1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃውያት ሀገሮች እና የሊቢያ ወረት

ቅዳሜ፣ መጋቢት 17 2003

በሊቢያ የመንግስቱ ጦር ኃይላት በሀገራቸው የተቃዋሙ ቡድኖች አንጻር ግዙፍ የኃይል ርምጃ ከወሰዱ በኋላ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሊቢያ ላይ የበረራ ዕገዳ ማዕቀብ በመጣል ካለፈው ሳምንት ወዲህ ይህችኑ ሀገር በመደብደብ ላይ ይገኛል።

https://p.dw.com/p/RCuh
ምስል AP



ካለፉት ጥቂት ሳምንታትም ወዲህ በውጭ የሚገኘው የሊቢያው መሪ ሙአመር ኧል ጋዳፊ ንብረት እንዳይንቀሳቀስ ጠንካራ ማዕቀብ ጥሎዋል። በዚሁ መሰረት በአውሮጳ የሚገኘው የጋዳፊ እና የቤተሰባቸው የባንክ ሂሳብ ታግዶዋል። ይሁን እንጂ፡ በአፍሪቃ የሚገኘው የሊቢያው መሪ ንብረት በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ተገልጾዋል። ጋዳፊ በብዙ አፍሪቃውያት ሀገሮች ውስጥ በመጓጓዣው፡ በግንባታው፡ በአገልግሎት ሰጪው ዘርፍ እና በተቋማት ውስጥ ገንዘባቸውን በሰፊው እያሰሩ ነው። የሊቢያ መንግስት ንብረት የሆነው ኦይል ሊቢያ የተሰኘው ኩባንያም በሀያ አፍሪቃውያት ሀገሮች ውስጥ ከሁለት ሺህ የሚበልጡ የቤንዚን ማደያ ጣቢያዎች አሉት። አሁን ምዕራባዊው ዓለም በሊቢያ አንጻር እያካሄደው ያለው የጥቃት ዘመቻ በብዙ የአፍሪቃ ሀገሮች ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታኣዊ ተጽዕኖ ማሳረፉ እንደማይቀር የኤኮኖሚ ጠበብት ግምታቸውን አሰምተዋል።

አርያም ተክሌ

መስፍን መኮንን