1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ኢትዮጵያ ዛሬ ይፋ በተደረገው የዓለም የረሐብ አመልካች ዘገባ ከ104ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች

ሐሙስ፣ ጥቅምት 2 2010

ረሐብ በዓለም ዙሪያ ከጎርጎሮሳዊው 2000 ዓ.ም. ጀምሮ በአራት እጅ ቀንሷል። ግጭት እና ድንገተኛ የአየር ጠባይ ክስተት ግን ረሀብን በመቀነሱ ረገድ የተገኘውን ውጤት ወደ ኋላ ሊመልሱት ይችላሉ ሲል ዛሬ ይፋ የሆነው የዓለም የረሐብ አመልካች ዘገባ አስጠንቅቋል።

https://p.dw.com/p/2lkMn
Infografik Welthungerindex 2017 ENG ***SPERRFRIST BIS 12.10.2017 (10:00 Uhr CEST)***

ኢትዮጵያ 104ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች

ኢትዮጵያ ዛሬ ይፋ በተደረገው የዓለም የረሐብ አመልካች ዘገባ ከ104ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በኢትዮጵያ ያለው ረሐብ እንደ አንጎላ እና ርዋንዳ ሁሉ ብርቱ ከሚባሉት ጎራ ተመድቧል።  ሶስቱ አገሮች ከገቡበት የረሐብ ማጥ ለማገገም ከፍ ያሉ ፈተናዎች ይጠብቋቸዋል። ቢሆንም ከከፋ ረሐብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጦት በመላቀቃቸው በደም አፋሳሽ ግጭት እና ጠኔ ለሚዋትቱ አገሮች ግን ተስፋ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል። 

በዓለም ላይ የሚታየው ረሐብ ባለፉት ሰባት አመታት በአራት እጅ ቢቀንስም ዛሬ ይፋ የተደረገው ዘገባ ግን እንደገና ማንሰራራቱን ይጠቁማል። ዘገባው እንደሚለው የረሐብ ቅነሳው በሁሉም የዓለም ክፍል እኩል አይደለም። ባለፈው የጎርጎሮሳውያኑ አመት አራት አገራት ረሐብ ጥላውን ጥሎባቸው ነበር። ግጭት እና የአየር ጠባይ ለውጥም በተለይ በድሆች ላይ በርትተዋል። 

አፍሪቃ በተለይም ከሰሐራ በታች የሚገኙ አገራት በዋንኛነት ችግሩ የጠናባቸው ተብለዋል።  በዘገባው መሰረት ረሐብ በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ "እጅግ አሳሳቢ" ከሚባልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በዘገባው በተሰጣት ነጥብ ግጭት አለቅሽ ያላት አገር ከሰባት አመታት በፊት ከነበረችበት ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ቻድ፤ ሴራ ሊዮን፤ማዳጋስካር እና ዛምቢያ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክን ይከተላሉ። 

የረሐብ አመልካቹ በኦመታዊ ዘገባው የዳሰሳቸው 119 አገሮች ብርቱ፣አሳሳቢ እና እጅግ አሳሳቢ ረሐብ ያለባቸው ናቸው። ቤልት ሑንገር ሒልፈ የተባለው የጀርመን የግብረ-ሰናይ ድርት ኃላፊ ባርብል ዲክማን እንደሚሉት የአየር ጠባይ ለውጥ፤ግጭት እና ጦርነት ረሐብን የመግታቱን ጥረት ወደ ኋላ እየጎተቱት ነው።

"በ50 በመቶ የተሻሻሉ 14 አገሮች አሉ። ይሁንና በግችት፤ጦርነት እና በአፍሪቃ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ሁኔታዎች እየተባባሱ መሔዳቸውም እውነት ነው።"

ረሐብ ሊያገግምባቸው ይችላል ተብለው የሚጠረጠሩት ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ በመረጃ እጦት ምክንያት በዚህ ዘገባ ውስጥ አልተካተቱም። 

በዚህ ዓመት መጀመሪያ በረሐብ የተመታችው ደቡብ ሱዳን ዳግም ልትራብ ትችላለች የሚል ሥጋት አጥልቶባታል። በበርካታ አገሮች ከጎርጎሮሳዊው 2000 ዓ.ም. ጀምሮ ረሐብ ቢቀንስም በሁሉም የአገሮቹ አካባቢዎች ግን አይደለም። ባርብል ዲክማን ለዚህ ናይጄሪያ ጥሩ ማሳያ ነች ይላሉ።

"175 ሚሊዮን ሰዎች የሚኖሩባት ናይጄሪያ የተቃርኖው ማሳያ ጥሩ ምሳሌ ነች። በሰሜን ናይጄሪያ የቦኮ ሐራም ግጭት በፈጠረው ችግር ምክንያት 4.5 ሚሊዮን ዜጎች ለረሐብ እጅጉን ተጋላጭ ናቸው።"

 የዳሰሳ ጥናቱ ሰኔጋል፣ አዘርባጃን፣ ፔሩ፣ ፓናማ፣ ብራዚል እና ቻይናን ጨምሮ 14 አገሮች ባለፉት ሰባት አመታት ረሐብን በመቀነሱ ረገት ትርጉም ያለው ለውጥ አምጥተዋል ሲል አትቷል። በዘገባው መሰረት ሴቶች፣ሕፃናት እና ህዳጣን ሕዝቦች ከሌላው በባሰ የረሐብ ሥጋት የሚጫናቸው ናቸው። 

"የእኩልነት መጓደል ዘርፈ-ብዙ ነው። ሴቶች ብዙ ጊዜ እኩልነታቸው አልተረጋገጠም። ሁሉም ጎሳዎችም እኩል አይታዩም። ለምሳሌ በሕንድ የተትረፈረፈ ሐብት እና ብዙ ቢሊየነሮች ቢኖሩም፣ 200 ሚሊዮን ሰዎች ተርበዋል።"

እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ