1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዳጊ ሐገራትና የሐዋላጥቅም

ረቡዕ፣ ኅዳር 19 2005

የሚሰጠዉን ወይም ለመስጠት ቃል የገባዉን የልማት ርዳታም አጥፏል ወይም ቀንሷል። የወለደ ግን አይጥልም።የተወለደም አይረሳም።እና ድርጅቱ እንደሚለዉ አሁን የአፍሪቃና የብጤዎቻቸዉ የገንዘብ ምንጭ፥ እኒያ ሲሆን በቦሌ፥ ካልሆነም በባሌ- ዩሮ፥ ዶላር፥ ሪያል-ዲናር ካለበት የደረሱት ተወላጆች ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/16sAA
The Ukrainian and American money is a background, © Aptyp_koK #14678971
ምስል Fotolia


የበለፀጉት ሐገራት እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ2008 በገንዘብ ቀዉስ ከተመቱ ወዲሕ ወደ ድሆቹ ሐገራት የሚፈሰዉ ዓለም አቀፍ ወረት (ኢንቨስትመንት) በግማሽ ቀንሷል።የበለፀጉት ሐገራት ለድሆቹ  ሐገራት የሚሰጡት የልማት ርዳትም አንድም ቀንሷል ወይም በነበረበት እንደቆመ ነዉ።የተባበሩት መንግሥት ድርጅት እስከ 2015 ከዓለማዉ እንዲደርስ ያቀደዉ የአመአቱ ግብም ከታለመለት የሚደርስ አልሆነም።የበለፀጉት ሐገራት ከአጠቃላይ ዓመታዊ ገቢያቸዉ 0.7 በመቶዉን ለድሆቹ ሐገራት ለመርዳት የገቡት ቃልም በአብዛኛዉ አልተከበረም።ለድሐዉ ዓለም የቀረዉ ተስፋ አንድ ነዉ።ሐዋላ።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ


እርግጥ ነዉ-የኢትዮጵያን ደን ጫካ፥ የኤርትራን ተረተር፥ ተራራ፥ ወይም የሶማሊያን ሁዳድ፥ ሜዳ፥ አልፎ-አንድም እንደ ሲናይ የመኑ፥ የበረሐ ሲሳይ አለያም እንደ አደን ባሕረ ሠላጤዉ፥ እንደ ሜድትራንያኑ፥ እንደ ታንዛኒያ፥ ማላዊዉ የባሕር፥ ሐይቅ ሲያሳይ የሆነዉን ወጣት ታሪክ ያየ-የሰማ---በሬ ሆይ ሳሩን አይተሕ--- ኢትዮጵያዊ ነባር ብሒሊን ከዘግናኙ እዉነታ ጋር ማሰላሰሉ አይቀርም።

የእድለ ቢሶችን ቀባሪ ያጣ አስከሬን እየተዘናገረ «ሳሩ» ካለበት የደረሰዉ አፍሪቃዊ በጣሙን ሴቱ በየደረሰበት የሚገጥመዉ ፍዳ፥ ፈተና የየዕለት አሳዛኝ ገጠመኝ ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ጉባኤ UNCTAD በምሕፃሩ እንደሚለዉ ግን የበለፀገዉ ዓለም በገጠመዉ የገንዘብ ቀዉስና የምጣኔ ሐብት ኪሳራ የተከፈቱ ቀዳዶቹን ለመድፈን በሚባትልበት ባሁኑ ወቅት አፍሪቃን ወደ መሳሰሉቿን ዘንግቷቸዋል።

ወደ ድሆቹ ሐገራት የሚያፈሰዉን መዋዕለ ንዋይ በእጅጉ ቀንሷል።የሚሰጠዉን ወይም ለመስጠት ቃል የገባዉን የልማት ርዳታም አጥፏል ወይም ቀንሷል። የወለደ ግን አይጥልም።የተወለደም አይረሳም።እና ድርጅቱ እንደሚለዉ አሁን የአፍሪቃና የብጤዎቻቸዉ የገንዘብ ምንጭ፥ እኒያ ሲሆን በቦሌ፥ ካልሆነም በባሌ- ዩሮ፥ ዶላር፥ ሪያል-ዲናር ካለበት የደረሱት ተወላጆች ናቸዉ።
              
«ሥለ ድሆቹ ሐገራት በቀረበዉ ዘገባ የተጠቀሰዉ መረጃ እንደሚያመለክተዉ በሐዋላ የሚላከዉ የገንዘብ መጠን አንደኛ፥-እየጨመረ ነዉ።ሁለተኛ፥-ለድሆቹ ሐገራት ከፍተኛ የዉጪ ገቢ ምንጭ ነዉ።»

ይላሉ የዩኒክታዱ ባልደረባ ኢጎር ፓኖቪኒች።የበለፀጉት ሐገራትን የመታዉ የገንዘብ ቀዉስ እዚያ የሚኖሩና የሚሰሩትን የድሆቹን ሐገራት ተወላጆች ሥራ-ኑሮን ማዛባቱ አንዳዶቹን መጉዳቱም አልቀረም።ወደየሐገራቸዉ የሚልኩት የገንዘብ መጠን ግን ፓኖቪኒች እንደሚሉት በተቃራኒዉ እየጨመረ ነዉ።
              
«ከሌሎች የዉጪ ገቢዎች ጋር ሲነፃፀር ሐዋላን የሚበልጠዉ ይፋዊዉ የልማት ርዳታ ብቻ ነዉ።የልማት ርዳታዉ መጠን በሁለት ሺሕ አስር አርባ-ሁለት ቢሊዮን ዶላር ግድም ነበር።ሐዋላዉ ሃያ-ሰባት ቢሊዮን።ሥለዚሕ ሐዋላ ለድሆቹ ሐገራት ሁለተኛዉ ከፍተኛ ጠቃሚ የዉጪ ገቢ ምንጭ ነዉ።ከዚሕም በተጨማሪ ሐዋላ ወደ ድሆቹ ሐገራት ከዉጪ የሚፈሰዉን የቀጥታ መዋዕለ ንዋይ መጠንን በእጥፍ አሳድጎታል።»

ዉጪ የሚኖረዉ የሚልከዉ ገንዘብ ለየቤተሰቡ የዕለት ከዕለት ፍጆታ ብቻ የሚዉል አይደለም። እሕት-ወንድም፥ ዘመድ-አዝማዱን ያስተምርበታል፥ ያሳክምበታል። ኪዮስ፥ ሻሒ ቤት ብጤ የሚከፍት፥ ቤት የሚያሠራም አለ።ሌላም።ሌላ።በዚሕም ምክንያት የጀርመኑ የልማት ጥናት ተቋም (DIE)  ባልደረባ ቤንያሚን ሻራቨን እንደሚሉት በሐዋላ የሚላከዉ ገንዘብ የየሚላክበትን ሐገር አጠቃላይ ምጣኔ ሐብቱን ለማጎልበትም ጠቃሚ ነዉ።
                      
«በመጀመሪያ ደረጃ የሚላከዉ ገንዘብ የየላኪዉን ቤተ-ሠብ ወቅታዊ ፍላጎት ወይም ፍጆታ ለማሟላት ብቻ የሚዉል አይደለም። ለሌሎች አገልግሎቶችም፥ ለምሳሌ ቋሚ የቤት ቁሳቁሶች ለመግዢያ፥በምጣኔ ሐብቱ እንቅስቃሴ ለሚያሳትፉ ለሌሎች ሥራዎችም ይዉላል።ይሕ ማለት የሚላከዉ ገንዘብ ዳግም ተወርቶ ለሌሎችም የሥራ-እድልና ጥሩ ጥቅም ይሰጣል።»

በዚሕ ሁሉ ጥቅሙ መሐል ግን ችግርም አለዉ።ገንዘቡ የሚላክባቸዉ የድሆቹ ሐገራት መንግሥታት ላኪዎች የሚልኩትን ገንዘብ ተጨማሪ ሥራ-በሚፈጥርበት መስክ ላይ እንዲያዉሉት ወይም ተጨማሪ ገንዘብ እንዲልኩ የሚያበረታታ መርሕ የላቸዉም።

በአብዛኞቹ ሐገራት የተቀላጠፈ፥ ሁሉም ጋ የሚዳረስ፥ ከሙስና የፀዳ፥ ርካሽ የባንክ አግልግሎት፥ ሥለሌለ ገንዘቡ የሚላከዉ በሰዉ፥ በሰዉ፥ የሚመነዘረዉ በጥቁር ገበያ ነዉ።አንዳዴ መላኪያዉ በጣም ዉድ በመሆኑ የሚላከዉ ገንዘብ መጠን በጣም ያንሳል።ለምሳሌ ከደቡብ አፍሪቃ ወደ ዛምቢያ ሁለት መቶ ዶላር ለመላክ አርባ አምስት ዶላር መክፈል ግድ ነዉ።

አንዴዴ ደግሞ ላኪዎች ሌት-ከቀን ደክመዉ የላኩት ገንዘብ ሐላፊነት ከጎደላቸዉ ወጣቶች እጅ ይገባና ወጣቶቹን ለሚጎዳ ወጪ ይባክናል።ሻራቨን እንደሚሉት የገንዘብ ዝዉዉሩ ቁጥጥር ሥለማይደረግበት ለሌላ ጥፋት ይዉልም ይሆናል።

ነጋሽ መሐመድ

Titel: Dollar iran Symbolbild Währungkriese Beschreinung: Ein Makler auf dem Teheraner Währungsmarkt zeigt die US amerikanische Dollar Lizenz: DW (wie oben)
ምስል DW
Logo UNCTAD

አርያም ተኬሌ
                    

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ