1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የፍልሰት ሕግ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 6 2011

በቀደመው ሕግ ሞያቸው ተፈላጊ የሆነ የውጭ ዜጎች በጀርመን ሥራ የሚያገኙት ለቦታው የሚመጥን ጀርመናዊ ቀጥሉ የአውሮጳ ኅብረት ዜጋ ካልተገኘ ነበር። እነዚህን ገደቦች ግን በአዲሱ ረቂቅ ሕግ ተሻሽለዋል። ከዛሬ 5 ወር በፊት የጀርመን ካቢኔ የተስማማበት ይህ ረቂቅ ሕግ የጀርመን አሠሪዎች ለዓመታት ሲያሰሙ ለቆዩት አቤቱታ መልስ የሚሰጥ መስሏል።

https://p.dw.com/p/3IUtf
Einwanderungsgesetz Bundestagsdebatte
ምስል picture-alliance/dpa/R. Hirschberger

አዲሱ የጀርመን የፍልሰት ሕግ

ጀርመን ውስጥ ከ1.6 ሚሊዮን የሚበልጡ ሞያተኛ ያላገኙ ክፍት የስራ ቦታዎች አሉ። በነዚህ የስራ ቦታዎች ተፈላጊዎቹን ባለሞያዎች ለመቅጠር ጀርመን ወደ ውጭ ማማትር ከጀመረች ቆይታለች። ሆኖም በየጊዜው  የሚወጡት የሀገሪቱ የፍልሰት ህጎች የሚያስቀምጧቸው መስፈርቶች ጀርመን ለመሥራት የሚፈልጉ የውጭ ዜጎችን የሚስቡ እና የሚያበረታቱም ባለመሆናቸው የሚፈለገውን የውጭ ሙያተኛ ማግኘት ሳይቻል መቆየቱን የመስኩ ምሁራን እና የጀርመን ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ይናገራሉ። ከዚህ ሌላ በቀደመው ሕግ ሞያቸው ተፈላጊ የሆነ  የውጭ ዜጎች በጀርመን የሥራ እድል የሚያገኙት ለሥራ መስኩ የሚመጥን  ጀርመናዊ ቀጥሉ የአውሮጳ ህብረት ዜጋ ካልተገኘ ነበር። እነዚህን የመሳሰሉት ገደቦች ባለፈው ሳምንትለጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በቀረበው በአዲሱ ረቂቅ ሕግ ተሻሽለዋል። ከዛሬ 5 ወር በፊት የጀርመን ካቢኔ የተስማማበት ይህ ረቂቅ ሕግ የጀርመን አሠሪዎች ለዓመታት ሲያሰሙ ለቆዩት አቤቱታ መልስ የሚሰጥ መስሏል። ረቂቁ ሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለተባባሰው የሰለጠኑ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሞያተኞችን፣ መሀንዲሶችን እና የጤና ባለሞያዎችን ጨምሮ በተለያዩ የሥራ መስኮች የሚፈለጉ የቴክኒክ ሠራተኞችን እጥረትን ለማቃለል ይረዳል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል። የጀርመን ጥምር መንግሥት አካል የሆነው የወግ አጥባቂው የጀርመን ክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲ የክብር ሊቀመንበር እና የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኽርስት ዜሆፈር ባለፈው ሳምንት ረቂቁን ለጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ሲያቀርቡ ሕጉ ሀገሪቱ ታሪካዊ ወቅት ላይ መድረሷን ያሳያል ብለዋል። ማን ጀርመን መጥቶ መሥራት እንደሚችል ለዚህም አስፈላጊዎቹን መስፈርቶች በግልጽ ያስቀመጠ ነውም ሲሉ አስረድተዋል። 
«በዚህ ሕግ ኤኮኖሚያችን በአጣዳፊ የሚፈልጋቸው የሰለጠኑ ባለሞያዎች የሚፈለግባቸውን አሟልተው ቁጥጥር እና ስርዓት ባለው መንገድ ወደ እኛ መምጣት የሚያስችላቸውን ሁኔታ አስቀምጠናል። እኔ እንደማስበው ይህ ከብዙ አሥርት ዓመታት በኋላ የጀርመን ሪፐብሊክ የደረሰበት ታሪካዊ ወቅት ነው። 
በአዲሱ ረቂቅ ሕግ ማሻሻያ ከተደረገባቸው ቁልፍ ጉዳዮች መካከል የስራ ማመልከቻ አቀባበል አንዱ ነው። ከዚህ ሌላ አዲሱ ህግ፣ ምሁራን ላይ ከሚያተኩረው የቀደመ ህግ በተለየ፣ በተለየየ የሥራ መስኮች የሰለጠኑ የቴክኒክ ሞያተኞችም በቀላሉ ጀርመን መግባት እንዲችሉ ያደርጋልም ተብሏል። ይህ ብቻ አይደለም በጀርመን የቴክኒክ ሞያ ስልጠና መውሰድ ለሚፈልጉ ሰዎችም ከተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎች ጋር ስልጠና ሊፈቀድላቸው እንደሚችልም ተገልጿል። ጀርመን የሚኖሩ የሚሰሩት የሕግ ባለሞያ እና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ አዲሱ ረቂቅ የፍልሰት ሕግ ቁልፍ የሚባሉ ለውጦች የተደረጉበት መሆኑን ይናገራሉ። ከዓላማው በመነሳት፣ በጀርመን የሰው ኃይል እጥረት ባለበት ሞያ ለመስራት ከተለያየ የዓለም ክፍል ለሚመጡ ሰዎች የተቀመጡት ዋና ዋና መስፈርቶች ይዘረዝራሉ ።ይሁንና ሕጉ በአንዳንድ የተለዩ ሁኔታዎች ገደቦችን ማስቀመጡም አልቀረም። ከዚህ ሌላ የጀርመን መንግሥት በተለይ እውቅና ላልተሰጣቸው ነገር ግን እዚህ ጀርመን የቋንቋ ትምህርት እና የሞያ ስልጠና የወሰዱ ተገን ጠያቂዎችን የሚመለከት የተሻሻለ ሌላ ረቂቅ ሕግም ለምክር ቤቱ አቅርቧል። 
ሁለቱም ረቂቅ ሕጎች በጀርመን ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሙሉ ማለት ይቻላል መተቸቱ አልቀረም። ተቃዋሚው የነጻ ዴሞክራቶች ፓርቲ «ያን ያህል አጓጓ እና ብዙም ለውጥ የተደረገበት አይደለም ብሏል። የውጭ ዜጎች ጀርመን በብዛት መግባታቸውን የሚቃወመው አማራጭ ለጀርመን የተባለው ቀኝ ጽንፈና ፓርቲ ደግሞ ሕጉ የሚፈለጉትን ባለሞያዎች ሳይሆን የሚፈለገው ስልጠና የሌላቸውን በድህነት ምክንያት የሚሰደዱ ሰዎችን ብቻ የሚስብ ነው ሲል አጣጥሎታል።  አዲሱ ረቂቅ ህግ ባለፈው ሳምንት ለጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በቀረበበት ወቅት በምክር ቤቱ የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ አባላት ሰብሳቢ ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ሥራ ፈላጊዎች ጀርመን ውስጥ ለግማሽ ዓመት ያህል ሥራ ሳይጀምሩ እንዲቆዩ መደረጉን ተቃውመዋል። 
«አንድ ተፈላጊ ሞያተኛ ሥራ ከመያዙ ከ6 ወር በፊት ጀርመን መምጣት ይችላል። ከመጣ በኋላ ግን በዚህ ግማሽ ዓመት ሥራ እንዲጀምር አይፈቀድለትም። ይህን ማን ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል።የትኛው ሥራ ፈላጊ የውጭ ዜጋ ነው ይህን ያህል ጊዜ ሊያቆየው የሚችል ብዙ ገንዘብ ይዞ የሚመጣው።»
በቀደመው ህግ የሰለጠነ ሙያተኛ የሚፈለግበት የሥራ ዘርፍ ከውጭ ለሚመጡ ተወዳዳሪዎች ክፍት የሚሆነው ጀርመናዊ ወይም የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገር ዜጋ ለክፍት የሥራ ቦታው አለማመልከቱ ከተረጋገጠ በኋላ መሆኑ መቅረቱ፣ ከሦስተኛው ዓለም ለሚመጡ ሥራ ፈላጊዎች እድሉን ያሰፋል ተብሎ ይገመታል። አዲሱ ረቂቅ የፍልሰት ኢትዮጵያን ጨምሮ በሦስተኛው ዓለም ለሚገኙ ሥራ ፈላጊዎች ትርጉም እንዳለውም ዶክተር ለማ ገልጸዋል። 
ምንም እንኳን ረቂቅ ሕጉ ጀርመን መሥራት ለሚፈልጉ የሰለጠኑ ባለሞያዎች የተሻለ እድል ይሰጣል ቢባልም ከቀደመው ልምድ በመነሳት ሂደቱ በቢሮክራሲው ውጣ ውረድ ምክንያት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል የሚገምቱ አሉ። ይሁን እና እንደ ዶክተር ለማ በአዲሱ ህግ ይህን የሚያቀላጥፉ አሰራሮች ታቅደዋል።
የጀርመን መንግሥት የባለሞያዎች እጥረት ባለባቸው የሥራ መስኮች የውጭ ዜጎችን አስገብቶ ለማሰራት እስካሁን ያወጣቸው የተለያዩ ሕጎች ልዩ ልዩ ገደቦችን በማስቀመጣቸው ውጤታማ መሆን አለመቻላቸው ይነገራል። ከአሜሪካን ከካናዳ እና ከመሳሰሉት የፍልሰት ሕጎች ጋር ሲነጻጸር የጀርመኑ ሕግ ጥብቅ የሚሆንበት ምክንያት ምን ይሆን? ዶክተር ለማ የዚህ ምክንያቱ የስነ ልቦና ዝግጅት አለመኖር ነው ይላሉ። በርሳቸው አስተያየት በጀርመን እንደ አሜሪካ እና እንደ ካናዳ የውጭ ዜጎችን ተቀብሎ ተዋህዶ አብሮ ለመኖር የህብረተሰቡ ስነ ልቦና አሁንም ዝግጁ አይመስላቸውም። የፍልሰት ጉዳይ ባለሞያዎች እንደሚሉት ጀርመን አሁን በተለያዩ ዘርፎች የሰለጠኑ ባለሞያዎችን በአጣዳፊ ትፈልጋለች። በዚህ የተነሳም አዲሱ ሕግ ከሚቀጥለው ዓመት ጥር አንስቶ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ሕጉ ተግባራዊ እስኪሆን ሊወስድ የሚችለውን የቢሮክራሲ ውጣ ወረድ በማሰብም የ6 ወራት የዝግጅት ጊዜ ተይዟል። በዚህ መሠረትም የሀገሪቱ ምክር ቤት ሕጉን በመጪው የበጋ ወራት ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። 

Arbeitende Migranten in Deutschland
ምስል picture-alliance/dpa/M. Skolimowska
Arbeitende Migranten in Deutschland
ምስል picture-alliance/dpa/C. Schmidt
Einwanderungsgesetz Bundestagsdebatte Horst Seehofer
ምስል picture-alliance/dpa/R. Hirschberger

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ