1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዴፓ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አማካሪ ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነት አጨ

ሰኞ፣ ሐምሌ 8 2011

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ለአማራ ክልል አዲስ ዕጩ ርዕሰ መስተዳድር መሰየሙን ዛሬ አስታወቀ። ፓርቲው በዕጩነት የሰየማቸው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር የሆኑትን አቶ ተመስገን ጥሩነህ ናቸው። አቶ ተመስገን የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ አባላትን ለመተካት በተደረገው ምርጫም ተመርጠዋል።

https://p.dw.com/p/3M7Nk
Das Logo der ADP Amharische Demokratischen Partei
ምስል ADP

አዴፓ አዲስ ምክትል ሊቀመንበር መርጧል

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ለአማራ ክልል አዲስ እጩ ርዕሰ መስተዳድር ሰየመ። የተጓደሉ የአዴፓ እና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባላትንም መርጧል።

የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሀም አለኸኝ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት ፓርቲው በቅርቡ በተገደሉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አምባቸው መኮንን ምትክ አቶ ተመስገን ጥሩነህን እጩ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ መሰየሙን ገልፀዋል።

አቶ ተመስገን በአማራ ክልል እና በፌደራል መንግስት ያላቸውን ረጅም ሥራ ልምድ የዘረዘሩት አቶ አብርሀም እጩ ርዕሰ መስተዳድሩ ለተሰየሙበት ቦታ ብቁ መሆናቸውን አስረድተዋል። የእጩ ርዕሰ መስተዳድሩ ሹመት የሚፀድቀው በአማራ ክልል ምክር ቤት እንደሚሆንም ኃላፊው በመግለጫው ጠቁመዋል።

የአማራ ክልልን እያስተዳደረ የሚገኘው አዴፓ በባህር ዳሩ የሰኔ 15 ጥቃት በተገደሉ የፓርቲው አመራሮች እና የስራ አስፈጻሚ አባላት የሚተኩ አባላትን መምረጡን የፓርቲው ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ገልጸዋል። ፓርቲውን በ ምክትል ሊቀመንበርነት እንዲመሩ አሁን የፓርቲውን የማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት በኃላፊ እየመሩ የሚገኙት አቶ ዮሐንስ ቧያለው መመደባቸውን ይፋ አድርገዋል።

Äthiopien Ato Yohannes Buayalew ADP
ምስል DW/A. Mekonnen

ዕጩ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ተመስገን እና የክልሉ የሰላም ግንባታ እና የደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር ለፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መመረጣቸውን አብራርተዋል። ሁለቱ አዲስ ተመራጮች የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እንዲሆኑ መመረጣቸውንም አቶ አብርሃም ገልጸዋል። 

በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላለፉት አምስት ቀናት ስብሰባ ሲያካሄዱ የቆዩት የአዴፓ ሥራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የደረሱባቸው ውሳኔዎች ተዘርዝረዋል። ሁለቱም ኮሚቴዎች በአማራ ክልል የህግን የበላይነትን ለማስከበር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አቶ አብርሃም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። የአማራን ህዝብ ማናቸውንም ጥያቄዎች ለመመለስ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋልም ብለዋል።

“ከትግራይ ህዝብ ጋር ምንም ዓይነት ችግር እንደማይኖር” የተናገሩት አቶ አብርሃም  “የሁለቱን ህዝቦች የቆየ ታሪክ እና እሴት ለመጠበቅ ማዕከላዊ ኮሚቴውም ሆነ ሥራ አስፈፃሚው የፀና አቋም እንዳላቸው” አመልክተዋል።

ዓለምነው መኮንን

ተስፋለም ወልደየስ 
አዜብ ታደሰ