1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የግሪክ እቅድ

እሑድ፣ ሰኔ 14 2007

የግሪክ መንግሥት ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ለመንግሥት ሰራተኞችና ለጡረተኞች ሙሉ ክፍያን መስጠት እንደማይችል ተገለፀ። ይህንን የዘገበው የጀርመኑ «ፍራንክፈርተር አልገማይነ» የተሰኘው ጋዜጣ በዛሬዉ እትሙ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ዓለማ አቀፍ አበዳሪዎች ገንዘባቸዉን ስለሚፈልጉ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1FkVz
Griechenland und Russland unterschreiben Pipeline-Deal
ምስል Reuters/M. Shemetov

የግሪክ አበዳሪዎች እንዳሰሉት ከሆነ ግሪክ በወሩ መጨረሻ ከ 2 እስከ 3,6 ቢሊዮን ዩሮ ገንዘብ ይጎድላታል። ከዚህም በተጨማሪ ከግብር የምታሰባስበው ገንዘብ በከፍተኛ መጠን ቀንሷል። የግሪክ መንግሥት ያለበትን 1,6 ቢሊዮን ዩሮ እዳ ለዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም መክፈል አቅቶታል። የግሪኩ ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሲስ ሲፕራስ ግሪክ ያለባትን የገንዘብ እዳ በተመለከተ ነገ ለሚካሄደዉ ልዩ ጉባኤ ካቢኒያቸው ዛሬ ጠዋት ሲመክር ቆይቷል። ኋላም ሲፕራስ መፍትሄ ያሉትን ሀሳብ ለጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል፣ ለፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ኦሎንድ እና የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ኃላፊ ዦን ክሎድ ዩንከር በስልክ መግለፃቸውን የግሪክ መንግሥት ባወጣው ዘገባ ገልጿል። የሲፕራስ የመፍትሄ ሀሳብ ይዘት ግን በዘገባው አልተካተተም።

የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ግሪክ ያለባትን የገንዘብ እዳ በተመለከተ በሚካሄደዉ ልዩ ጉባኤ ላይ ጥሩ መልስን አገኛለሁ ብላ ከፍተኛ ጉጉት ይዛ እንዳትቀርብ ማስጠንቀቃጨዉ ይታወቃል። የፊታችን ሰኞ የሚካሄደዉ ጉባኤ ወሳኝ ሊሆን የሚችለዉ፤ ግሪክ ለዉሳኔዉ መሠረታዊ መረጃዎችዋን ይዛ ስትቀርብ ብቻ መሆኑን ሜርክል ተናግረዋል። ይኸዉም የግሪክ ተሃድሶ መረሃ-ግብር በሶስቱ ተቋማት ማለትም፤ በዓለም የገንዘብ ተቋም፤ በአዉሮጳ ማዕከላዊ ባንክና በአዉሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ተቀባይነት ያለዉ መልስን ሲያገኝ ብቻ መሆኑ ተመልክቶአል። ግሪክ እስከ ያዝነዉ ወር መጨረሻ ከአለባት እዳ 1,5 ቢሊዮን ዩሮ ለዓለሙ የገንዘብ ተቋም መክፈል ይኖርባታል። ዓለም አቀፍ ገንዘብ አበዳሪዎች ካልተስማሙ ግን የአቴንሱ መንግሥት ምንም ዓይነት የገንዘብ ርዳታን እንደማያገኝ ተገልፆአል። ግሪክ ከአበዳሪዎች 7,2 ቢሊዮን ይሮን ለማግኘት በቀጣይ የኤኮኖሚ ታህድሶዋን እና የቁጠባ እቅድ መረሃ -ግብሯን በተለይ ደግሞ የቫት ክፍያን እንድታሳድግ እንዲሁም የጡረታ ክፍያ መጠንን እንድትቀንስ ይጠበቅባታል። እስካሁን ግን የግሪኩ የአሌክሲስ ሲፕራስ መንግስት በዚህ እቅድ ላይ መስማማት አልፈለገም።

Symbolbild Griechenland EU Ausblick Gipfel
ምስል Getty Images/AFP/A. Messinis

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ