1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲስ ካቢኔ፤ ኢሬቻ፤ ፌስቡክ፤ ተ.መ.ድ. እና ኢትዮጵያ 

ዓርብ፣ መስከረም 28 2014

ከበዓለ ሲመት እስከ አዲስ መንግሥት ምስረታ፤ ከኢሬቻ በዓል የመንግሥት ተቃውሞ እስከ ተቃዋሚዎች በካቢኔው መግባት ተካቶበታል። የፌስቡክ አጭር መቋረጥ እና የፀጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መወያየቱም የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ቅኝት የሳምንቱ ዐበይት መነጋገሪያዎች ነበሩ።

https://p.dw.com/p/41Ps1
USA | UN-Sicherheitsrat zu Äthiopien
ምስል Loey Felipe/UN Photo/Xinhua/picture alliance

የማኅበራዊ መገናና አውታሮች ቅኝት

በሳምንቱ በርካታ ጉዳዮች የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ቅኝት ዐበይት መነጋገሪያ ሆነው ቆይተዋል። ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰባት ሠራተኞችን ከሀገር ማባረሯ በተገለጠ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ የፀጥታው ምክር ቤት ዳግም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተነጋግሯል። በኢትዮጵያ አዲስ መንግሥት ምስረታ ዋዜማ በኢሬቻ በዓል ላይ መንግሥትን የሚቃወሙ ድምፆች ተሰምተዋል። የኢፌዴሪ ስድስተኛው ምክር ቤት መክፈቻ እና የጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ በዓለ ሲመትም የሳምንቱ መነጋገሪያ ነበር። በዋናው ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲተላለፍ የነበረው የበዓለ ሲመቱ የቀጥታ የፌስቡክ ስርጭት መጠለፉ፤ ቆየት ብሎም ፌስቡክ፤ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ በመላው ዓለም ለግማሽ ቀን ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸው አወያይቷል። የኢትዮጵያ አዲሱ ካቢኔ ሦስት የተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችን በሚንሥትር ማዕረግ ማካተቱም ትኩረት ስቧል። እነዚሁ ጉዳዮችን በሚመለከት በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ የተሰጡ 

የፀጥታው ምክር ቤት

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ባባረረቻቸው 7 የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች ጉዳይ ላይ ባሳለፍነው ረቡዕ አስቸኳይ ስብሰባ አድርጓል። ተመድ በኢትዮጵያ ጉዳይ  ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሲሰበሰብ ለሁለተኛ ግዜ መሆኑ ነው።  የተመድ ሠራተኞች ከሀገር እንዲባረሩ መወሰኑ የተሰማው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነበር። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፦ «የተባረሩት የዓለም አቀፉ ድርጅቶች ሠራተኞች የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የሚጥስ እና ለብሔራዊ ደህንነት ስጋት የሚሆኑ ድርጊቶችን ፈጽመው በመገኘታቸው ነው» ሲል  ከሷል።  አበባየሁ አበበ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በትዊተር ገጻቸው ላይ፦ «ኢትዮጵያ ሉአላዊት እና ነፃ ሀገር መሆንዋን እንዳትዘነጉ» ሲሉ ጽፈዋል። 

የፀጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ለመምከር አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱን በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚች ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ብለውታል። ዳኛቸው በየነ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በምክር ቤቱ ፊት የተናገሩትን አጭር የቪዲዮ ምስል አያይዘው ቀጣዩን ጽፈዋል። «ሀገራት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞችን እና የሀገራት ዲፕሎማቶችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከሀገራቸው በታወቀም ሆነ ወይም ግልጽ ባልሆን ምክንያት ማስወጣታቸውን ዕናውቃለን» ሲል ይነበባል ጽሑፉ። «ሆኖም ግን» ሲል ይቀጥላል። «ሆኖም ተመድ እንዲህ ያለ ውሳኔን ለማጠየቅ ስብሰባ አድርጎ ያውቅ ይሆንን?» ሲሉም አምባሳደሩ በእንግሊዥኛ ካሰሙት ንግግር የተቀነጨበው ትርጉም ሰፍሯል። «ዲፌንድ ኢትዮጵያን ስፔን» የበተባለ የትዊተር ስም ደግሞ ቀጣዩ መልእክት ይነበባል። «በኢትዮጵያ መንግሥት ከአገር እንዲወጡ የታዘዙት ሰባቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ከአገር ወጥተዋል» ሲል።  መልእክቱ የሚጠናቀቀው «ሕግ ለሁሉም ይሰራል» በሚል ነው። 

USA | UN-Sicherheitsrat zu Äthiopien
ምስል Loey Felipe/UN Photo/Xinhua/picture alliance

የፀጥታው ምክር ቤት በአንድ ሳምንት ጊዜ ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ጉዳይ ለመምከር ቢሰበሰብም በአባላቱ ዘንድ ግን የተለያዩ አቋሞች ተንጸባርቀዋል። ዩናይትድ ስቴትስ የፀጥታው ምክር ቤት ርምጃ እንዲወስድ ወትውታለች። ሩስያ እና ቻይና በዋናነት ጉዳዩ በፀጥታው ምክር ቤት መታየቱን አልደገፉትም። ሁለቱም በኢትዮጵ ለተመሰረተው አዲስ መንግሥት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።  ቻይና ከርምጃ ይልቅ ያልተጩዋጩኸ ሰከን ያለ ዲፕሎማሲያዊ ንግግር እንዲደረግ መክራለች። የሩስያ ተወካይም፦ «የሆነውን ነገር ብዙ ባናጩጩኸው ስንል ጥሪ እናቀርባለን» ብለዋል። 

በስብሰባው ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴን ጥያቄ ጠይቀዋቸዋል። ኢትዮጵያ የመንግሥታቱን ድርጅት ሠራተኞች ላባረረችበት ክስ ማስረጃ ታቅርብም ብለዋል ዋና ጸሐፊው።
የአሜሪካ ድምፅ የተባበሩት መንግሥታት ዘጋቢ ማርጋሬት በሺር በዋና ጸሐፊው ድርጊት በመደመም ቀጣዩን ትዊተር ላይ ጽፋለች። «በፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ቀጥታ ምላሽ ሲሰጡ ያየሁበት አንድም ትዝ የሚለኝ ጊዜ የለም» ስትል። «አንቶኒዮ ጉተሬሽ የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴን በመጠየቅ ግን አድርገውታል። ኢትዮጵያ የተመድ ሠራተኞችን የማባረር መብት የላትም፤ ተመድ ይኼን የዓለም አቀፍ ጥሰት ነው ብሎ ያምናል በማለት» ተናግረዋል። 

ዋና ጸሐፊው ከስብሰባው ሲወጡ ከአንዲት ጋዜጠኛ ጥያቄ ቀርቦላቸውም ነበር። «እስከማስታውሰው ድረስ በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ መልስ ሲሰጡ አንድም ጊዜ ታይተው ዐያውቁም ነበር። ይኼ የሚያሳየው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ መንግሥት ደስተኛ ያለመሆኖትን መጠን ይሆን?» በሚል ነበር ጥያቄው የቀረበላቸው። ዋና ጸሐፊው ቆጣ ባለ ገጽታ የሰጡት አጠር ያለ መልስ እንዲህ የሚል ነበር ። «የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ክብርን ማስጠበቅ ግዴታዬ ነው።» ጉራጌ ፈርስት የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ የዋና ጸሐፊው የቪዲዮ መልእክትን በማያያዝ፦ የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ በአጠቃላይ በድርጅቱ ቻርተር ላይ እንደሰፈረው «ለሰብአዊነት፣ ለእውነት፣ ለፍትህ፣ ለገለልተኝነት፣ ከወገንተኝነት ውጪ መሆን እና በውብ ቃላት እንደሰፈሩት ሌሎች ግቦች ሳይሆን የድርጅቱን ክብር ማስጠበቅ ነበር ለካ» ሲሉ ተችተዋል። ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ እንዲሁም ሩስያ፤ ቻይና እና ሌሎች ሃገራት የተናገሩትን በርካቶች በማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተነጋግረውበታል። 

Äthiopien Gobe ​​and Shinoye in Addis Abeba
ምስል Seyoum Getu/DW

ኢሬቻ ተቃውሞ
የኢሬቻ በዓል ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚከበርበት ወቅት የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ወጣቶች መንግስትን በመቃወም ድምጻቸውን አሰምተዋል። ወጣቶቹ ሲያሰሟቸው በነበሩ መፈክሮች ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድን በስም ጠርተው አውግዘዋል። ወጣቶቹ የድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተቀሰቀሰው ዐመጽ ተጠርጥረው በእስር ላይ ለሚገኙት አቶ ጀዋር መሐመድ ያላቸውን ድጋፍ መግለጻቸውን አሶሽየትድ ፕረስ ዘግቧል። አቶ ጀዋር መሐመድ እና ሌሎች ባልደረቦቻቸው በኢትዮጵያ መንግስት በሽብርተኝነት ተከሰዋል። ነገር ግን አክቲቪስቶች የፖለቲከኛው መታሰር ፖለቲካዊ ተልዕኮ እንዳለው ነው የሚገልጹት።

የኢሬቻ በዓል በተከበረበት ቀን የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ድረ-ገጽ ተባባሪ መሥራች እና ዋና አርታኢ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ አዲስ አበባ ውስጥ ሜክሲኮ በሚባለው ሰፈር በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ በቁጥጥር ስር ውሎ እንደነበር የተነገረው በማኅበራዊ የመገናኛ አውታር ነው። ተስፋለም የታሰሩ ፖለቲከኞች እንዲለቀቁ የሚጠይቁ እና የጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ አህመድን አስተዳደር የሚቃወሙ ድምፆችን ያካተቱ የኢሬቻ በዓልን የተመለከቱ ዘገባዎችን ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር ከሠራ በኋላም ነበር በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ የተሰማው፤ ሆኖም በዚሁ ሳምንት ማክሰኞ ዕለት መለቀቁን ዶይቼ ቬለ ዘግቧል። 

በኢሬቻ በዓል ወቅት የተሰማውን ተቃውሞ በተመለከተ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል፦ ደጀኔ ረጋሳ ፌስቡክ ገጽ ላይ «አገር ተወጥራ እያለ እንደዚ መሆን ምን ማለት ነው ሌላ ችግር አለ?» ሲሉ ጠይቀዋል።  ሐዊ ፈንታሌ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ደግሞ በኢሬቻ በዓል ላይ ተቃውሞ ይኖራል ተብሎ ማንም ጠብቆ እንዳልነበር ጽፈዋል። «ቄሮ ሁሉንም ድንገት አስደምሟል» ሲሉ በእንግሊዝኛ ጽሑፋቸው አክለዋል።ሞሐመድ መካ፦ ፌስቡክ ላይ፦ «ስንቱን ጉደኛ ነው የተሸከምሽው ሀገሬ» ሲሉ በአጭሩ ጽፈዋል። 

Störung | WhatsApp, Facebook und Instagram
ምስል Ozge Elif Kizil/AA/picture alliance

ሌላው በሳምንቱ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎችን ያስደመመ ምናልባትም ለሰአታት ዘወትር ከለመዱት የዕለት ተዕለት ተግባራቻው ያገደ ክስተትም ድንገት ተፈጥሯል። በመጀመሪያ የሆነው እንዲህ ነው። የጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ በዓለ ሲመት ከመስቀል አደባባይ በቀጥታ በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያው በሚሰራጭበት ወቅት ስርጭቱን የሚያስተላልፈው የፌስቡክ ገጽ መጠለፉ ይነገራል። እናም ከበዓለ ሲመቱ ጋር የማይገናኙ መልእክቶች በጠላፊዎቹ ከተላለፉ በኋላ የተለጠፉት መልእክቶች ይነሳሉ። በዕለቱ ብዙም ሳይቆይ የፌስቡክ እና የፌስቡክ ንብረት የሆኑት ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ መተግበሪያዎች በመላው ዓለም ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸው ዐቢይ የዜና ርእስ ሆኖ ቆይቷል። ይኸው የሁለቱ ክስተቶች በተቀራራቢ ሰዓት መፈጠር በርካቶች ከቀልድ እስከምር የተለያዩ መላ ምቶችን እንዲሰነዝሩ አድርጓል።  

ሙክታሮቪች ኦስማኖቫ በትዊተር ገጹ፦ «ፌስቡክ የመንግስት ምስረታው መሳካት አበሳጭቶት ኔትወርኩን ዘጋው እንዴ» ሲል ከሳቅ ምልክት ጋር መልእክቱን አስፍሯል። ይህንኑ መልእክት ወደ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ሰዎች መውደዳቸውን በላይክ አረጋግጠዋል። «አጋጣሚ ይሁን ባላቅም በዕለቱ ፌስ ቡክ ለ6 ሰዓታት በዓለም አቀፍ ደረጃ አገልግሎት ተቋርጦ እንደነበር አሳውቋል» ሲሉ የጻፉት ደግሞ ደጀን አብተው ናቸው እዛው ትዊተር ላይ። 

በፌስቡክ ለጊዜው መቋረጥ እነ ትዊተርን የመሳሰሉ ታላላቅ የመገናኛ አውታሮች አጋጣሚውን በመጠቀም በስላቅ አጫጭር መልእክታቸውን አስፍረዋል። የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች እነ ፌስቡክን ከትዊተር ጋር እያነጻጸሩ በጽሑፍም በምስልም ያቀረቧቸው መልእክቶች አዝናንም ነበሩ። ለአብነት ያህል አንዱ ምስል ላይ፦ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ የሚል ጽሑፍ ያለበት ሰው ከአናቱ እስከ እግር ጥፍሩ በፋሻ ተጀቡኖ ይታያል። ከአጠገቡ ኮሜዲያን ሚስቴር ቤን ትዊተር የሚል ጽሑፍ ከፊት ለፊቱ እንደተደረገበት እግሩን እያነባበረ እና እያወረደ በፋሻ የተጠቀለለው ሰው ላይ ሲስቅ ይታያል።  ይህን የቪዲዮ መልእክት በበርካቶች ዘንድ በስላቅ መልክ ተንሸራሽሯል። ትዊተር ብቻውን መሥራቱን ለማወደስ። 

በዓለም ዙርያ ለሚገኙ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች የፌስቡክ ግልጋሎት ለስድስት ሰዓታት የመቋረጡ ምክንያትን ፌስቡክ «መረጃዎችን ለማስተላለፍ እንደገና የተዋቀረበት መንገድ ስህተት ስለነበረዉ» እንደሆነ ራሱ ገልጧል። 

በሳምንቱ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች መነጋገሪያ ከሆኑ ሌሎች ጉዳዮች መካከል በኢትዮጵያ አዲሱ ካቢኔ ውስጥ የሦስት የተለያዩ የተቀዋሚ ፓርቲዎች አመራር መካተታቸውም ነበር። በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ አስተያየቶች ተንሸራሽረዋል። ሚፍታህ ረሺድ፦ «አካታች ሆኖ ሁሉም በየኔነት እንዲቀበለው ከማድረግ አንፃር ገና ብዙ የሚቀረው ነው» ሲሉ፤ «ኢትዮጵያ የፈለገችውን መሪ አግኝታለች» ያሉት ደግሞ ይሄይስ ፍስሐ ናቸው ፌስቡክ ላይ። መስፍን ተክሉ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፦ «አገሬ ምን ዓይነት አሰተማሪ መሪ እንዳገኝች ያየሁበት ቀን ነው ምንም ማደረግ አይቻልም ኢትዮጵያ ታሸንፋለች» ብለዋል። የተሰጡት አስተያየቶች በርካታ ናቸው። 

Der neue Ministerrat von Äthiopien
ምስል House of people’s representative of Ethiopia

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ