1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲስ አበባ፥ እነ ፌስቡክ በኢትዮጵያ ተዘጉ

እሑድ፣ ሐምሌ 3 2008

ኢትዮጵያ ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ለሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ዘጋች። ርምጃው የተወሰደው ባለፈው ወር የብሔራዊ የመልቀቂያ ፈተና ከነመልሶቻቸው በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መሰራጨቱን ተከትሎ ከተከሰተው እሰጣ አገባ በኋላ ነው።

https://p.dw.com/p/1JMeI
Symbolbild Facebook Klarnamenpflicht Pseudonyme Anonymität
ምስል picture-alliance/dpa/F. Gabbert

የመንግስት ኮምዩንኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳ ፌስቡክን መሰል ማሕበራዊ ድረ-ገጾች የታገዱት በዚህ ሳምንት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ሐሳባቸው እንዳይበታተን ለመታደግ ታስቦ ነው ሲሉ መናገራቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። ከዕለተ-ቅዳሜ ጨምሮ ፌስቡክ፤ ትዊተር፤ ኢንስታግራም እና ቫይበርን የመሳሰሉ ማሕበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች አገልግሎት አይሰጡም። አቶ ጌታቸው ረዳም መዘጋታቸውን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ በኢንተርኔት ላይ ሳንሱር በማድረግ ከአፍሪቃ አገሮች ቀዳሚዋ ናት ሲሉ ተንታኞች ይናገራሉ። ጦማሪ ዳንዔል ብርሐነ ርምጃውን «አደገኛ» ብሎታል። ዳንዔል «ለምን እንደሚዘጋ እና ለምን ያክል ጊዜ እንደሚዘጋ ማን እንደሚወስን ግልጽ አይደለም» ሲል ያክላል። «አሁን ለጥቂት ቀናት ነው። በሚቀጥለው ለወራት ሊሆን ይችላል» ሲል ስጋቱን ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት የገለጠው ጦማሪ ዳንዔል ብርሀነ «ጡንቻቸውን እየሞከሩ ነው። በርካታ ቁሳቁሶች አሏቸው። እነሱን እየሞከሩ ነው» ብሏል። ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ካውንስል የኢንተርኔት አገልግሎትን ማገድ ወይም ማቋረጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው ሲል ውሳኔ አስተላልፏል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ