1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃና የለም መሬቱ ቅርጫ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 6 2002

የውጭ ባለሃብቶች የአፍሪቃን ለም የእርሻ መሬት በሰፊው መግዛት ወይም መከራየት መያዛቸው ሰፊ ዓለምአቀፍ ትኩረት ማግኘት ከያዘ አንድ ዓመት ገደማ ሆነው።

https://p.dw.com/p/MwGM
ምስል AP

ረሃብ በአብዛኛው መለያው በሆነው ከሣሃራ በስተደቡብ በሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል ድሃው ገበሬ በመሬቱ ችብቸባ ይብስ እንዳይጎዳ ማሳሳቡና ከያቅጣጫው ቅሬታ መሰማቱም አልቀረም። ታዲያ ችግሮች በፍጥነት በሚፈራረቁባት በዛሬይቱ ዓለማችን ላይ ጉዳዩ በሌሎች ነገሮች ይሸፈን ወይም ከዓይን ሰወር ይበል እንጂ እክሉ ዛሬም ቢሆን አልተወገደም። የውጩ የግል ኩባንያዎች ግልጽነትን የሚያረጋግጥ ዓለምአቀፍ የስነ-ምግባር ደምብን ከማስፈን ወደ ኋላ እንዳሉ ሲሆን አፍሪቃውያን ባለሥልጣናት ደግሞ ሙስናንና የምግብ ዋስትና እጦትን ያዳብራል ተብሎ በሚፈራው ውል ተጠቃሚ እንደሆኑ ናቸው።

አፍሪቃ ውስጥ ባለፉት አራት ዓመታት ከሰላሣ ሺህ ሄክታር የሚበልጥ ለም የእርሻ መሬት ለውጭ ባለሃብቶች መከራየቱና መሸጡ ነው የሚገመተው። የውጭ ኩባንያዎችና መንግሥታት ጥቅም ባዩበት በዚህ ተግባር ድሆቹ የአፍሪቃ አገሮች የሚጎላቸውን ገንዘብና ቴክኖሎጂ በማግኘት ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ተሥፋ የጣሉ አይታጡም። ይሁንና ብዙዎች ባለሙያዎች፤ በተለይም ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች ሂደቱ ረሃብንና ማሕበራዊ ችግሮችን እንዳያባብስ ሲያስጠነቅቁ ነው የቆዩት።

በተወሰነው የታዳጊው ዓለም ክፍል ባለፉት ሁለት ዓመታት የታየው የረሃብ ዓመጽ ወይ ቁጣ በግልጽ የምግብ ዋጋ መናር ተጽዕኖ ያስከተለው ነበር። ሆኖም በተመሳሳይ ጊዜ ዓለምአቀፍ ባለሃብቶች በዓለም ላይ ለም በሆኑት አካባቢዎች በተለይም በአፍሪቃ የዕርሻ መሬት መግዛት ይቀጥላሉ። አፍሪቃውያኑ መንግሥታት በፊናቸው ንግዱን አዘውትረው “የእርሻ ኢንቨስትመንት” ይበሉት እንጂ የመሬት ሽያጩን የተወሰነው የአፍሪቃና የምዕራቡ ሲቪል ሕብረተሰብ ክፍል የመሬት ንጥቂያ አድርጎ ነው የሚመለከተው።

በአፍሪቃ የተያዘውን የለም መሬት ሩጫ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት በጊዜው ከሃብታም አገሮች የዕጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ዘይቤ ጋር ነበር ያመሳሰለው። ፊያን በመባል የሚታወቀው የሰብዓዊ መብት ድርጅት ባልደረባ ሶፊያ ሞንሣልቭም ገበሬዎቹ የሚያጡት መሬታቸውን ብቻ ሣይሆን ራሳቸውን በራሳቸው የመቀለብ ዕድላቸውን ጭምር እንደሆነ ነበር ያስገነዘቡት።

“የሚያሳዝን ሆኖ አዘውትረን የምንታዘበው እነዚህን ዓይነቶቹ ባለሃብቶች መሬቱን የመጠቀሙን መብት ሲያገኙ ወይም ሲገዙት በዚያ ይኖሩ የነበሩት ሰዎች በሃይል ሲባረሩ ነው። ካሣ አያገኙም፤ በሌላ ቦታ እንዲሰፍሩም አይደረግም። ይህ ደግሞ በግልጽ በዓለምአቀፍ ሕግጋት መሠረት በቀላሉ መቀበል የማይቻል የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው”

የአነስተኛው ገበሬ መብት በዚህ መልክ መረገጡን ከቀጠለና በገዛ አገሩ የአጥር ውጭ ተመልካች እንዲሆን ከተደረገ ብዙዎች የቅርብ ታዛቢ ባለሙያዎች እንደሚሉት የሚከተለው ዓመጽ ነው። በማዳጋስካር የቀድሞው ፕሬዚደንት ማርክ ራቫሎማናና ሥልጣን ለመልቀቅ የበቁት በዚሁ በለም መሬት ንግድ ሳቢያ በተቀሰቀሰ ቁጣ ነበር። ፕሬዚደንቱ ለደቡብ ኮሪያው ዴዉ ኩባንያ 1,3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለ 99ዓመታት ለማከራየት ሲነሱ ይህም ለግንዛቤ ያህል ከደሴቲቱ ለም መሬት ግምሹን ያህል መሆኑ ነበር።
በቆሎና የወይራ ዘይት ተክል በማምረት ወደ እሢያ ለመላክ ያቀደው ኩባንያ ምንም እንኳ ሰባ ሺህ የሥራ ቦታዎችን እከፍታለሁ ሲል ተሥፋ ቢሰጥም ተቃውሞው ሊቀሰቀሰ ብዙ አልወሰደበትም። ሁኔታው በማዳጋስካር ብቻ የተወሰነም አይደለም። ከማዳጋስካር ሌላ ለም የእርሻ መሬታቸውን ለኪራይ ወይም ለሽያጭ የሚያቀርቡት የአፍሪቃ አገሮች ቁጥር ኢትዮጵያን ጨምሮ ባለፉት ዓመታት እየጨመረ ነው የመጣው። የራሳቸውን እያደገ የሚሄድ የምግብና የባዩ ነዳጅ ፍላጎት ለማሟላት ወይም በርካሽ ያመረቱትን በሌሎች ገበዮች በመሸጥ ለመጠቀም መሬት ከሚፈልጉት መካከል ደግሞ ቻይናን፣ ሕንድን ደቡብ ኮሪያን፣ ጃፓንን፣ ሳውዲት አረቢያንና ኩዌይትን የመሳሰሉት የሚገኙበት ሲሆን የአውሮፓ ኩባንያዎች ትኩረትም እየጨመረ ሄዷል።

ለነገሩ በተባበሩት መንግሥታት የተፈጥሮ ጥበቃ ተቋም የምግብ ጉዳይ ባለሙያ በክሪስቲያን ኔለማን ዕምነት በተወሰነ ሁኔታ ለአፍሪቃ አገሮችም ጥቅም ባልጠፋ ነበር።

“ሌሎች መሬት መከራየታቸው በመሠረቱ በአከራዮቹ አገሮች ዘንድ ለመዋዕለ-ነዋይ ዕድገት መነሻ ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ የሥራ ቦታዎችን በመፍጠርና ደሞዝን ከፍ በማድረግ ለኪራይ በተመረጠው አገር ውስጥ የምግብ ዋስትናንም ሊያሳድግ የሚበጅ ነው”

ግን ለዚህ የአፈጻጸሙ ሁኔታ ወሣኝ ነው።

“እርግጥ ይህ የሚሆነው የኢንቨስትመንቱ አፈጻጸም ግልጽ በሆነ መንገድ ሲካሄድና ዋናው ትኩረት በእርሻው ልማት፤ እንዲሁም በእርሻው ልማት ዕርምጃ ላይ ሲያርፍ ነው። ይህ ከተደረገ ጠቃሚ ነገር ይሆናል ...”

ካለፈው ዓመት ወዲህ አሻሚ ሆኖ በሚገኘው በዚሁ ጉዳይ ተቀማጭነቱ ለንደን ላይ የሆነው ነጻ ድርጅት ዓለምአቀፉ የአካባቢ ተፈጥሮና የልማት ኢንስቲቲዩትም ማተኮሩ ይታወቃል። ድርጅቱ “የመሬት ንጥቂያ ወይስ የልማት ዕድል?” በሚል ርዕስ ባካሄደው ጥናት መዋዕለ-ነዋዩ የአካባቢውን ነዋሪ የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል አዲስ ዕድልን ይፈጥራል ወይም አበለዚያ ድሃውን ሕዝብ ይበልጥ ያገላል ሲል ነበር የደመደመው።

እርግጥ ስምምነቱ በአግባብ ከሰፈነ ለልማት ሊበጅ ይችላል። የበለጠ መዋዕለ-ነዋይ በሥራ መዋሉ አጠቃላይ ብሄራዊ ምርትንና የመንግሥትን ገቢ ሊጨምር የሚችል ነው። በዚሁም የውጭ ባለሃብቶች ካፒታል፣ ቴክኖሎጂና ዕውቀትን ሊያስገቡ ይችላሉ፤ ይህም በመሠረቱ ለአካባቢው የኑሮ ደረጃ ዕድገት መንገድ የሚከፍት ነው። ግን መንግሥት ለባለሃብች መሬት በሚሰጥበት ጊዜ የአካባቢው ነዋሪዎች ለሕልውናቸው መሠረት ከሆኑ ምንጮች ሊነጠሉም ይችላሉ። ይህም ሲባል መሬት ብቻ አይደለም፤ ውሃን፣ እንጨትንና የግጦሽ መሬትን የመሳሰሉትንም ይጠቀልላል።

በጥቅሉ የለም መሬቱ ዘመቻ ከፍተኛ ክርክርን ከቀሰቀሰ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላም በለተይ ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ተቆርቋሪ ድርጅቶች ለተሥፋ ብዙም ምክንያት አይታይም በሚል አቋማቸው ጸንተው እንደቀጠሉ ነው። ታንዛኒያ ለምሳሌ አክሺን-ኤይድ ለተሰኘው ዓለምአቀፍ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጉዳዩን የሚከታተሉት አንቱዋን ቡሄይ እንዳስረዱት በትናንሽ ገበሬዎች ግፊት በባዮ-ነዳጅ እርሻዎች ላይ መዋዕለ-ነዋይ መደረጉን ባለፈው ሕዳር አግዳለች።

የእርሻ መዋዕለ-ነዋይን በተመለከተ መሠረታዊ መርህ ለማስፈን የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት፣ የዓለም ባንክና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማትም ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው አልቀረም። ችግሩ እስካሁን ጭብጥ ነገር አለመታየቱ ላይ ነው። የውስጥ አዋቂዎች እንደሚሉት ጉዳዩ አሁንም መግባባት ያልተገኘበት ነው። አንዳንድ ለጋሽ ሃገራት የስነ-ምግባር ደምብ ለማርቀቅ የሚሹ ቢሆንም በሌላ በኩል የግሉን ዘርፍ ማግባባቱ ቀላል ነገር አልሆነም።
የለንደኑ ዓለምአቀፍ የአካባቢ ተፈጥሮና ልማት ኢንስቲቲዩት በዘገባው እንዳስገነዘበው በብሄራዊ ደረጃ ዋስትና የሚሰጥ ፍቱን ሕግ፤ እንዲሁም በብቃትና በግልጽነት በሚካሄድ ድርድር የሚሰፍኑ ውሎች የድሃውን ገበሬ የመሬትና የውሃ መብት ለማረጋገጥ ቁልፍ ናቸው። ሆኖም እንደ ድርጅቱ ሃላፊ እንደ ካሚላ ቱልሚን ዛሬ በብዙዎቹ ውሎች ላይ የሚደረገው ድርድር የሚካሄደው ዝግ ሆኖ ነው። እንግዲህ የግልጽ አሠራር መጓደልና ሙስና ሃብታሞቹንና ሃያላኑን መጥቀሙ አልቀረም።

ይህ በዚህ መቀጠል የለበትም። መንግሥታት ለመደረራደርና ተገቢውን ውል ለማስፈን ብቃት ከሌላቸው፤ ሲቪሉ ሕብረተሰብም በመንግሥት አካሄድ ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ ካልበቃ ጨርሶ ሁኔታውን ለማሻሻል አይቻልም። ዛሬ 80 በመቶው ረሃብተኛ የዓለም ሕዝብ የሚኖረው በገጠር፤ በአብዛኛውም በአፍሪቃ ነው። ብዙዎቹ ደግሞ ቢቂ የሚታረስ መሬት ስለሌላቸው የሚፈልጉትን ያህል ሊያመርቱ አይችሉም። የአካባቢ አየር ለውጥና ሌሎች ምክያቶችም ተጨምረው ደግሞ ሁኔታቸውን ቀላል አያደርጉትም። በመሆኑም ምግብ የማግኘት ሰብዓዊ መብታቸው እንዳይገፋ ዋስትና የሚሰጥ የእርሻ ልማት ፖሊሲ በግድ መራመድ እንዳለበት ነው ጉዳዩ የሚመለከታቸው የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን ኦሊቨር-ዴ-ሹተር ገና ከጅምሩ ያስገነዘቡት።

“ድሆቹን ማገዝ እንዲቻል ምግብን በብዛት ማምረቱ ብቻ በቂ አይደለም። በተሻለ ሁኔታ ጭምር እንጂ! ምርቱን ከክፍፍሉ ነጥለን ካየነውም ስኬት ልናገኝ አንችልም”

መስፍን መኮንን/አርያም ተክሌ