1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ቴክኒክ

አፍሪቃውያን ሴቶች ለምን ከኢንተርኔት ራቁ?

ዓርብ፣ ነሐሴ 3 2011

በርግጠኝነት ኢትዮጵያ ውስጥ ዕድሉ ኖሯቸው እንኳን ኢንተርኔት የማይጠቀሙ ሴቶች ታውቃላችሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአፍሪቃ ሃገራትም ተመሳሳይ ሁኔታ ይስተዋላል። ሴቶች ከወንዶች ጋር ሲነፃጸር አፍሪቃ ውስጥ እንብዛም የኢንተርኔት ተጠቃሚ አይደሉም። ለምን?

https://p.dw.com/p/3Na9I
Kenia Symbolbild Smartphones
ምስል Getty Images/AFP/Y. Chiba

አፍሪቃውያን ሴቶች ለምን ከኢንተርኔት ራቁ?

ፈልገውም ይሁን ሳይፈልጉ 200 ሚሊዮን የሚሆኑ ሴት አፍሪቃውያን ዛሬም የኢንተርኔት ተጠቃሚ አይደሉም። ተንቀሳቃሽ ስልክ ካላቸው ሴቶች አንድ ሦስተኛ ያህሉ ብቻ በስልካቸው ኢንተርኔት ይጠቀማሉ ተብሎ ይታመናል። ወንዶች በአንጻሩ ካጠቃላይ ቁጥር ሁለት ሦስተኛ ይሆናሉ። ኢንተርኔት አጠቃቀምን በተመለከተ አፍሪቃ ውስጥ በሁለቱ ፆታዎች መካከል ያለው ልዩነት ወይም የ«ሞባይል ኢንተርኔት ጀንደር ጋፕ» ሰፊ ነው። 41 በመቶ ያህል። ሴት ኢትዮጵያውያን ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ? የ 22 ዓመቷ ወጣት አሚናት አሚር « በኢኮኖሚ እና በነፃነት ማጣት ምክንያት ኢንተርኔት መጠቀሜን ቀንሻለሁ ትላለች።

ወይዘሮ አሚናት ኢብራሂም ደግሞ በወሎ ገጠራማ አካባቢ ነው የሚኖሩት። ማንበብ መጻፍ አለመቻላቻው ኢንተርኔትን በፈለጉት መጠን እንዳይጠቀሙ አድርጓቸዋል። « ኃትስዓፕ እና የመሳሰሉትን እንዴት እንደሚሰራ አይተን በድምፅ መልዕክት መለዋወጥ እንጠቀማለን።»

ሴኔጋላዊቷ አኢሳታ ፋል ምንም እንኳን ስማርት ፎን ተብሎ የሚጠራው ዘመናዊ ተንወሳቃሽ ስልክ ቢኖራትም እንብዛም ተጠቃሚ አይደለችም።« እርግጥ ነው ስማርት ፎን አስፈላጊ መሣሪያ ነው። ለሥራም ይሁን ከቤተሰብና ጎደኞች ጋር ለመገናኘት ይረዳል። ብዙ ሴቶች ኢንተርኔት ለመጠቀም ገንዘቡ የላቸውም። ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ እንደ እኔ ያገባች ሴት የማይሆን መልዕክት ወይም ፎቶ ቢላክላት እና ቀናተኛ ባል ካላት ብዙ ችግር ውስጥ ሊከታት ይችላል። » ትላለች አኢሳታ ።

ናይጄሪያዊቷ ጠበቃ ያልዋቲ ሹአቡም ቢሆኑ በስልካቸው ኢንተርኔት የሚጠቀሙት የሥራ ጉዳይን በተመለከተ በኢሜል የሚመጣላቸውን መልእክት ለማንበብ ሲፈልጉ ነው።« በስልኬ ኢንተርኔት እንብዛም አልጠቀምም። የሥራዬ ተፈጥሮ ሆኖ ዘግይቼ ነው የምጨርሰው። እቤት እንደገባሁ የቤተሰቤ ጉዳዮች ላይ ነው የማተኩረው። እኔ የመጣሁበት ማኅበረሰብ ሴቶች ኢንተርኔት አይጠቀሙም። አብዛኞቹም ስማርት ፎን የላቸውም። ኢንተርኔት ለመጠቀም ደግሞ እንደዚህ አይነት ስልኮች ያስፈልጋሉ። ወንዶች ከሴቶች የበለጠ ኢንተርኔት የሚጠቀሙበት በርካታ ምክንያቶች አሉ።  ወንዶች በብዙ ቦታዎች ተሳትፎ አላቸው፣ ከሴቶች የተለየ ብዙ አላማም አላቸው።»

Kenia Bäuerinnen erhalten per SMS Nachricht auf dem Handy
ምስል Imago Images/photothek/T. Imo

ለምን የኢንተርኔት አጠቃቀም በፆታዎች መካከል ይህን ያህል ልዩነት ፈጠረ? በመላው ዓለም 800 የሚጠጉ የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች ሕብረት የሆነው GSMA ለልዩነቱ በርካታ ምክንያቶችን ያነሳል።  መጻፍ እና ማንበብ አለመቻል፣ የኢንተርኔት አገልግሎቱን አጠቃቀም አለማወቅ፣ ዳታ የማግኘት ውስንነት እና የአስተማማኝነቱ ሁኔታ ጥቂቶቹ ናቸው።

« ስልክ እና ኢንተርኔትን ለመጠቀም በራሱ የሚጠይቀው ዕውቀት አለ። አህጉሩ ላይ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት በዚህ በኩል ሴቶች ከወንዶች ወደ ኋላ ቀርተዋል። ሌላው ደግሞ ስልኮች እና የኢንተርኔት ዳታዎች ርካሽ አይደሉም። አንድ በኬንያ የገጠር መንደር ውስጥ ያለች ሴት ስማርት ፎን ከምትገዛ ይልቅ ለበዓል ለልጆቿ በግ ብትገዛ ትመርጣለች። ቤተሰባቸውን  በቀን በ አንድ  ዶላር ለማኖር ለሚታገሉ ሰዎች የኢንተርኔት አገልግሎትን ገዝቶ መጠቀም በጣም ከባድ ነው። » ይላሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሁማን ራይትስ ዎች ድርጅት የሴቶች መብት ባለሙያ አግነስ ኦዲሃምቦ ።

የ 21 ዓመቷ ወጣት ሞዛምቢካዊት ኢሬኔ ሎሬንሶ ለምሳሌ ኢንተርኔት መጠቀም ብትችል ምኞቷ ነበር። ሞዛምቢክ ውስጥ ካሉት ሴቶች ግማሽ ያህሉ ዘመናዊ ስልክ ቢኖራቸውም ኢንተርኔት የሚጠቀሙት ግን አንድ አስረኛ ያህሉ ናቸው።« ምንም እንኳን ኢንተርኔት ማግኘት የምችልበት ስልክ ቢኖረኝም ኢንተርኔት አልጠቀምም። መጽሐፍ ስልኬ ላይ መጫን ብችል ደስ ይለኝ ነበር። ነገር ግን ዋጋው ውድ ነው። »

Afrika | Mobile money
ምስል picture-alliance/dpa/Godong

አፍሪቃውያን ሴቶች ከወንዶች ጋር ሲነፃፀር በኢንተርኔት አጠቃቀማቸው ወደ ኋላ ለቀሩበት ምክንያት ኬንያዊቷ ኦዲሃምቦ ሌላ ምክንያትም ያነሳሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች ሴቶች ዘመናዊ ስልክ መያዛቸው አግባብ ተደርጎ አይቆጠርም። ይህ ብቻ አይደለም። ራሳቸው ካርድ ፍቀው ሂሳብ ለመሙላት አቅሙም ጊዜውም የላቸውም። « ሴቶች እርሻ መሄድ፣ ውኃ ለመቅዳት ምንጭ መውረድ፣ ልጆችን መንከባከብ ይኖርባቸዋል። በዚህ መሃል ኢንተርኔት አገልግሎት የምታገኝበትን ካርድ ለመግዛት ብዙ ተጉዛ ስልኳን ለመሙላት ጊዜ አይኖራትም።» 

በገጠራማ አካባቢ ገንዘብ መሙላቱ ብቻ ሳይሆን የመብራት አገልግሎትም ስለማይኖር ባትሪውን ለመሙላት ኤሌክትሪክ ኃይል ወደሚያገኙበት አካባቢ ርቆ መጓዝም ሌላኛው የሴቶች ፈተና እንደሆነ የመብት ባለሙያዋ ይናገራሉ።

የኢንተርኔት አቅራቢዎች ሕብረት የሆነው GSMA በዓለም ዙሪያ ያሉ ሴቶች እንደ ወንዶች የኢንተርኔት ተጠቃሚ ሆነው ቢሆን ኖሮ አጠቃላይ የአለም አመታዊ ምርት በ 700 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያድግ እንደነበር ያመለክታል።  ይህ ለአፍሪቃም ትልቅ ዕድል ይፈጥር ነበር። እንደ GSMA ከሆነ አፍሪቃ ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት በሞባይል ቴክኖሎጂ አገልግሎት 110 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር አግኝታለች።  ሦስት ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በዘርፉ ተሰማርተው ይሠራሉ።  ዕቅዱ የኢኮኖሚ ብቻ አይደለም። የሴቶች መብት ተሟጋቿ ሞዛምቢካዊት ግሬሳ ሳሞ እንደሚሉት የፖለቲካም ነው።

« በዚህ ዓመት በሞዛምቢክ ምርጫ ይካሄዳል። ይህ ደግሞ በኢንተርኔት አማካኝነት ከሴቶች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እና መረጃ ለማቀበል ዕድል ይሰጣል። የምርጫውን ሂደት፤ በምርጫ ሂደቱ ክርክሮች ለምን እንደሚያስፈልጉ፣ ሴቶች እንዴት በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ተሳታፊ መሆን እንደሚችሉ ያውቃሉ ፣ የውሳኔው አካልም ይሆናሉ፤ ያኔ መሪዎቻቸውን ተጠያቂ ሊያደርጉ ይችላሉ። »

Frau mit Mobiltelefon, Quelimane, Mosambik, Afrika
ምስል picture-alliance/imagebroker/U. Doering

የኢንተርኔት አቅራቢዎች ሕብረት የሆነው GSMA የተፈጠረውን ክፍተት ሊደፍኑ የሚያስችሉ የመፍትሄ ሀሳቦች አሉት። በቅድሚያ መንግሥታት ሴቶች የበለጠ የኢንተርኔት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገዶች በግልፅ ማቅረብ ይኖርባቸዋል። ከዚህም ሌላ ከሴቶች የገንዘብ አቅም ጋር የተመጣጠነ የስልክ አገልግሎት ስልጠና መሰጠት አለበት። ጋና ውስጥ ለምሳሌ መንግሥታዊ ያልሆነው ICT ድርጅት ልጃ ገረዶች በኮሙኒኬሽን እና ቴክኖሎጂው ዘርፍ ተሳታፊ የሚሆኑበትን ፕሮጀክት ነድፎ እየሠራ ይገኛል። በገጠራማ አካባቢ የሚኖሩ ሴቶችን ተንቀሳቃሽ ስልክ በመስጠት እንዲሁም ሴቶች የማንበብ ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ የኢንተርኔት አቅራቢዎች ትኩረት ሰጥተው ይሠራሉ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ አግነስ ኦዲሃምቦ እንደዚህ አይነት ተሳትፎዎች የበለጠ እንዲበረታቱ ይመክራሉ። « ሴቶች ተንቀሳቃሽ ስልክ እና ኢንተርኔትን ጨምሮ ለቴክኖሎጂ ዕድል እንዲያገኙ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። በዲጂታል ዘመን ነው የምንኖረው። መረጃ ትልቅ አቅም አለው። ብዙ አገልግሎቶች እየተሰጡ ነው። ሴቶች ለኢኮኖሚው ወሳኝ ናቸው። ቤተሰብ እና ማኅብረተሰባችንን ይመሠርታሉ። ይህንን አካል መርሳት ማለት ደግሞ የምጣኔ ሀብታችንን አቅም በአግባቡ አለመጠቀም ማለት ነው።»

አፍሪቃ ውስጥ ሴቶች ከወንዶች ጋር ሲነፃጸር እንብዛም የኢንተርኔት ተጠቃሚ ያልሆኑበትን ምክንያቶች እና መፍትሄ የቃኘው የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት በዚሁ ይጠናቀቃል።

ሲልጃ ፍሮህሊሽ/ ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ