1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

አዲስ ፕሬዝዳንት አሮጌ ችግሮች በኢራን

ሰኞ፣ ነሐሴ 3 2013

የዋጋ ንረት፣ የውኃ እጥረት፣ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ የሚፈትናት ኢራን አዲስ ፕሬዝደንት ባለፈው ሳምንት ሥልጣን ተረክበዋል።ለበርካታ አሮጌ ችግሮች መፍትሔ የማፈላለግ ኃላፊነት የተጣለባቸው ፕሬዝደንት ኢብራሒም ራይሲ ምዕራቡን ዓለም በጥርጣሬ የሚመለከቱ ወግ አጥባቂ ናቸው። በኢራን የኑክሌር መርሐ ግብር ላይ የሚደረገው ድርድር ሌላው የቤት ሥራቸው ነው

https://p.dw.com/p/3ykpU
Iran Präsident Ebrahim Reisi
ምስል ATTA KENARE/AFP/Getty Images

ማሕደረ ዜና፦ አዲስ ፕሬዝዳንት አሮጌ ችግሮች በኢራን

ኢራን ከምዕራባውያኑ አዲስ ውዝግብ ውስጥ ገብታለች። ከኦማን አቅራቢያ ከሁለት ሣምንታት በፊት ከታንዛኒያ ወደ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በመጓዝ ላይ የነበረ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሳቢያ ተከታታይ ክሶች እና ውግዘቶችም ቀርቦባታል። አሜሪካ፣ እስራኤል እና ብሪታኒያ ለጥቃቱ ተሒራንን ለመክሰስ ቀዳሚ ነበሩ። ከዚያ የቡድን ሰባት አባል አገራት ተከተሉ። የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የቡድን ሰባት አባል አገራት ያቀረቡትን ውንጀላ መሠረተ ቢስ በማለት አጣጥለዋል። ይኸ ግን ክስ እና ወቀሳውን አላቆመውም። ትናንት እሁድ "ሁሉም ማስረጃዎች በግልጽ ወደ ኢራን ይጠቁማሉ" ያሉት የአውሮፓ ኅብረት የዉጪ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል ጥቃቱን በማውገዝ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግቡን ተቀላቅለዋል።

አዲሱ ትኩሳት

የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ ሜርሰር ስትሪት በተባለው ግዙፍ መርከብ ላይ ጥቃት የተፈጸመበት ሰው አልባ የአየር ላይ ተሽከርካሪ (UAV) በኢራን የተመረተ ነው ከሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱን ባለፈው ቅዳሜ ይፋ አድርጓል። መርማሪዎች መርከቡ በሶስት ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት ደርሶበታል የሚል እምነት አላቸው። በዚህ ጥቃት ሁለት የመርከቡ የጥበቃ ጓዶች ተገድለዋል።ጉዳዩን ውስብስብ ያደረገው መርከቡን ለሥራ ያሰማራው ዞዲያክ ሜሪታይም የተባለ ኩባንያ ኢያል ኦፈር የተባሉ እስራኤላዊ ቢሊየነር ንብረት መሆኑ ነው።

Schiffstanker I M/T Mercer Street
የላይቤሪያ ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልበው ሜርሰር ስትሪት የተባለ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ከታንዛኒያ ወደ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በመጓዝ ላይ ሳለ የተፈጸመበት ጥቃት ኢራንን ከምዕራባውያን ለአዲስ ውዝግብ ዳርጓልምስል Johan Victor/AP/picture alliance

በኢራን ላይ ያነጣጠረው ትኩስ ውዝግብ የተቀሰቀሰው ባለፈው ሐሙስ አዲሱ ፕሬዝደንት ኢብራሒም ራይሲ በአገሪቱ ምክር ቤት ቃለ-መሐላ ፈጽመው ገና ሥልጣን ከመረከባቸው ነው። የ60 አመቱ ራይሲ ከኢራን አብዮት ወዲህ ስድስተኛው ፕሬዝደንት ናቸው። በዓለ ሲመታቸው የተፈጸመው የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አሊ ኻሚኒ ለፕሬዝዳንትነታቸው ቡራኬ ከሰጡ ከሁለት ቀናት በኋላ ነበር። ሓሳን ሩሐኒን ተክተው አገሪቱን ለመምራት በተወዳደሩበት የወርሀ ሰኔው ምርጫ ይኸ ነው የሚባል ተገዳዳሪ አልገጠማቸውም። ኢብራሒም ራይሲ ምዕራቡን ዓለም በጥርጣሬ የሚመለከቱ ወግ አጥባቂ ናቸው።

አዲሱ ፕሬዝደንት ኢብራሒም ራይሲ ምን አሉ?

አዲሱ ፕሬዝደንት የሚመሩት የኢራን መንግሥት ትኩሱን ውዝግብ ጨምሮ በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፉ መድረክ የሚጋፈጣቸው ዘርፈ-ብዙ ችግሮች አሉ። ኢራን የውኃ እጥረት፣ ተደጋጋሚ የኃይል መቋረጥ እና የዋጋ ንረት የሚፈትናት አገር ናት። በአሜሪካ የተጣለባት ማዕቀብ ኤኮኖሚዋን እጅ ተወርች ጠፍሮታል።

ፕሬዝደንት ኢብራሒም ራይሲ "ኢራን ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች መነሳት አለባቸው። ይኸን ግብ የሚያሳኩ ማናቸውም ዲፕሎማሲያዊ ዕቅዶችን እንደግፋለን" ሲሉ ተናግረዋል።

ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ለታጣቂ ቡድኖች ታደርገዋለች የሚባለው ድጋፍ እና ከሶርያ መንግሥት ጋር ያላት ግንኙነት በቀጠናው አወዛጋቢ አድርጓት ቆይቷል። ሳዑዲ አረቢያን ከመሳሰሉ የቀጠናው ኃያላን እና ከእስራኤል ጋር ያላት ግንኙነት ከመሻከር ተሻግሮ መቃቃር የበረታበት ነው። አሜሪካን ጨምሮ በርካታ አገሮች በቀጠናው ላለው ውጥረት ጣታቸውን በኢራን ላይ ይቀስራሉ። ራይሲ በበዓለ ሲመታቸው ያሉት ግን በተለይ ምዕራባውያን አገራቸውን ከሚከሱበት እጅጉን የራቀ ነው።

ኢብራሒም ራይሲ "እኛ የሰብዓዊ መብት እውነተኛ ጠበቆች ነን። በጭቆና፣ በወንጀል እና በመብት ረገጣ ፊት ዝምታን አንቀበልም። በአውሮፓ ልብ፣ በአሜሪካ፣ በየመን፣ በሶርያ እና በፍልስጤም ወንጀል እና ጭቆና ሲኖር ከተበደሉ ጎን እንቆማለን" ሲሉ ተደምጠዋል።

Iran | Parlament | Vereidigung Ebrahim Raisi
ፕሬዝደንት ኢብራሒም ራይሲ ወግ አጥባቂው አያቶላ አሊ ኻሚኒ ከጎርጎሮሳዊው 1981 እስከ 1989 የያዙትን ሥልጣን በመረከብ የኢራን መንፈሳዊ መሪን ፈለግ እየተከተሉ ነውምስል Farsnews

ኢራን ቀውስ ውስጥ በገባችው የመን የሑቲ አማፅያንን ትደግፋለች የሚል ብርቱ ክስ ላለፉት አመታት ሳይለያት ቆይቷል። ከሊባኖሱ ሒዝቦላሕ ጋር ያላት ግንኙነትም በምዕራባውያንም ይሁን በቀጠናው አገራት አይወደድላትም። ራይሲ በምክር ቤቱ ባሰሙት ንግግራቸው "የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ኃይል በቀጠናው ጸጥታን ያሰፍናል። ኢራን በቀጣናው ያላት አቅም ሰላም እና መረጋጋትን በተለያዩ አገሮች ይደግፋል። ኃይላችንን የምንጠቀመው ግን ሥጋቶችን ለመጋፈጥ እና ጨቋኝ ኃይሎችን ለመመከት ብቻ ነው" እያሉ የአገራቸውን ወታደራዊ ኃይል አወድሰዋል።

በራይሲ በዓለ ሲመት በቁጥር በርከት ያሉ ዲፕሎማቶች ታድመዋል። በበዓለ ሲመቱ ሳዑዲ አረቢያ እንድትታደም የኢራን ባለሥልጣናት ያቀረቡት ግብዣ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። ፕሬዝደንቱ በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ አገሮች ኢራን ግንኙነቷን ለማደስ ፍላጎት እንዳላት ጥቆማ ሰጥተዋል። "የወዳጅነት እና ወንድማማችነት ግብዣዬን በቀጣናው ለሚገኙ አገሮች ሁሉ በተለይም ለጎረቤቶቻችን እነሆ አቀርባለሁ" ያሉት አዲሱ ፕሬዝደንት ኢብራሒም ራይሲ  "ጠላቶች በቀጠናው የሚያደርጉት ጣል ገብነት የትኛውንም ችግር አይፈታም። እንዲያውም በራሱ ችግር ነው" ብለዋል።

በተሒራን ጎዳናዎች ምን ተባለ?

ፕሬዝደንቱ ቃለ መሐላ በፈጸሙበት ዕለት በተሒራን ጎዳናዎች በኢራን ዜጎች ዘንድ የተደበላለቀ ስሜት ይንጸባረቅ ነበር። ዋና የዜና አገልግሎት በተሒራን ጎዳናዎች ያነጋገራቸው የአገሪቱ ዜጎች ተስፋ እና ሥጋታቸውን ከመናገር አልተቆጠቡም። ከእነዚህ መካከል በመንገድ ላይ ንግድ የሚተዳደረው አሊ "እውነቱን ለመናገር ምንም ተስፋ የለኝም። ለውጥ ያመጣል የተባለው የቀድሞው መንግሥት ደጋፊ ነበርኩ። ሩሓኒ ፕሬዝደንት በነበሩባቸው ስምንት አመታት የሆነው ግን እነሱ የተስፋ ዕቅድ ያሉት እኛን ተስፋ አሳጣን። አሁንም ራይሲ በማዕቀቦች እና ኤኮኖሚያዊ ጫና በሕዝቡ ላይ የተፈጠረውን ችግር ለማቃለል አንዳች ነገር ማድረግ ስለመቻላቸው እጠራጠራለሁ" ብሏል።

እንዲህ ተስፋ የመቁረጥ ዝንባሌ የሚታየው ግን አሊን በመሳሰሉ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ዘንድ ብቻ አይደለም። ኢራናውያን የአገሪቱን ምጣኔ ሐብት ላዳሸቀው የምዕራባውያን ማዕቀብ ከራይሲ መንግሥት መፍትሔ ይሻሉ።

"የኤኮኖሚ ጫናው በተለይ ለእኛ ለወጣቶች እጅግ አስቸጋሪ ሆኗል። በተለይ ደግሞ እንደ እኔ በቅርብ ጊዜ ትዳር ለመሰረትን ሰዎች እጅግ ከፍቷል። የምግብ ወጪያችንን እንኳ መክፈል አልቻልንም" የምትለው ሌላ የተሒራን ነዋሪ "ከመንግሥት መጀመሪያ የምጠብቀው ይኸን ኤኮኖሚያዊ ጫና እንዲያቃልሉ ነው" በማለት የራይሲ የቤት ሥራ ያለችውን ጠቁማለች።

ኢራን ለዓለም ገበያ የምታቀርበውን የነዳጅ ምርት መጠን በመገደብ እና ከዓለም አቀፉ የባንክ አገልግሎት እንድትገለል በማድረግ የአሜሪካ ማዕቀብ ብርቱ ጫና አሳድሮባታል። አሜሪካ የጣለቻቸው ማዕቀቦች በሒደት እንዲነሱ የ60 አመቱ ጎልማሳ መንግሥታቸው የሚወስዳቸው እርምጃዎች እንደሚኖሩ ቃል ገብተዋል።

Iran Landflucht & Dürre
ኢራናውያንን ከሚፈትኑ በርካታ ችግሮች መካከል የውኃ እጥረት አንዱ ነውምስል Mehr

ራይሲ ዳኛ ሳሉ ፈጸሟቸው በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሳቢያ በአሜሪካ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል። ኢራናውያን ምዕራባውያኑ በአገራቸው ላይ በያዙት አቋም የተከፋፈለ ስሜት አላቸው። ራይሲ ከምዕራባውያኑ የተጣጣመ ፖለቲካዊ አቋም እንዲኖራቸው የሚሹ የመኖራቸውን ያክል ቆፍጠን ማለታቸውን የሚወዱም ጥቂት አይደሉም።

"በጠላት ፊት ቁርጠኝነት እጅግ ጠቃሚ ነገር ነው ብዬ አስባለሁ። ይኸ ደግሞ ፕሬዝዳንት ራይሲ አላቸው። አይንበረከኩም፤ ባለፉት ስምንት አመታት አገራችን የተቀማችው ኃይል ይመለሳል የሚል ተስፋ አለኝ" ሲሉ አንድ የተሒራን ነዋሪ በራይሲ እንደሚተማመኑ ገልጸዋል።   

ኢራን ባለፉት 50 አመታት ከገጠማት ሁሉ የከፋ ድርቅ ይፈትናታል። የውኃ እጥረት በርትቷል፤ የኤሌክትሪክ ኃይል በተደጋጋሚ ይቋረጣል። የኮሮና ቫይረስ በከፍተኛ ፍጥነት ከሚስፋፋባቸው አገሮች አንዷ ነች። ይኸ በኢራናውያን ላይ ብርቱ ጫና አሳድሯል። ራይሲ የፕሬዝደንትነት መንበረ ሥልጣኑን ሲጨብጡ "ዜጎቻችን ለሁሉም ጫናዎች መፍትሔ በማበጀት አኗኗራቸውን ማሻሻል ይፈልጋሉ። ዜጎቻችን ብሔራዊ ደስታ እና ማኅበራዊ መግባባት በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዲበለጽግ ይሻሉ" ብለዋል።

የኢራን የኑክሌር መርሐ ግብር እና ድርድር

የአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት ልዕለ ኃያላኑ በኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር ላይ ከተሒራን የተፈራረሙት ሥምምነት መልሶ ነፍስ እንዲዘራ በመጪው መስከረም እንደገና ውይይት ይጀመራል የሚል ተስፋ አላቸው። የሥምምነቱ ፈራሚ የሆኑት አሜሪካ፣ ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና፣ ሩሲያ እና ጀርመን እስካሁን ስድስት ጊዜ ከኢራን ተደራድረዋል። ከስድስት አመታት በፊት ተፈርሞ ገቢራዊ የሆነውን ውል የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸውን በማስወጣት ፋይዳ አሳጥተውታል። ኢራንም ምዕራባውያኑ ቃላቸውን ካላከበሩ ለውሉ ሙሉ በሙሉ እንደማትገዛ በማሳወቅ እየሸራረፈች የኑክሌር መርሐ-ግብሯን ማሳደግ ቀጥላለች።

Teheran, Iran | Ebrahim Raisi | Inauguration
የ60 አመቱ ኢብራሒም ራይሲ በዓለ ሲመታቸው የተፈጸመው የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አሊ ኻሚኒ ለፕሬዝዳንትነታቸውን ቡራኬ ከሰጡ ከሁለት ቀናት በኋላ ነበር።ምስል FARARU

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ባለፈው ሳምንት ራይሲ በይፋ ሥልጣን ሲጨብጡ "ለፕሬዝደንት ራይሲ የምናስተላልፈው መልዕክት ከእርሳቸው በፊት ለነበሩት ካስተላለፍንው ተመሳሳይ ነው። ይኸም ዩናይትድ ስቴትስ የራሷን እና የአጋሮቻችንን ብሔራዊ ጥቅሞች ታስጠብቃለች። ኢራን ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔዎችን ለማበጀት ከሁላችንም ፊት የሚገኙ ዕድሎችን ትጠቀማለች ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ይኸን ለማየት እየጠበቅን ነው። አዲሱ የኢራን መንግሥት የሚወስደውን አማራጭ ተመልክተን ከአጋሮቻችን በመመካከር በፊናችን መልስ እንሰጣለን" በማለት ተናግረዋል።

"በእኛ በኩል ድርድሩን ለመቀጠል ወደ ቪየና ለመመለስ ተዘጋጅተናል። ይኸን የምናደርገው በአንድ ቀላል ምክንያት ብቻ ነው። ይኸም ለፕሬዝደንት ራይሲ ወዳስተላለፍንው መልዕክት ይመልሰናል። ይኸን የምናደርገው የብሔራዊ ጸጥታ ጥቅማችን ስለሆነ ነው" ያሉት ቃል አቀባዩ ይሁንና አሜሪካ ኢራን ወደ ድርድሩ እስክትመለስ ለረዥም ጊዜ እንደማትጠብቅ አስረድተዋል።

እንደ ኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ  ሁሉ ራይሲ በአገራቸው የኑክሌር መርሐ ግብር ላይ ለሚደረገው ድርድር ይሁንታ ሰጥተዋል። ከዚህ ቀደም ከኢራን ለተፈረመው የኑክሌር መርሐ ግብር ውል ልዕለ ኃያላኑ መልሰው ነፍስ ሊዘሩበት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ