1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃን ያሰጋው የረሀብ አደጋ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 2 2009

በአንዳንድ የአፍሪቃ ሀገራት በተከሰተው ድርቅ ሰበብ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የረሀብ አደጋ አስግቷቸዋል። በሶማልያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ እና በቻድ ሀይቅ አካባቢ ሁኔታው አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የርዳታ ድርጅቶች በማመልከት ለተጎጂዎች ድጋፍ እንዲቀርብ ጥሪ አስተላልፈዋል።

https://p.dw.com/p/2afu3
Südsudan Hunger Behinderung von Hilfsorganisationen
ምስል Getty Images/AFP/Stringer

Hungerkrise Afrika - MP3-Stereo

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የችግሩን አሳሳቢነት ቢያውቅም፣ ሀብታሞቹ ሀገራት ለመስጠት ቃል ከገቡት ርዳታ መካከል እስካሁን ያቀረቡት በጣም ንዑሱን ከፊል ብቻ ነው። ምንም እንኳን የአፍሪቃ ህብረት ለቀውሱ መፍትሔ ለማፋላለግ ቢሞክርም እና አንዳንድ ሀገራትም የበኩላቸውን ቢያደርጉም፣ በአፍሪቃ  ተጎጂዎቹን ለመርዳት የታየው ትብብርም፣  ያን ያህል አለመሆኑ ነው የሚሰማው።  
                                
በተመድ የብሪታንያ አምባሳደር ማትዩ ራይክሮፍት ከአንድ የልዑካን ቡድን ጋር ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማልያ እና የቻድ ሀይቅ አካባቢን በመጎብኘት የረሀቡ አደጋ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተመልክተዋል። በዚሁ በናይጀሪያ፣ ኒዠር እና ቻድ መካከል በሚገኘው አካባቢ የናይጀሪያ አሸባሪ ቡድን ቦኮ ሀራም ከብዙ ዓመታት ወዲህ ሽብሩን አስፋፍቷል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፣ ታግተዋል፣ ከመንደሮቻቸው ተባረዋል። ይህ አልበቃ ያለ ይመስል ደግሞ  አሁን በድርቅ ሰበብ ትልቅ ችግር እንደገጠማቸው ራይክሮፍት አስታውቀዋል።
« የሰብዓዊ ቀውሱ ደረጃ ተጋኖ ቀርቧል የሚል ጥያቄ ሲነሳ ይሰማል። ግን፣ አልተጋነነም። ሁኔታው በየቀኑ እየከፋ በመሄድ ላይ መሆኑን ተመልክተናል።  አዎ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና የተጎዱት ሀገራት ራሳቸው አንዳንድ ርምጃ በመውሰዳቸው፣ እርግጥ፣ አሁን በሁሉም አካባቢዎች እኩል ረሀብ ገብቷል ብለን ልንናገር አንችልም፣ ረሀብ ገብቷል የምንልበት ደረጃ ላይ አለመድረሳችንን አፅንዖት ሰጥቼ እናገራለሁ። »
በረሀብ እጅግ ብዙ ሰዎች በመጎዳታቸው፣ ራይክሮፍትም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ላይ አስፈላጊውን ርዳታ በጊዜ እንዲያቀርብ ግፊታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው በሚገባ ተገንዝበውታል። ። ከአፍሪቃውያን አጋሮቻቸውም ጋር በግልጽ መነጋገር አለባቸው። 
« ለቀውሱ ዓለም አቀፉ  ብቻ ሳይሆን ብሔራዊው ምላሽም መሰጠት አለበት። የናይጀሪያ እና ያካባቢው ሀገራት መንግሥታት ቀውሱን ለመታገል ተጨማሪ ጥረት  እና የፋይናንስ ርዳታ እንዲያደርጉ ጠይቀናል። ለዚሁ ጥሪያችንም አበረታቺ ምላሽ ሰምተናል፣ እንግዲህ ፣ አሁን ይከው የገቡትን ቃል በተግባር የሚተረጉሙበትን ርምጃቸውን በመጠባባቅ ላይ እንገኛለን። »  
ናይጀሪያ አንድ ቢልዮን ዶላር ዝግጁ ለማድረግ አስታውቃለች፣ ይሁንና፣ እስካሁን አንድም የቀረበ ገንዘብ የለም። «አክት ፎር አካውንተብሊቲ» የተሰኘው የናይጀሪያውያን ሲቭል ማህበረሰብ ተቋም ባልደረባ ኦሞሎላ አዴል ኦሶ እንደሚሉት ግን፣ በረሀብ አንፃር በሚደረገው ትግል ላይ የገንዘብ እጥረት ብቻ አይደለም ትልቁ ችግር። 
« ሙስናም ሌላው ችግር የደቀነ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ፣ ናይጀሪያ ውስጥ በርዳታ የቀረበ ሩዝ በሌላ ጆንያ ታሽጎ  በገበያ ሲሸጥ ይታያል። ስለዚህ ፣ ብዙው የምግብ ርዳታ ለተቸገሩት አይደርስም። »

Afrika - humanitäre Hilfe im Tschadsee-Gebiet
ምስል Getty Images/AFP/I. Sanogo
Somalia Hungerkrise Lebensmittel Not Juli 2011
ምስል dapd

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በረሀቡ አኳያ እጅግ ዘግይቶ ምላሽ የሰጠበትን ድርጊት የጀርመን የልማት ትብብር ሚንስትር ጌርድ ሚውለር አሳፋሪ ብለውታል። የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ሙሳ ፋኪ ማሀማታ አፍሪቃውያኑም ራሳቸው ቢሆኑ የድርቅ ሰለባዎችን ለመርዳት በቂ ትብብር አላሳዩም በማለት ወቀሳ ሰንዝረዋል።  

« ብዙውን የአፍሪቃ ከፊል በወቅቱ ያሰጋው የረሀብ አደጋ በእውነት ለኛ ውርደት ነው። አህጉራችን የያዘው ግዙፍ እድል እና አንዳንድ የአፍሪቃ ህብረት አባል ሀገራት ያሳዩት አስገራሚ የኤኮኖሚ እድገት ሲታሰብ ፣ ይህን አሳዛኝ ሰብዓዊ ቀውስ ርምጃ ሳንወስድ ልናልፍ የምንችልበት አንድም መከራከሪያ ሀሳብ ልናቀርብ አንችልም። »
በሶማልያ አሸባብ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች እና መንግሥት እና ዓማፅያን የሕዝቡን ስቃይ ችላ በማለት ውጊያ በቀጠሉባት ደቡብ ሱዳን ውስጥ ሁኔታው እየከፋ የሄደ ሲሆን፣ ጥቂት አፍሪቃ ህብረት አባል ሀገራት ብቻ ናቸው ችግሩን በመቀነሱ ረገድ ኃላፊነት ያሳዩት። ዩጋንዳ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን ተቀብላለች፣ ኢትዮጵያም በምትችለው ሁሉ ሶማልያውያን የረሀብ ሰለባዎችን ለመርዳት በምትችለው ሁሉ እየሞከረች መሆኑን በጀርመን የኢትዮጵያ ዲፕሎማት አቶ ሙሉጌታ ዘውዴ ገልጸዋል። 
« ከሶማልያ ወደ ሶማሌ ክልል መምጣት የሚፈልጉትን ሶማልያውያን ኢትዮጵያ  ለመቀበል ወስናለች፣ ምክንያቱም እጅግ የከፋ ችግር ውስጥ ነው የሚገኙት። ባንድ በኩል በጦርነት፣ በሌላ ወገን ደግሞ በድርቅ እየተሰቃዩ ነው። እና እነዚህን ሰዎች አሁን ካልሆነ ሌላ ጊዜ ልትረዳ አትችልም። »
ኢትዮጵያ ግን ራሷ በወቅቱ 5,6 ሚልዮን ሕዝቧ የምግብ እጥረት አጋጥሞታል፣ ከዚህም መካከል ሁለት ሚልዮኑ የሚኖረው በሶማሌ ክልል ነው። ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ ለዚሁ ዝግጁነታቸው ከሌሎች አፍሪቃውያት ሀገራት ድጋፍ ለማግኘት ተስፋ ቢያደርጉም፣ ይኸው ጥሪያቸው እስካሁን ሰሚ አላገኘም። ለቀውሱ መፍትሔ በማፈላለጉ ረገድ እስካሁን ውጤት ያላስገኘው የአፍሪቃ ህብረት ፣ ባልተመጣጠነ አመጋገብ ለተጎዱ ህፃናት መርጃ የሚሆን 200,000 ዶላር ብቻ ዝግጁ በማድረግ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ  ርዳታ ለመስጠት የገባውን ቃል እንዲጠብቅ መጠየቁን ቀጥሏል።

Äthiopien Bundesentwicklungsminister Gerd Müller in der Somali-Region
ምስል picture-alliance/dpa/K. Nietfeld

አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ