1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲስ የልማት እርዳታ መረሃ-ግብር

ዓርብ፣ ሐምሌ 1 2003

በኢትዮጵያ እና በጀርመን መንግስት መካከል የተካሄደዉ አዲስ የልማት ትብብር መረሃ-ግብር ድርድር ይበልጡን የትምህርቱን ዘርፋ ማስፋፋት ላይ ለማዋል በመስማማት መጠቃለሉን የጀርመን ኤኮኖሚ ተራድኦ ሚኒስቴር BMZ ይፋ አደረገ።

https://p.dw.com/p/RYhY

በስምምነቱ መሠረትም በቀጣይ ለሶስት ዓመታት ጀርመን ለኢትዮጵያ ከምትሰጠዉ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ዩሮ ዉስጥ አብዛኛዉ ለትምህርት ዘርፍ እንደሚዉል ተገልጿል። ጀርመን ስለምታቀርበዉ የልማት እርዳታ በሁለቱ መንግስታት መካከል የተደረሱትን ስምምነቶች በማስመልከት የዶቸ ቬለዉ ሉድገር ሻዶምስኪ በምስራቅ አፍሪቃ የጀርመን የልማት እድገት ትብብር ሚኒስቴር ተጠሪን አነጋግሯል። አዜብ ታደሰ ታቀርበዋለች።
ጀርመን አዲስ በነደፈችዉ የአፍሪቃ ልማት መረሃ-ግብር አኳያ በቀጣይ ለኢትዮጽያ የልማት እርዳታ ለመስጠት ሁለቱ መንግስታት ከሰኔ 21 እስ 23 እዚህ ቦን ከተማ ድርድር አካሂደዋል። በድርድሩም ኢትዮጵያ ከጀርመን የምታገኘዉ የልማት ትብብር እርዳታዉ በዋነኛነት ለትምህርት ማስፋፊያ መዋል ይኖርበታል በሚለዉ ሃሳብ በመስማማት ተጠቃልዋል። ጀርመን ለሚቀጥሉት ሶስት አመታት ለኢትዮጽያ 102 ሚሊዮን ይሮ የምትሰጥ ሲሆን ከዚህ ዉስጥ ለትምህርት ዘርፉ 38 ሚሊዮን ይሮ ተመድቧል። በምስራቅ አፍሪቃ የጀርመን የልማት እድገት ትብብር ሚኒስቴር ተጠሪ ቶማስ አልበርት አገራቸዉ የምትሰጠዉ የልማት ርዳታ አጠቃቀምን በሚመለከት አዲስ ፖሊስ መቀየሷን አመልክተዋል።

«በተስማማነዉ መሰረት ይህ የተመደበዉ ገንዘብ እንዳልነዉ በትምህርት ማስፋፋት ላይ የማይዉል ከሆነ እኛም አብረን መስራታችንን እናቆማለን። በቀጣይ መፍትሄ እስካልመጣ እና እንደገና አዲስ ድርድር ከኢትዮጽያ መንግስት ጋር እስከሚደረግ። መፍትሄ ካላገኘን የምንሰጠዉን የልማት እርዳታ እናቋርጣለን። ለልማት እርዳታዉ የታሰበዉ ገንዘብ በታቀደዉ አመት እና ግዜ ወጭ ካልሆነ ደግሞ በመቀጠል ሊሰጥ የታሰበዉን በጀት ዝቅ ያደርገዋል። እናም በዚህ አዲስ መንገድ ብቻ ልንሰራ እንደምንችል ለኢትዮጵያ መንግስትም ግልጽ አድርገናል።»
ኢትዮጽያ መንግስት ከዩክሬን በአንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር ሁለት መቶ ታንክን ለመግዛት ማቀዱ፤ እንዲሁም በቅርቡ እንደ ኢትዮጽያ መንግስት ገለጻ ከራሱ ኪስ አልያም በቦንድ ሽያጭ ሊሰራ አቅጃለሁ ያለዉ የአባይ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ በድርድሩ ወቅት ርእስ አልነበረምን? ቶማስ አልበርት፤
«በርግጥ በድርድሩ ወቅት ነገሩ እንደ ርእስ ባይነሳም በሃሳባችን ነበር። በዚህም ምክንያት የጀርመን የልማት ትብብር ሚኒስትሩ በአገሪቷ በሁሉም ረገድ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች እንዲከበር፣ አነጋጋሪዉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በሚመለከት የወጣዉ ህግ፣ እንዲሁም የመሬት መቀራመት ጉዳይ ጥንቃቄ እንዲወሰድበት አበክረዉ ተናግረዋል። »
እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር 2010 ዓ.ም መጨረሻ ሂዉማን ራይትስ ዎች በዘገባዉ የኢሃዴግ መንግስት ለአገሪቷ የሚሰጠዉን የልማት ትብብር ገንዘብ ለስልጣን ማቆያ እያዋለዉ ነዉ ሲል ማዉጣቱ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ የጀርመን አጣሪ ኮሚሽን በቦታዉ ተገኝቶ በልማት ትብብሩ ረገድ የተሰራዉን ፈትሾ የራሱን ዘገባ አጠናቅሮ ተመልሶአል። ይህ ለወደፊቱ በልማት እርዳታ ትብብር ተግባር ምን ያህል ይጠቅማል ለሚለዉ ሲመልሱ፤

Dirk Niebel Pressekonferenz Potsdam
የጀርመኑ የልማት ትብብር ሚኒስትር ዲርክ ኔብልምስል picture alliance/dpa

«የታሰበዉ ነገር በቦታዉ ላይ ሳይዉል ለፖለቲካ ጉዳይ መጠቀምያ መሆኑ ከታወቀ እና የኢትዮጵያ በጀት ግልጽ ካልሆነ እኛ አብረን መስራት አንችልም። እናም እናመሰግናለን የራሳችሁን ጉዳይ እራሳችሁ ጨርሱ እንላቸዋለን።»
የጀርመኑ የልማት ትብብር ሚኒስትር ዲርክ ኔብል ኢትዮጽያን ጎብኝተዉ ከተመለሱ በኋላ ባደረጉት ንግግር ለኢትዮጽያ የሚሰጥ ቀጥተኛ የበጀት እርዳታ አይኖርም ብለዋል?
«ኢትዮጽያ ለዚህ ጉዳይ የተመቻቸ ሁኔታ ይኖራል ብለን ስለማንገምት ከጀርመን በኩል የበጀት እገዛ ይሰጣል የሚል ግምት የለንም።»
በቅርቡ በአገሪቷ በወጣዉ የፀረ-ሽብርተኝነት ህግ ሰበብ ለምሳሌ በኦጋዴን አካባቢ ከፑንት ላንድ የመጡ ሁለት የስዊድን ጋዜጠኞች ተይዘዋል ምናልባት በጸረ አሸባሪነት ክስ ሳይመሰረትባቸዉ አይቀርም። ሌላዉ ከአልሻባብ፣ አልቃይዳ ጋር ኦብነግ ኦነግ ከአሸባሪነት ተፈረጀዋል። ከቅርብ ወራቶች ወዲህ በርካታ ሰዎች እየታሰሩ ነዉ። ታድያ በአገሪቷ የሚታየዉ ይህ ሁሉ ዉጥረት ምናልባት በአገሪቷ ላይ ሌላ ነገር ሊቀሰቅስ አይችልም ብለዉ ያምናሉ?
«የኢትዮጽያ መንግስት ይህንን ሁሉ ነገር በአንድ ክዳን አፍኖ መያዝ እንዳልቻለ ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን እያየን ነዉ፥ እኛም በልማት ትብብሩ ለምንሠራዉ ተግባር እንቆማለን።»
ሌላዉ ለዉጭ ባለንዋዮች የአርሻ መሬት መሰጠቱ ቀጥሏል። ይገነባል የተባለዉ የህክምና ጣብያና ትምህርት ቤቶች አልተሰሩም። እጅግ አነስተኛ የሆነዉ የደምወዝ ክፍያን ማንሳቱ እዚህ ላይ ብዙም አስፈላጊ አይመስልም። ታድያ ከዚህ ሁሉ ችግር ጋር ከአኢትዮጽያ ጋር የትብብር ወዳጅነት ለመቀጠል ትዕግስቱ ይኖራል? ቶማስ አልበርት፤
«የሰብአዊ መብት ጉዳይ በሚመለከት በአገሪቷ ያለዉ ሁኔታ እንዴት ነዉ? መንግስት ለህዝብ ምን አይነት አመለካከት አለዉ። ይሄን መንግስትስ መርዳት እንችላለን? ለምን ያህል ግዜ? ሙሉ በሙሉ ግልጽነት የተላበሰ አሰራርን እንጠብቃለን፤ እንዲሁም እንደ አጋር አገር ያልነዉ ሊሰማልን ሊከበርልን ይገባል። ከመንግስት ጋር ልንነጋገርበት የምንችልበት መድረክም ሊፈጠር ይገባል። ለልማት የምንሰጠዉ ገንዘብ የህዝባችን በመሆኑ ምን ላይ እንዳዋልነዉ ለምንጠየቀዉ ጥያቄ የሚገባ መልስን መመለስ እንዲያስችለን።»
ዶቼ ቬለ የአማረኛዉ ስርጭት አገልግሎት በኢትዮጽያ እና አካባቢዋ እንዳይደመጥ መንግስት እያፈነዉ መሆኑን አሳዉቀናል። በድርድሩ ወቅት ይህ ርእስ ተነስቶ ነበርን?
«የልማት ትብብር ሚኒስሩ በተቀዳሚነት ያስቀመጡት ርእስ ነበር፣ በግልጽም ይህ አሰራራችሁ ትክክል ባለመሆኑ ልታስተካክሉት ይገባል ብለዋል።»

አዜብ ታደሰ


ሸዋዪ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ