1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የዩኤስ አሜሪካ ትኩረት ለአፍሪቃ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 2 2006

ዩጋንዳ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት በእስር የሚፈለጉትን የዓማፂው ቡድን «ሎርድ ሬዚስተንስ አሚ፣ » በምሕፃሩ « ኤል አር ኤ» መሪ ጆሴፍ ኮኒን ለመያዝ በጀመረችው እንቅስቃሴ ላይ ዩኤስ አሜሪካ ተባብራ ትሰራለች። በዚሁ ትብብሯ ቀደም ሲል 100 ወታደሮች የላከችው የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ባለፈው

https://p.dw.com/p/1Bfr2
ምስል picture alliance/landov

መጋቢት አጋማሽም ተጨማሪ 150 ወታደሮች እና አይሮፕላኖችም ወደ ዩጋንዳ እንዲላኩ ወስነዋል። ያሜሪካውያኑ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፣ ዩኤስ አሜሪካ በዚሁ ርምጃዋ በአፍሪቃ የጦር ህልውናዋን በጉልህ ለማስፋፋት ማቀዷን የሚያሳይ ነው።

«ማዘር ጆንስ» የተባለው የኢንተርኔት መጽሔት በጀርመን የሽቱትጋርት ከተማ የሚገኘውን በምሕፃሩ «አፍሪኮም» በመባል የሚታወቀውን ለአፍሪቃ የተቋቋመው የዩኤስ አሜሪካ የጦር እዝ ጀነራል ዴቪድ ሮድሪጌዝን ጠቅሶ እንዳመለከተው፣ ዩ ኤስ ሜሪካ እአአ በ2013 ዓም በአፍሪቃ 546 ጊዜ ወታደራዊ እንቅስቃሴ አካሂዳለች። ይህ አሜሪካ በአፍሪቃ የጦር ህልውናዋን ለማጠናከር ጠንክራ እየሰራች መሆኑን በዋሽንግተን የፀጥታ ጥናት ተቋም« ሴንተር ፎር ፕሮግረስ ተመራማሪ ሩዲ ደ ሌዎን አረጋግጠዋል።

AFRICOM
ምስል AP

« የተሻራኪዎችን አቅም በመገንባቱ ላይ ጠንካራ ጥረት ሲደረግ እናያለን። ይህም፣ ያካባቢው ጦር ኃይላት ራሳቸውን መከላከል ፣ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ማጠናከር እና የሕግ የበላይነትን ማክበር የሚችሉበትን አቅማቸውን እንዲያጠናክሩ መርዳት ማለት ነው። »

ደ ሌዎን ትክክለኛ አሀዝ ባይጠቅሱም፣ «ሎስ አንጀለስ ታይምስ» ግን በአሁኑ ጊዜ ከ5,000 የሚበልጡ አሜሪካውያን ወታደሮች በ38 የአፍሪቃ ሀገራት ውስጥ ፣ በሶማልያ፣ ሊቢያ ወይም በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ጭምር፣ መሠማራታቸውን በማስታወቅ ፣ ይህ ለብዙ ጊዜ በጦርነት፣ በረሀብ እና በችግር ብቻ ተታወቅ የነበረችው አፍሪቃ ባሁኑ ጊዜ በዩኤስ አሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ላይ ትኩረት እያገኘች መሆንዋን በግልጽ የሚጠቁም ነው ብሎታል። ያሜሪካ መንግሥት እና ጠበብት አፍሪቃ ን ሥልታዊ ትርጓሜ እንደገና ማጤን መጀመራቸውን ሌላው የዋሽንግተን ጥናት ተቋም « ሲ ኤስ አይ ሲ» ባልደረባ ጄኒፈር ኩክ ገልጸዋል። ከሌላው የዓለም ከፊል የሚባረሩ አሸባሪዎች በአፍሪቃ መሸሸጊያ ሊያገኙ ይችላላሉ የሚለው ስጋት ለዚሁ ያስተሳሰብ ለውጥ ድርሻ ማበርከቱንም ኩክ አስረድተዋል። ነገር ግን፣ ባሜሪካውያኑ ፖሊሲ ቀዳሚውን ቦታ እንድትይዝ አድርጓታል ማለት አለመሆኑን ነው አክለው ያመለከቱት።

« የፀጥታ ስጋቶች ፣ አፍሪቃን ፣ በተለይ ከሌሎች አካባቢዎች ለሚባረሩ አክራሪ ቡድኖች እና ድንበር ተሻጋሪ የወንጀለኛ መረቦች አመቺ መሸሸጊያ ቦታ ሳያደርጉዋት አልቀሩም። ይህ ስለሆነም ፣ ትኩረት አግኝታለች፣ ግን፣ በዝርዝሩ ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ አልያዘችም። እስከምትይዝም ፣ ጥቂት ጊዜ ይወስዳል። »

Bewegung Befreiung Azawad Gebiet Tuareg Mali MNLA Afrika Mali
ምስል KENZO TRIBOUILLARD/AFP/Getty Images

በጄኒፈር ኩክ ግምት፣ ዩኤስ አሜሪካ በወቅቱ ከበስተጀርባ በመሆን በአነስተኛ ጦር ቡድኖች ብቻ መንቀሳቀሱን የመረጠችበት አንዱ ምክንያት ካሁን ቀደም በአሜሪካ አንፃር የታየው ዓይነቱን ጥላቻ ስሜት እንደገና ለመቀስቀስ ባለመፈለጓ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ግን፣ ለ«አፍሪኮም» የተመደበው በጀት ፣ ያሜሪካ ልዩ ትኩረት ባረፈባቸው በአፍጋኒስታን ወይም በፓሲፊክ አካባቢ ሀገሮች ለተቋቋመው የዩኤስ እዝ አንፃር፣ በጣም ንዑስ በመሆኑ ነው።

« የቀጥታ ጥቅማችንን በተመለከተ ፣ አፍሪቃ በአሁኑ ጊዜ ሌሎች የዓለም አካባቢዎች የያዙት ደረጃ ላይ አልደረሰችም። »

የ«አፍሪኮም አዛዥ ጀነራል ሮድሪጌዝም በቂ አብራሪ የለሽ መረጃ ሰብሳባ አይሮፕላን እንዳልቀረበላቸው ባለፈው መጋቢት ወር ለሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ኮሚቴ ማስታወቃቸው ይታወሳል። ደ ሌዎን እንዳሰረዱት፣ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ በሶርያ አንፃር በአፍሪቃ የሀገራቸውን የጦር እንቅስቃሴ ማስፋፋታቸው አበረታቺ ቢሆንም፣ ያሜሪካውያኑ ሥልት ፈረንሳይ በሰሜን አፍሪቃ በሚነቀሳቀሱ ዓማፅያን አንፃር ካካሄደችው ዓይነቱ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት መቆጠብ ነው። ካለፉት ዓመታት ወዲህ በአፍሪቃ ህልውናዋን በጣም ባስፋፋችው ቻይና አንፃር ይኸው ዩኤስ አሜሪካ በ«አፍሪኮም» አማካኝነት የምትከተለው ሥልት የተሳካ ውጤት ያስገኛል አያስገኝም የሚለውን ለማየት ትንሽ ጠብቆ ማየቱን እንደሚመርጡ ደ ሌዎን ገልጸዋል፣ ይሁንና፣ ሥልቱ በሩቅ ጊዜ ሲታይ ጥቅም ማስገኘቱ አይቀርም።

Szene aus dem US-Spielfilm "Black Hawk Down" (2001)
ምስል picture alliance/Mary Evans Picture Library

« የአፍሪቃን ጦር እዝ የማቋቋሙ ዓላማ፣ በመጀመሪያ ደረጃ፣ በአፍሪቃ ፣ ያሜሪካን ወይም የአውሮጳን ኢንቬስትመንት ለማስፋፋት አይደለም። በዚህ ፈንታ፣ በአካባቢው፣ በረጅም ጊዜ ሲታይ፣ ጥቅም የሚያስገኘውን መልካም አስተዳደር መፍጠር ነው። ምክንያቱም፣ አካባቢው የራሱን ተፈጥሮ ሀብት ራሱ መቆጣጠር እና የራሱን ዕጣም ራሱ መወሰን ይፈልጋልና። »

ጌሮ ሽሊስ/አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ