1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የኢትዮጵያዉያን የኪነጥበብ ማኅበር በሰሜን አሜሪካ

ሐሙስ፣ ሰኔ 20 2011

በሰሜን አሜሪካ የሥነ-ፅሁፍ ፣ ቴአትር ፣ ሙዚቃ ፣ ውዝዋዜ ፣ ፊልም ፣ ሥዕል ፣ ቅርፃቅርፅና የመሳሰሉ ሙያ ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ። እነዚህን የጥበብ ሰዎች አንዲሁም አድናቂዎች በአንድ ጥላ ስር ለማሰባሰብ እና ለማደራጀት የሚያስችል የኢትዮጵያውያን የኪነ-ጥበብ ማህበረሰብ በሰሜን አሜሪካ የተሰኘ ማኅበር ሊመሰረት ዝግጅቱ ተጠናቆአል።

https://p.dw.com/p/3L8Ld
Ethiopian Cultural Association in Northern America
ምስል Yohannes Molla

በሰሜን አሜሪካ የሥነ-ፅሁፍ ፣ ቴአትር ፣ ሙዚቃ ፣ ውዝዋዜ ፣ ፊልም ፣ ሥዕል ፣ ቅርፃቅርፅና የመሳሰሉ ሙያ ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ። እነዚህን የጥበብ ሰዎች አንዲሁም አድናቂዎች በአንድ ጥላ ስር ለማሰባሰብ እና ለማደራጀት የሚያስችል የኢትዮጵያውያን የኪነ-ጥበብ ማህበረሰብ በሰሜን አሜሪካ የተሰኘ ማኅበር ሊመሰረት ዝግጅቱ ተጠናቆአል።

ከማኅበሩ መስራችን አንዱ «ቂምና ይቅርታ» ሲል የቋጠራት ስንኝ

«እግሮቹን ቆራርጠዉ ዓይኑን እንዳጠፉት ልቡ እያወቀ፤ በንፉቅቁ ሄዶ እነኛን ግፈኞች ይቅር ሊል ፈቀደ። በፍፁም ትህትና ራሱን ዝቅ አድርጎ ቆሞ ከበራቸዉ፤ ከመሬት ላይ ወድቆ በአንድ ዓይኑ እገዛ ሽቅብ ቢያስተዉላቸዉ፤ ይቅርታዉ ሟሸሸች፤ የወጉት የደሙት በጥይት የቆሉት ታይቶት ጭካኒያቸዉ። ታገለ ከራሱ፤ ገድለኸዋል እኮ መትረፍህ ተዓምር ነዉ ይለዋል ስሜቱ። ይቅር በል ይቅር በል፤ የፈጣሪዉ ትዕዛዝ ይጮኻል ከዉስጡ። በቂምና ይቅርታ መሃል ተወጥሮ፤ ግራ እንደተጋባ ቀረ ተኮማትሮ። ለካ ሰዉ ሲበድል በሁለት አስልቶ፤ አንድም በህሊና በስጋ አሰቃይቶ፤ አንድም እጅግ ፈታኝ እግዜር የሚያርመዉ የቤት ስራ ሰቶ። »

 ፀሐፊ ቴዮድሮስ ታደሰ የቋጠራት ስንኝ ነች።  በሰሜን አሜሪካ አትላንታ ዉስጥ ነዋሪ የሆነዉ እና በሥነ-ግጥምቹና በሥነ -ጽሑፉ በኢትዮጵያዉያን ዘንድ ታዋቂነትን ያተረፈዉ ቴዮድሮስ ታደሰ በሚኖርበት በሰሜን አሜሪካ ኢትዮጵያዉያን የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች በአንድ ጥላ እንዲሰባሰቡ በማኅበር እንዲደራጁ ኃሳብ አፍልቆ፤ ተግባራዊ ሊደረግ ጥቂት ቀናት ቀርተዉታል። አንጋፋዋን ፀሐፊ የመድረክ እንቁ አርቲስ ዓለምፀሐይ ወዳጆን ጨምሮ በፀሐፊ ቴዮድሮስ ታደሰ አነሳሽነት በቅርቡ 15 የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች የፊታችን  ሰኔ 27 ማለትም ጁላይ 04 በአትላንታ ጆርጅያ ላይ «በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ማኅበር» የተባለ ተቋምን ሊመሰርቱ  ዝግጅታቸዉን አጠናቀዋል።  በርግጥ ማኅበሩ ከአገር ርቆ ለኪነ-ጥበቡ ዘርፍ የሚያበረክተዉ አስተዋፅኦ ይኖር ይሆን። ማኅበሩን ለመመስረት በዝግጅት ላይ ያሉ የኪነ-ጥበብ ባለሞያችን አነጋግረን ዝግጅት አቀናብረናል።

በሰሜን አሜሪካ  የሥነ-ፅሁፍ ፣ ቴአትር ፣ ሙዚቃ ፣ ውዝዋዜ ፣ የፊልም ፣ ሥዕል ፣ ቅርፃ ቅርፅና የመሳሰሉ ተሰጥዖ ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን  ይኖራሉ። በዋሽንግተን እና አካባቢዋ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች አንጋፋዋ የጥበብ ፈርጥ አርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆ በምታስተዳድረዉ «ጣይቱ የባህል ማዕከል» በየግዜዊ በመሰባሰብ ሥነ-ግጥም ፤ መጣጥፍ ፤ ትያትር እና የተለያዩ ባህላዊና ሃገራዊ ኹነቶችን ይለዋወጣሉ።  በአትላንታ ነዋሪ የሆነዉ ፀሐፊ ቴዮድሮስ ታደሰ እንደሚለዉ በአሜሪካ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዉያን የኪነ-ጥበብ ሰዎች መሰባሰብና ልምዳቸዉን መለዋወጥ መደጋገፍ አለባቸዉ ብዬ ማኅበር ለመመሰረት ሃሳቡ የመጣልኝ የዛሬ ሁለት ዓመት ነዉ። 

Ethiopian Cultural Association in Northern America
ምስል Yohannes Molla

«በሰሜን አሜሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ዓመታዊ የእግርኳስ ዉድድራቸዉን ሳንሆዜ ላይ ባካሄዱበት ወቅት የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ነበር ይህን ሃሳብ አንስቼ ከተወሰኑ ሰዎች ጋር የተወያየሁት። የተወሰነ ከተጓዝን በኋላ ማለትም የኳስ ግጥምያዉ ሊካሄድ ሁለት ሦስት ሳምንት ሲቀረዉ አይ ነገሩን አሁን በቅጡ ስላልተዘጋጀንበት በአሁኑ ወቅት ማቅረቡ ጥሩ አይሆንም ብለን ለጊዜዉ ተዉነዉ ። ሌላ ጊዜ ተዘጋጅተን እናቀርባለን በሚል ተስማማን። በሚቀጥለዉ ይኸዉ የኢትዮጵያዉያኑ የእግርኳስ ጨዋታ ዳላስ ላይ ተካሄደ ። ነገሩን ሳናነሳ አለፍን። አሁን ግን የኳስ ግጥምያዉ አትላንታ ስለሚካሄድ የምኖረዉም አትላንታ በመሆኑ ጉዳዩን ለማንሳት ወሰንኩ ነገሩንም በፊስ ቡክ አሳወኩ። በአሁን ወቅት ከኔ ጋር አስራ አምስት በተለያዩ በኪነ-ጥበብ ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያዉያን በጋራ ሆነን የኪነጥበብ ሰዎች እንዲሰባሰቡ ጠርተናል።»    

 «የብርሃን ልክፍት» «የብርሃን ስብስቦች » በተሰኝ ለአንባብያን ባቀረባቸዉ ሁለት የግጥም መድብሎቹ የሚታወቀዉ ሌላዉ ፀሐፊ ዮሃንስ ሞላ፤ ማኅበሩን ለመመስረት በሥራ ከተጠመዱት አስራ አምስት የኪነ-ጥበብ ሰዎች አንዱ ነዉ። የሥነ-ግጥም ባለሞያዉ ዮሃንስ የተለያዩ ኢሜሎችን የስልክ ጥሪዎችን በማድረግ ኢትዮጵያዉያን የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎችን እና አፍቃሪዎችን በማሰባሰብ ላይ ይገኛል።

ከአስራ አምስቱ የማኅበር መስራቾች መካከል በሰሜን አሜሪካ ሜኒሶታ ዉስጥ ነዋሪ የሆነችዉ ሌላዉ ፀሐፊ ዘመናይ ዘሪሁን ትባላለች። ዘመናይ እንደተናገረችዉ ከሆነ በሰሜን አሜሪካ በተለያዩ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን የኪነ-ጥበብ ሰዎች በየመኖያ አካባቢያቸዉ የተለያዩ ዝግጅቶች ቢኖራቸዉም ቅሉ በአንድ የሚያሰባስብ ማህበር ያስፈልጋቸዋል።

ፀሐፊ ቴዮድሮስ ታደሰ በበኩሉ ማኅበሩን መመስረት ያስፈለገዉ በሰሜን አሜሪካ በሚኖሩ የኪነ-ጥበብ ሰዎች መካከል ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ነዉ ብሎአል።

ፀሐፊ ዮሃንስ ሞላም፤ የሚመሰረተዉ ማኅበር የኪነ-ጥበብ ተሰጥኦ ያላቸዉን የሚያካትት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዉያን ሁሉ እንዲሰባሰቡበት እዉቀትና ሃገርኛ ኹነቶችንም እንዲለዋወጡበት ነዉ ሲል ተናግሮአል።

በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያዉያን የኪነ-ጥበብ ማኅበር የወቅቱ ተጠሪ  ፀሐፊ ቴዮድሮስ ታደሰ እንደገለጸዉ፤ የማህበሩ ዓላማ በተለያዩ የሰሜን አሜሪካ ግዛቶች ያሉ የጥበብ ሰዎችንና አድናቂዎችን በማሰባሰብ ፤  «እርስ በርስ ጠንካራ የግንኙነት መስመር ለመመስረትና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ«ጥበብን በመጠቀም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በበጎ ስራ ላይ ለመተባበር » «በየዓመቱ የሰሜን አሜሪካ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጅባቸው ከተሞች በመገኘት ለታዳሚው ጥሩና የተሻለ አማራጭ የሚፈጥር ደረጃውን የጠበቀ የኪነ-ጥበብ ዝግጅት ለማቅረብ» «የላቀ አስተዋፅዎ ላደረጉ አንጋፋ እንዲሁም ወጣት የጥበብ ሰዎች እውቅና ለመስጠትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ለመከወን ነው።» ሲል ገልፆአል። 

ምስረታዉ ሰኔ 27 ወይም ጁላይ 04, 2019 ከ2-5pm አትላንታ ከተማ በሚገኘው Doubletree by Hilton ሆቴል ውስጥ አርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆን ጨምሮ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ አንጋፋና ተወዳጅ የጥበብ ሰዎች የሚሳተፉበት ደማቅ የኪነ-ጥበብ መርሃ- ግብር መዘጋጀቱ ተመልክቶአል።  

በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩት ኢትዮጵያዉያኑ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች ያሰቡት ተሳክቶ ደማቅ ጠንካራ ትስስርን የያዘ የኪነ-ጥበብ ማኅበር አቋቁመዉ በመድረኩ ተገኝተን ሌላ መሰናዶ ለመስራት ያብቃን ። ለሰጡን ቃለ-ምልልስ እያመሰገንን ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ