1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የካቶሊካዉያን መንፈሳዊ አባትና አሰተያየት

ሐሙስ፣ መጋቢት 5 2005

የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ካርዲናሎች፣ በትናንት ማታ ስብሰባቸው፤ የ 76 ዓመቱን አዛውንት የቦይነስ አይረስ ፣አርጀንቲና ሊቀ ጳጳስ ሆርጌ ማሪዮ በርጎግሊዮን፣ በቅርቡ በጤና ሳቢያ ሥልጣናቸውን የለቀቁትን ርእሰ ሊቃነ-ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛ

https://p.dw.com/p/17yBs
ምስል Reuters

ቀጥሎ ከፍተኛውን ውጤት ያገኙ ሆርጌ ማሪዮ በርጎግሊዮ እንደነበሩም ታውቋል። በካቶሊካውያን የበላይ አባትነት ማዕረጋቸው ርእሰ-ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ፣ ከአውሮፓ ውጭ ለዚህ ከፍተኛ ሥልጣን ለመመረጥ ፤ ከ 1,282 ዓመታት ገደማ ወዲህ የመጀመሪያው ናቸው። አሁን የካቶሊካዊቷን ቤተ ክርስቲያን እጅግ ከፍተኛ ማዕረግ ለማግኘት የበቁት ርእሰ-ሊቃነ ጳጳሳት፣ ማን ናቸው?

Argentinen / Papst / Jubel
ምስል Reuters

ምንም እንኳ ከአውሮፓ ከፈለሱ ኢጣልያውያን ቤተሰብ ከተወለዱ 5 ልጆች መካከል አንዱ ቢሆኑም ፤ በዜግነት ፣ አርጀንቲናዊ ናቸው። የተወለዱት በመዲናይቱ በቦይነስ አይረስ ፣እ ጎ አ በ 1936 ዓ ም ነው። አሁን 266ኛው የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ-ጳጳሳት ለመሆን የበቁት፤ ሆርጌ ማሪዮ ቤርጎግሊዮ ፣ የክህነት ሥልጣን እ ጎ አ በ1969 ካገኙ በኋላ፣ በ 1998 የቦይነስ አይረስ ሊቀ-ጳጳስ፣ በ 2001 ደግሞ ካርዲናል ሆኑ።

ርእሰ-ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በላቲን አጠራር ፍርንሲስከስ ፣ በካቶሊካዊቷ ቤተ ክርስቲያን ሥር ኢየሱሳውያን የሚሰኘው ምድብ አባል ሲሆኑ ፣ የካቲት 11 ቀን 731 ዓ ም፣ ከተመረጡት ከሦሪያዊው የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ-ጳጳሳት «ፖፕ ግሪጎሪ» ወዲህ ፤ ከአውሮፓ ውጪ ከፍተኛውን የቤተ ክርስቲያኒቱን የበላይ ሥልጣን ለማግኘት ርእሰ-ሊቃነ ጳጳሳት ፍርንሲስ የመጀመሪያው ናቸው። ፍርንሲስ የተሰኘውን ስም የወሰዱት ፤ ጥንት ኢጣልያ ውስጥ በዑምብሪያ ክፍለ ሀገር በአሲሲ ንዑስ ከተማ ከተወለዱትና በኋላ ቅዱስ ፍራንስስ ከተባሉት የፍርንሲስካኖች ወንድማማችነት ማኅበር መሥራች ነው።

Papst Franziskus am Tag nach der Papstwahl in Santa Maria Maggiore
ምስል Reuters

ወደ ሥነ-መለኮት ትምህርት ከመመለሳቸው በፊት ፣ በቦይነስ አይረስ ዩንቨርስቲ፣ ሥነ ቅመማ (ኬምስትሪ ) በማጥናት ፣ በማስተርስ ዲግሪ መመረቃቸው ታውቋል።

ስለአዲሱ የሮማ ካቶሊካዊት ርእሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ማንነት ፤ የጀርመን ካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባዔ ሊቀመንበር ፣ የፍራይቡርግ ሊቀ ጳጳስ Robert Zollitsch

እንዲህ ብለዋል።

1,«ፍራንሲስኩስ ፣አዲሱ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት መርኀ ግብራቸው ህዝብን ማቅረብ ነው። በተለይም ድሆችንና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን!ይህ ደግሞ በግልጽ የተመሠከረላቸው ጉዳይ ነው!እንደ አንድ ኢየሱሳዊ ማኅበርተኛና የሥነ መለኮት ምሁር፣ በቋንቋም ቢሆን መገናኛ ድልድይ ገንቢ ናቸው። ያም ድልድይ የወላጆቻቸውን ሀገር ኢጣልያን ብቻ ሳይሆን ጀርመንና አውሮፓን የሚያጠቃልል ነው። እናም አሁን፤ ያገኘናቸውን «አባት» በትክክል ለመግለጽ ፣ ድልድይ ሠሪ ናቸው፤ የፖፕ ትርጉሙም ይኸው ነው።»

Papst Franziskus Fresko Franz von Assisi
ምስል picture-alliance/dpa

ከፕሮቴስታንቶች በኩል፤ የጀርመን ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ም/ቤት ሊቀመንበር ኒኮላውስ ሽናይደር፣ ስለአዲሱ ተመራጭ የካቶሊካውያን ርእሰ-ሊቃነ ጳጳሳት እንዲህ ነበረ ያሉት።

«ፍርንሲስኩስ ማለት ዓለምን ከድሆች አኳያ የሚያይ፣ ተፈጥሮ እንዲጠበቅ የሚታገልሲሆን፣ ሥልጣንን አጠንክሮና ደምቆ መታየትም የሚፈልግ አይደለም። ይህ ስም ብዙ ትርጉሞች ሊኖሩት ይችላል። አሁን ሁላችንም ፣ አዲሱ ፖፕ መርኅ-ግብራቸውና ስማቸው እንዴት እንደሚተሣሠ ር ፣ ዓላማቸውም እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን ለማየት በጉጉት እንጠብቃለን። »

በዓለም ውስጥ ፤ ከ 1,2 ቢሊዮኑ ካቶሊካውያን መካከል 40 ከመቶው የሚገኙት በላቲን አሜሪካ ነው ፤ ቁጥራቸው በዚያ እየጨመረ ሲኼድ አውሮፓ ውስጥ ግን በመመናመን ላይ ነው። 8 ዓመት ባልሞላው የቤኔዲክት 16ኛ የሥልጣን ዘመን ፣ ካቶሊካዊቷ ቤተ ክርስቲያን፣ የገጠሟት አሳሳቢ ችግሮች ፣ በተለይ ልጆች በካቶሊካውያን የሃይማኖት ሰዎች የተደፈሩበት የቅሌት ተግባር ፣ ጎልቶ የተነገረበትና ኀላፊነት የሚሰማቸውን የቤተክርስቲያኒቱን ሰዎች ያስጨነቀ ጉዳይ ነበረ። አሁንም ያሳስባቸዋል።

Papst Franziskus Leben in Argentinien
ምስል Reuters

ለተለያዩ ችግሮች መፍትኄ መሻትና ከቤተክርስቲያኒቱ የራቁትን ምዕመናን እንደገና ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱ ሰፊ ጥረት ማድረግ ፤ ለዘብ ያሉ ወግ አጥባቂ መሆናቸው የሚነገርላቸው ፣ የአዲሱ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ተግባር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። አዲሱ መሪ ፍራንሲስ ፣ በመጪው ማክሰኞ በዓለ-ሢመታቸው እንደሚከናወን ተነግሯል። በካቶሊካውያን በዓላት፤ ቀኑ የሚውለው በቅዱስ ዮሴፍ መታሰቢያ ዕለት ነው። እርሱም በዓለም ዙሪያ አያሌ ተከታዮች ያሏት ቤተክርስቲያን ዐቃቤ መሆኑ ነው የሚነገርለት።

የአርጀቲናዉ ካድርዲናል ሆኼ ማርዮ ቤኹሉዮ የሮማ ካቶሊካዊት ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳት ሆነዉ መመረጣቸዉ ከአዉሮጳ ዉጪ ለሚገኘዉ የካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ተከታይ አስደሳች ዜና ብጤ ነዉ የሆነዉ።አፍሪቃዊ በርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳትነት ይመረጥ ይሆናል ብለዉ ተመኝተዉ በነበሩት አፍሪቃዉያን ዘንድ ግን ደስታም ቅሬታም ሳይፈጥር አልቀረም።የሮሙ ወኪላችን ተኽለ እግዚ ገብረኢየሱስ እንደሚለዉ ደግሞ እዚያዉ ሮም ያሉ አፍሪቃዉያን ቀሳዉስትና የመንፈሳዊ ምሁራን ገና ከመጀመሪያዉ አፍሪቃዊ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ይመረጣል ብለዉ አልጠበቁም ነበር።ተኽለ እግዚን ሥለ አዲሱ ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳት ማንነትና ሥለ አፍሪቃዉያን ቀሳዉስት ስሜት በስልክ ጠይቄዉ ነበር።



የ ጋና ጳጳስ አስተያየት


ከአፍሪቃዊያን ካርዲናሎች ወይም ጳጳሳት መካካል የርዕሠ-ሊቃነ ጵጵስናዉን ሥልጣን ይይዛሉ ተብለዉ በሰፊዉ ተጠብቀዉ ከነበሩት ጋናዊዉ ጳጳስ ፒተር ታክሰን ግንባር ቀደሙ ነበሩ።የጋና የካቶሊካዉያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳት ጆሴፍ ኦሴ ቦንሱ ዛሬ እንዳሉት፥ አሁን ባይሳካም አፍሪቃዊ ለ-ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳስነት የሚመረጥበት ጊዜ ይመጣል።


የኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ የካቶሊካዉያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳት ብርሐነ የሱስ ደ ሡራፌል በበኩላቸዉ ርዕሠ-ሊቀና ጳጳሳት ፍራንስ ቤተ-ክርስቲያኒቱ ያጋጠማትን ችግር ለማቃለል ይረዳሉ የሚል እምነት አላቸዉ።

ተክሌ የኋላ

ተኽለ እግዚ ገብረኢየሱስ

ነጋሽ መሐመድ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ ዘገባዎች አሳይ