1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲስ የዓማፂ ቡድን በደቡብ ሱዳን

ቅዳሜ፣ መጋቢት 2 2009

በደቡብ ሱዳን ከአንድ ወር በፊት ስልጣናቸውን የለቀቁት  ሊየተና ጀነራል ቶማስ ሲሪሎ ስዋካ ከአንድ ሳምንት በፊት እጎአ ባለፈው ሰኞ መጋቢት ስድስት፣ 2017 ዓም በፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር በሚመራው መንግሥት አንፃር የሚታገል «ናሽናል ሳልቬሽን ፍሮንት»፣ በምህፃሩ «ኤን ኤ ኤስ»  የተባለ አንድ ቡድን አቋቁመዋል።

https://p.dw.com/p/2YzJB
Südsudan Kämpfer
ምስል picture alliance/AP Photo/J. Lynch

Fokus Afrika A (11.03.2017) - MP3-Stereo

ስዋካ ፀረ መንግሥቱን ቡድን ያቋቋሙት ደቡብ ሱዳን ሁሉን የህብረተሰቡን ክፍል የሚያሳትፍ ውይይት በጀመረችበት ጊዜ መሆኑ ሂደቶችን  ይበልጡን እንደሚያወሳስብ ታዛቢዎች አመልክተዋል።  አጠቃላዩ ውይይት እጎአ ነሀሴ 2015 ዓም የተፈረመውን የሰላም ስምምነት በተግባር መተርጎም የሚቻልበትን ሁኔታ የማመቻቸት ዓላማ ይዞ ነው የተነሳው።

በዚህም የተነሳ የደቡብ ሱዳን መንግሥት በአንፃሩ የሚታገል አዲስ የዓማፅያን ቡድን ያቋቋሙትን ሊየተና ጀነራል ቶማስ ሲሪሎ ስዋካ  የኃይሉን ተግባር እንዲተዉ እና ለሀገሪቱ ችግሮች በውይይት መፍትሄ እንዲያፈላልጉ ጥሪ ማቅረቡን የሀገሪቱ  ማስታወቂያ ሚንስትር ማይክል ማክዌይ አስታቀዋል።
« ስዋካ የጀመሩትን ዓመፅ ካላቆሙ እና ብሔራዊን ውይይት ካልተቀላቀሉ  በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለብን እናያለን። ያሰቡትን ተግባራዊ ለማድረግ እስከየት ድረስ ርቀው እንደሚሄዱ እናያለን።  »    
ኤን ኤስ ኤ» በሀገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት ሊያወርድ እንደሚችል ባለ ሙሉ ተስፋ መሆናቸውን የገለጹት ስዋካ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ተጨማሪ ደም ሳይፈስ ስልጣናቸውን ቢለቁ መልካም እንደሚሆን ተናግረዋል። በሀገሪቱ ብሄራዊ ጦር ዉስጥ  የጠቅላላ የሎጅስቲክ  ምክትል ዋና አዛዥ የነበሩት ሊየተና ጀነራል ሲሪሎ ስዋካ  ፀረ መንግሥት ቡድናቸው ሳልቫ ኪር እስኪወርዱ ድረስ እንደሚታገል በማስታወቅ ፣ የደቡብ ሱዳን ሕዝብ በዚሁ ትግል እንዲሳተፍ ጠይቀዋል።  ሲሪሎ ስዋካ ያቋቋሙት ያማፅያን ቡድን ለመንግሥቱ አንዳችም ስጋት እንደማይደቅን ማክዌይ ገልጸዋል።
« ይህ ተንቀሳቃሽ  እንቅስቃሴ ነው። ትክክለኛ መሪ ከሆንክ ሕዝብ ወደ ስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች እንዲሄድ በፍፁም አትቀሰቅስም። ለምሳሌ እኔ መሪ ብሆን ጫካ  ገብቼ ነው የምታገለው። ሕዝቤም ወደጫካ በመምጣት አብሮኝ እንዲታገል ነው ጥሪ የማደርግለት። ለምንድን ነው በስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች እንዲቀላቀለሁ ትጠይቃለህ፣ ባንተ ስር ሳይሆን በተመድ ስር ነው ያሉት። እና በስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች  ያለውን ሕዝብ ለትግላቸው ለማግኘት አስበው ከሆነ ፣ ይህ በፍፁም አይሆንም እላለሁ።»
የኢኳቶርያል ግዛት  ከጥቂት ወራት በፊት ከጦር ኃይሉ ጥቃት እስከተሰነዘረበት ጊዜ ድረስ ሰላማዊ አካባቢ ሆኖ ነበር የቆየው። በመላ ሀገሪቱ የተከበሩ የነበሩት ከፍተኛው የጦር መኮንን ስልጣን መልቀቅ ለፕሬዚደንት ኪር መንግሥት እና ለጦር ኃይሉ እንደ ትልቅ ውርደት ታይቷል። ከኢኳቶርያል ግዛት የሚወለዱት ስዋካ የአንድ ጎሳ የበላይነት ፖሊሲ ይከተላሉ ያሉዋቸው ፕሬዚደንት ኪር እና በብዛት የኪር የዲንካ ጎሳ አባላት የተጠቃለሉበት ጦር ኃይል በሀገሪቱ የጎሳ ማጽዳት  እና የሀገሪቱን ንብረት የመዝረፍ ዘመቻ እያካሄዱ ነው በሚል ወቅሰዋል።  የተመድ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ተመልካች ኮሚሽን ከጥቂት ጊዜ በፊት ያወጣው ዘገባም በደቡብ ሱዳን የዘር ማጽዳት ዘመቻ እየተካሄደ እንደሆነ እና ሀገሪቱ ወደ ጎሳ ጭፍጨፋው አፋፍ ላይ እንደምትገኝ፣ ሲቭሉን ሕዝብ ሆን ብሎ የማስራብ እና በቦምብ የመደብደብ ተግባር እንደሚፈፀምም አመልክቶ ነበር። የደቡብ ሱዳን መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናትም ጥላቻ የሚያስፋፋ ንግግር እንደሚያሰሙም በተጨማሪ መግለጹ አይዘነጋም። ይሁን እንጂ፣ በጎሳ ጭፍጨፋ አፋፍ ላይ ትገኛለች በሚል ኮሚሽኑ ያወጣውን  ዘገባ በተመለከተ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉተረሽ  ሰሞኑን በናይሮቢ ኬንያ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ  ሲመልሱ ስጋቱ በወቅቱ በጉልህ እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል። 
«ገዜልሻፍት ፊውር በድሪተ ፈልከር» በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ለውሁዳን ቤሔሮች መብት የሚሟገተው የጀርመናውያኑ ድርጅት ኃላፊ ኡልሪኽ ዴልዩስ ሀገሪቱ በጎሳ ግጭት አፋፍ ላይ ትገኛለች የተባለበትን ስጋት  ጉተረሽ ቀንሷል ያሉበትን አነጋገራቸውን ችግሩን አሳንሶ ማየት ነው በሚል ወቅሰዋል።  እንደ ዴልዩስ አስተሳሰብ፣ የተመድ ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ በወቅቱ በደቡብ ሱዳን የሚፋለሙት ወገኖች  የሰብዓዊ መብት የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው ግልጽ በማድረጉ እና የረሀብ አደጋ ላሰጋው የሀገሪቱ ሕዝብም አስቸኳዩ የምግብ ርዳታ የሚቀርብበትን ሁኔታ በማመቻቸቱ ተግባር ላይ ሊያተኩር ይገባል። የተመድ እንዳስታወቀው፣ ደቡብ ሱዳን አሳሳቢ የረሀብ አደጋ ስጋት ተደቅኖባታል።   አስቸኳይ ርዳታ ካልቀረበ ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጋ የሀገሪቱ ሕዝብ የምግብ እጥረት ያጋጥመዋል።  ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ የቀጠለው ውዝግብ ህዝቡን ችግር ላይ እንደጣለው የርዳታ ስራ የሚያከናውeነው የዓለም የምግብ ድርጅት «ዳብል ዩ ኤፍ ፒ» ቃል አቀባይ ጆርጅ ፎሚንየን ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል።
« ውዝግቡ እጎአ ከ2013 ዓም ወዲህ ቀጥሏል። ይህ ውዝግብ ሕዝቡን ከመኖሪያ ቀየው አፈናቅሏል። አርሰው ምርት እንዳያመርቱ አድርጓቸዋል፣ ከብቶቻቸውን አሳጥቷቸዋል። ገንዘብ የላቸውም፣ ባካባቢያቸውም ገበያ የለም። ከዚህ በተጨማሪም፣ በውጊያ ሰበብ የሰብዓዊ ርዳታ ወዳካባቢያቸው መግባት አይችልም። እና አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። በዚህ አሁን ባለንባቸው ባንዳንድ የቀድሞው የዩኒቲ ግዛት አካባቢዎች ከከፋ ረሀብ እና ጠኔ ጋር የሚመሳል ሁኔታ ይታያል። »   

Antonio Guterres in Kenia
ምስል Reuters/T.Mukoya
Äthiopien Addis Abeba Salva Kiir Mayardit und  Hailemariam Desalegn
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker

ሊየተና ጀነራል ቶማስ ሲሪሎ ስዋካ ባለፈው የካቲት ሰባት፣ 2017 ዓም ስልጣናቸውን ከለቀቁ ከአንድ ወር በኋላ የደቡብ ሱዳን የስራ ሚንስትር የነበሩት ጋብርየል ዱዎፕ ላም የፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ወነኛ ተቀናቃኝ ለሆኑት በስደት በደቡብ አፍሪቃ ለሚገኙት የቀድሞው የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዚደንት ሪየክ ማቸር ታማኝነታቸውን በመግለጽ ስራቸውን ለቀዋል። የደቡብ ሱዳን የጦር ፍርድ ቤቶችን ስራ የበመሪነት ያስተዳድሩ የነበሩ ሁለት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ብርጋዲየር ጀነራል ሄንሪ ኦያይ እና ኮሎኔል ካሊድ ኦኖ ሎኪም መንግሥት በስራቸው ላይ ባደረገው ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት ሰበብ ሴቶችን በመድፈር እና ሲብሎችን በመግደል አብዝተው የሚወቀሱትን ወታደሮች ስነ ስርዓት ለማስያዝ አለመቻላቸውን በማስታወቅ ከስራቸው ተሰናብተዋል።  

አርያም ተክሌ

እሸቴ በቀለ