባለፈው ሰኞ ፓርላማው ሃላፊነታቸውን ያፀደቀው የሶማሊያ ሚኒስትሮች ፖለቲከኞች ሳይሆኑ ባለሞያዎች ናቸው ።

«አዳዲስ ሰዎች ይገኙበታል ፤በፖለቲካው ብዙም ልምድ የሌላቸው ሰዎች ይህ የተደረገው በቅርብ ጊዜ የሶማሊያ ታሪክ ውስጥ አሉታዊ ታሪክ የሌላቸውን የሶማሊያን ህዝብ ጉጉትና ፍላጎቶች ለሟሟላት ቆርጠው የተነሱ ሰዎችን ማስገባት በማስፈለጉ ነው ።

African Union Mission in Somalia AMISOM in Mogadischu am 25.12.2014
ምስል Getty Images/AFP/Mohamed Abdiwahab

የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦማር አብዲረሺድ አሊ ሻርማርኬ በመጀመሪያ ካቀረቡትየ25 ሰዎች ስም ዝርዝር ፓርላማው 10 ሩን አልተቀበለም ነበር ።ፓርላማው የሰዎቹን ምርጫ ውድቅ ያደረገው የቀድሞው መንግሥት አባላት ናቸው ሲል ነበር ። ሽርማርኬ ለሶስተኛ ጊዜ ያቀረቡት የሚኒስትሮች ዝርዝር ነው ባለፈው ሰኞ የብዙሃኑን ድጋፍ አግኝቶ ያለፈው ። አዳዲሶቹ ሚኒስትሮች የቀድሞ ችግሮችን አስወግደው ሃገሪቱ ወደፊት እንድትጓዝ ያደርጋሉ የሚል ተስፋ ተጥሎባቸዋል ። ይሁንና ለዚህ ሥራ ጊዜው በቂ መሆኑ ያጠራጥራል ። የሶማሊያ መንግሥት ሶማሊያውያን በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በመጋቢት 2016 ህዝበ ውሳኔ የሚሰጡበትን አዲስ ረቂቅ ህገ መንግሥት ማጠናቀቅ ይኖርበታል ።ከ6 ወራት በኋላ ደግሞ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ይካሄዳል ። ለነዚህ ምርጫዎች ደግሞ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል ።በሃገሪቱ አሳሳቢ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ የፀጥታ ችግር ነው ።ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ በጦርነት በተመሰቃቀለችው በሶማሊያ ደፈጣ ተዋጊው ቡድን አሸባብ ሰቆቃና ሽብር እየነዛ ነው ። ጥቃቶችና የቦምብ ፍንዳታዎች በየዕለቱ የሚያሳስቡ ጉዳዮች ናቸው ።የሶማሊያ ፓርላማ አዲሱን ካቢኔ ባፀደቀበት እለት እንኳን አንድ የፓርላማ አባል በአሸባብ ተተኩሶባቸው ተገድለዋል ። አንዳንድ ሶማሌዎች ግን የሃገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ መሻሻሉን ነው ለዶቼቬለ የሚናገሩት ።

«ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ቤት ውስጥ ነው የምንቆየው ።ሆኖም ፖሊስና ወታደሮች ማታ መንገዶችን ሮንድ እየዞሩ ይጠብቃሉ ።ይህ ከ10 ዓመታት በፊት የሚታሰብ አልነበረም ።»

Symbolbild al-Shabaab Kämpfer in Somalia
ምስል Imago/Xinhua

የሶማሊያ መንግሥት በአፍሪቃ ህብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ኃይል በምህጻሩ AMISOMና በዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ ደፈጣ ተዋጊዎችን እየተከላከለ ነው ።ባለፈው ሳምንት በዩናይትድ ስቴትስ አብራሪ-አልባ የጦር አውሮፕላን ጥቃት ዩሱፍ ድሄቅ የተባለው የአሸባብ አዛዥ ተገድሏል ።ተንታኙ አሳሞዋ እንደሚሉት አሸባብ ይዞታውን እያጣ ቢሆንም አሁንም አልተረታም ።

« አሸባብ ተዳክሟል ። ከውጊያው አልወጣም ። ውጊያውም አልቆመም ። ሆኖም መንግሥት አሸባብን መጣል የሚችል ጥንካሬ የለውም ። ስለዚህ አሁንም አሸባብ በሃገሪቱ በጣም ትልቅ ተፅእኖ ማሳደር ችሏል ።የሶማሊያን የፀጥታ ሁኔታ የመቆጣጠር ብቃት አላቸው ። አሸባብ በሶማሊያ በጎርጎሮሳውያኑ 2016 ምርጫ መካሄድ አለመካሄዱን በመወሰን ረገድ ከፍተኛ ተፅእኖ የሚያሳድር ነው የሚሆነው »

ታዛቢዎች መንግሥት አሸባብን ማሸነፍ ያቀተው በከፊል በሃገሪቱ ፕሬዝዳንትና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል በሚካሄድ ሽኩቻ ምክንያት ነው ይላሉ ። ይህ የሥልጣን ሽኩቻ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች እንዳይተላለፉ እንቅፋት ሆኖ ዘልቋል እንደ ታዛቢዎቹ ።

ኂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ