1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር

ማክሰኞ፣ የካቲት 7 2009

ሽታይንማየርን በቅርብ የሚያውቋቸው «የተናገሩትን የሚያደርጉ ፤የተግባር ሰው በእርግጠኝነነት የሚንቀሳቀሱ» ይሏቸዋል ። አሁን ለደረሱበት የፖለቲካ ደረጃ እና ላገኙት እውቅና መሠረት የሆኑት ጌርሃርድ ሽሮደር ደግሞ ሽታይንማየርን ለአሰቸጋሪ ግንኙነቶች የሚያስፈልጉ ሰው ብለዋቸዋል ።

https://p.dw.com/p/2XYlq
Berlin Wahl des Bundespräsidenten Antrittsrede Steinmeier
ምስል picture-alliance/dpa/B. von Jutrczenka

አዲሱ የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር

ጀርመን ከሁለት ቀናት በፊት አዲስ ፕሬዝዳንት መርጣለች ። የቀድሞ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር እንደተጠበቀው አዲሱ የጀርመን ፕሬዝዳንት በመሆን ተመርጠዋል 
ባለፈው እሁድ 12 ተኛ የጀርመን ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት  ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ባለፉት 20 ዓመታት በጀርመን መንግሥት ውስጥ በከፍተኛ የሥልጣን ማዕረጎች ያገለገሉ ሶሻል ዴሞክራት ፖለቲከኛ ናቸው ። ጀርመንን ተጣምረው የሚመሩት የእህትማማቾቹ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት በምህጻሩ CDU እና የክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲ CSU እንዲሁም የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ሽታይንማየርን የጋራ እጩ አድርገው በማቅረባቸው በእሁዱ ምርጫ በአብላጫ ድምጽ ማሸነፋቸው አጠራጣሪ አልነበረም ። ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለማካሄድ ከተሰየመው 1260 አባላት ካሉት ጉባኤ ሽታይንማየር የ931 ዱን ማለትም (73.9 %).ድምፅ አግኝተው ነው የተመረጡት ። የ77 ዓመቱን ተሰናባቹን የጀርመን ፕሬዝዳንት ዮአሒም ጋውክን የሚተኩት የ61 ዓመቱ ሽታይንማየር በጀርመን  ከረዥም ጊዜ አንስቶ እውቅና ያተረፉ ፖለቲከኛ ናቸው ። ይበልጡን የሚታወቁት በቀድሞው የጀርመን መራሄ መንግሥት ጌርሀርድ ሽሮደር ዘመነ መንግሥት በ2003 ዓምህረቱ የኤኮኖሚ ተሀድሶ እና የማህበራዊ ድጎማ ቅነሳ ውስጥ በነበራቸው ከፍተኛ ሚና ነው ። በህግ የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ሽታይንማየር ፣ ሽሮደር ፣ የኒደርዛክሰን ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት በጎርጎሮሳዊው በ1990 ዎቹ የቅርብ ረዳታቸው ነበሩ ። ሽሮደር በ1998  የመራሄ መንግሥቱን ሥልጣን ሲይዙም የሽታይንማየር  የፖለቲካ ሥልጣን አደገ ። የደህንነት አገልግሎት ጉዳዮች ሚኒስትር ዴታ ሆኑ ። ከ1999 እስከ 2005 ደግሞ የመራሄ መንግሥቱ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ነበሩ። በጀርመን ለመጀመሪያ ጊዜ በተቋቋመው ትልቁ ጥምር መንግሥት  ከ2005 እስከ 2009 ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል ። ከ2007 ዓም አንስቶ ምክትል መራሄ መንግሥትም ነበሩ ። በ2008 ዓም ለጥቂት ጊዜ የፓርቲያቸው ተጠባባቂ ሊቀመንበር ሆነው ካገለገሉ በኋላ በ2009 ዓም በተካሄደው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ፓርቲያቸውን ወክለው ለመራሄ መንግሥትነት በእጩነት ቢቀርቡም ፓርቲያቸው በመሸነፉ በፓርላማው የተቃዋሚ ፓርቲያቸው መሪነትን ተረከቡ ። ከ2013 ቱ ምርጫ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ በተመሠረተው ታላቁ ጥምር መንግሥት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኑ ። በህዳር 2016 ለጀርመን ፕሬዝዳንትነት የታጩት ሽታይንማየር  እስከ ጎርጎሮሳዊው ጥር 2017 በዚሁ ሃላፊነት ሰርተዋል ። ሽታይንማየር በቅርብ የሚያውቋቸው የተናገሩትን የሚያደርጉ የተግባር ሰው በእርግጠኝነነት የሚንቀሳቀሱ ይሏቸዋል ።ሽታይንማየር አሁን ለደረሱበት የፖለቲካ ደረጃ እና ላገኙት እውቅና መሠረት የሆኑት ጌርሃርድ ሽሮደር ሽታይንማየርን  ለአሰቸጋሪ  ግንኙነቶች  የሚያስፈልጉ ሰው ብለዋቸዋል ።
« እርሳቸው (ሽታይንማየር )የጀርመን መርህ በተለይ ከአሜሪካ ጋር ባለው ከባድ ግንኙነት ላይ ጠንካራ እና የዳበረ በራስ የመተማመን ይዘት እንዲኖረው ግፊት ያደርጋሉ ብዮ አስባለሁ ። አዲሱ የአሜሪካን ፕሬዝዳንት እንደሚናገሩት የተስፋ መመናመን ብቻ ሳይሆን በእርሳቸው አንጻር የሚኖረን መርህ በራስ መተማመን ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት ። ይህን ለማድረግ ደግሞ የፌደራዊ ሪፐብሊክዋ ፕሬዝዳንት ብዙ እገዛ ያደርጋል ። እሳቸው(ሽታይንማየር) ይህን ያደርጋሉ ብዬ አስባለሁ ። »
የፊታችን መጋቢት የፕሬዝዳንትነቱን ሃላፊነት የሚረከቡት ሽታይንማየር ከርሳቸው ከቀደሙት ከዮአሂም ጋውክ ጋር ሲነፃጸሩ ለፖለቲካው አዲስ አይደሉም ። ታዋቂው ፖለቲከኛ ሽታይንማየር ለተመረጡበት ሃላፊነት አስፈላጊ የሆኑ መስፈርቶችን ያሟላሉ ። በመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ሁለት የሥልጣን ዘመኖች የጥምር መንግሥቱ አባል የሆኑት የሁለቱ ትላልቅ ፓርቲዎች እኩል ከበሬታ ይሰጧቸዋል ። በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ባካበቱት ዲፕሎማሲያዊ ልምድ አድናቆት ይቸራቸዋል ።በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ቀውሶችን ለመፍታት ባደረጓቸው ጥረቶች ችሎታቸውን አስመስክረዋል ። በምዕራብ ጀርመኑ የኖርድ ራይን ቬስትፋለን ፌደራዊ ክፍለ ሀገር በምትገኘው ዴትሞልድ የተወለዱት የሽታይንማየር  አባት አናጺ ነበሩ ። እናታቸው ደግሞ ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት በኋላ ከፖላንድ ጀርመን የመጡ ስደተኛ ናቸው ። ሽታይንማየር የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርትታቸውን እንደጨረሱ ለሁለት ዓመታት የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ሰጥተዋል ። በጊሰን ዩኒቨርስቲ ህግ እና የፖለቲካ ሳይንስ ያጠኑት ሽታይንማየር በህግ የዶክትሬት ዲግሪ እስካገኙበት እስከ 1991 በተማሩበት በጊሰን ዩኒቨርስቲ  የህግና የፖለቲካ ሳይንስ ረዳት መምህር ነበሩ ።  በህዝብ አስተያየት መመዘኛዎችም ሽታይንማየር ለዓመታት ከተወዳጅ የጀርመን ፖለቲከኞች አንዱ ሆነው ነው የዘለቁት ። የጀርመን ፕሬዝዳንት ርዕሰ ብሔር ቢሆንም የመወሰን ፖለቲካዊ ሥልጣን እና ተግባራቱ የተገደቡ ናቸው ። ይህ የሆነውም ከናዚ ጀርመን ልምድ በመነሳት የጀርመን ፕሬዝዳንት ሁሉንም ሥልጣን ጠቅሎ እንዳይዝ ለማድረግ ነው ታስቦ ነው ። የጀርመን ህዝብ ፕሬዝዳንቱን የሚመርጠው በውክልና ዴሞክራሲ ሳይሆን ለዚሁ ተግባር በሚሰየም ልዩ ጉባኤ አማካይነት ነው ። ጉባኤው ለጀርመን ፕሬዝዳንት ምርጫ ብቻ የሚሰየም ሲሆን የሚያካትተውም የጀርመን ፓርላማ አባላትን በሙሉ እንዲሁም የ16 ቱ የጀርመን ፌደራል ክፍለ ግዛቶች መርጠው የሚልኳቸውን ተወካዮች ነው ። የእያንዳንዱ ፌደራል ክፍለ ግዛት ተወካዮች ቁጥር የሚወሰነውም በህዝባቸው ብዛት ነው ። ተወክለው የሚላኩትም ፖለቲከኞች ብቻ መሆን የለባቸውም ። አንዳንዴ ታዋቂ  ወይም ህዝብ የሚያከብራቸው ሰዎችም ሊወከሉ ይችላሉ ።ተፎካካሪዎቹም  የምርጫ ዘመቻ አያካሂዱም ። ምርጫው በምስጢር ድምጽ አሰጣጥ የሚከናወን ሲሆን እጩዎቹ ፍፁም የበላይነት ካላገኙ ሁለተኛ ሦስተኛ ዙር ምርጫ ይካሄዳል ።በጀርመን ፓርላማ ፕሬዝዳንት ሊቀመንበርነት የሚመራው የፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ጉባኤ ምርጫው ተካሂዶ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ተቀባይነት ሲያገኝ ይበተናል ። የጀርመን ፕሬዝዳንት የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ቢሆንም የመወሰን ፖለቲካዊ ሥልጣኑ ግን የተገደበ ነው ። ይሁን እና የሀገሪቱ የስነ ምግባር እና የፖለቲካ ስርዓቷ ምልክት ነው ።  ጀርመንን በተለይ በውጭው ዓለም ይወክላል ። በሀገር ውስጥም ህዝቡን አንድ የማድረግ ሃላፊነት አለበት ። ሽታይንማየር  ባለፈው እሁድ በአብላጫ ድምጽ ከተመረጡ በኋላ ባሰሙት ንግግር ለህዝቡ «እንድፈር ሌሎችን እናበረታታ ወደፊት ሊሆን የሚችለውን አንፍራ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል ። ዓለም አስቸጋሪ ወቅት ላይ እንደምትገኝ የጠቆሙት ሽታይንማየር፣ ጀርመን በዚህ ጊዜ የብዙዎች የተስፋ መልህቅ ሆና መገኘትዋ የሚደነቅ ነው ብለዋል  ። ጀርመንን ለዚህ ያበቃትም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ብዙ ሊባሉ የሚችሉ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻልዋ መሆኑንንም በንግግራቸው ገልጸዋል ። 
 «ሌሎችን የምናደፋፍረው  በሀገራችን ሁሉም ነገር ጥሩ ስለሆነ አይደለም ። ይልቁንም እኛ የተሻለ ጊዜ ሊመጣ እንደሚችል ስላሳየን እንጂ ። ከጦርነት በኋላ ሰላም ማስፈን እንደሚቻል ፣ ከመከፋፈል  በኋላ እርቀ ሰላም እንደሚወርድ፣ ከርዕዮተ ዓለም ልዩነቶች በኋላ አስተዋይ ፖለቲካ ሊመጣ እንደሚችል አሳይተናል ። በዚህ ረገድ በሀገራችን ብዙ ነገሮች ብዙ አሳክተናል ። »
ዲፕሎማቱ ሽታይንማየር በመላው ዓለም በተለይም በአውሮጳ እየተጠናከሩ የመጠትን ብሔረተኛ እና ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲዎች በእጅጉ ይኮንናሉ ። ሽታይንማየር ባለፈው ነሐሴ በሰጡት አስተያየት «ህዝብን በማስፈራራት ፖለቲካ ላይ የተመሰረተ» ሲሉ የፖለቲካ አካሄዳቸውን ከተቹት መካከል «አማራጭ ለጀርመን » የተባለው የጀርመኑ ብሔረተኛ ፓርቲ ፣ ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት እንድትወጣ ይቀሰቅሱ የነበሩ ወገኖች እንዲሁም «ጥላቻ ሰባኪ» ያሏቸው ያኔ የምርጫ ዘመቻ ላይ የነበሩት  ዶናልድ ትራምፕ ይገኙበታል ።ሽታይንማየር ባለፈው እሁድ ባሰሙት ንግግር እውነትን ከሀሰት ለይቶ የመናገር ድፍረት ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ማዳመጥ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል ።   
«ዛሬ ዓለማችንን በተለይም አውሮጳን ስንመለከት ጊዜው አስቸጋሪ መሆኑን እናያለን ። ይሁን እና ክቡራት እና ክቡራን ጊዜው የኛ ነው ። ሃላፊነቱን ተሸክመናል ። ሌሎችን ማደፋፈር ከፈለግን እኛም ራሳችን ደፋር ልንሆን ይገባል ።  ትክክለኛ እና ትክክለኛ ያልሆነውን ለይቶ የመናገር ድፍረቱ ሊኖረን ይገባል ። እውነቱን ከሀሰት ለይተን መናገር ይኖርብናል ። ሌሎችን የማዳመጥ ብርታት ያስፈልገናል ። በሌሎች ላይ የኛ ፍላጎቶች ላለመጫን መዘጋጀት አለብን ። »
ለዘብተኛ እና ለውጥ ፈላጊ ከሚባሉ ሶሻል ዴሞክራቶች አንዱ ሽታይንማየር የሚተቹባቸው ጉዳዮችም አይጠፉም ። ከመካከላቸው እርሳቸው ዋነኛ ተዋናይ የነበሩትበት አጀንዳ 2010 የተባለው አወዛጋቢው የሽሮደር የማህበራዊ ድጎማዎች ተሀድሶ ይገኝበታል ። ከዚህ ሌላ በሩስያ እና በቻይና ላይ የሚያራምዱት ለዘብተኛ አቋም ፣እንዲሁም ከሰብዓዊ መብቶች ይልቅ የጀርመንን የንግድ ጥቅሞች በማስቀደም ይወቀሳሉ  ። ባለትዳርና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ሽታይንማየር ከዓመታት በፊት ለተወሰኑ ወራት ከፖለቲካው ዓለም ራቅ ብለው ነበር ። በዚህ ጊዜም በኩላሊት ህመም ይሰቃዩ ለነበሩት እና ምትክ ኩላሊት ያስፈልጋቸው ለነበረው ለባለቤታቸው ለዳኛ ቡዌደንቤንደር ሽታይንማየር ከኩላሊታቸው አንዱን ለግሰዋል ። ይህም በህዝብ ዘንድ ያላቸውን ከበሪታ እና ተቀባይነት እንዲጨምር አድርጎላቸዋል ። ሽታይናማየር የፕሬዝዳንትነቱን ሥራ ሲጀምሩ ቀዳማዊት እመቤት ቡዌደንቤንደር ሽታይንማየር የጥቅም ግጭትን ለማስቀረት የዳኝነቱን ሥራ እንደሚያቆሙ ተነግሯል ። በሁለቱ የጀርመን ትላልቅ ፓርቲዎች ታጭተው በፕሬዝዳንትትነት የተመረጡት ሽታይንማየር በሥልጣና ዘመናቸው የሀገሪቱ አረጋጊ መልህቅ ይሆናሉ የሚል ተስፋ  ተጥሎባቸዋል ።
ኂሩት መለሰ

Deutschland | Wahl des Bundespräsidenten | Gottesdienst St. Hedwigs-Kathedrale | Ankunft Steinmeier
ምስል picture-alliance/dpa/K. Nietfeld
Deutschland Kabinettsumbildung Gauck mit Merkel und Steinmeier
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. SOhn
Bundespräsidendentenwahl Merkel gratuliert Frank-Walter Steinmeier
ምስል Getty Images/AFP/O. Andersen
Berlin Wahl des Bundespräsidenten Steinmeier Applaus
ምስል Reuters/H. Hanschke

አርያም ተክሌ