1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ በቀጣይ የልማት ሂደት

ረቡዕ፣ ጥር 18 2003

የአፍሪቃ ኤኮኖሚ በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ተጽዕኖ ሳቢያ ፈታኝ ሁኔታ ቢገጥመውም ችግሩን እንደምንም ተቋቁሞ በወቅቱ በዕድገት አቅጣጫ ማምራቱን ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/Qvdd
ምስል DW-TV

ይህም የውጭ መዋዕለ-ነዋይን ይበልጥ የመሳቡን ዕድል እያጠነከረ በመሄድ ላይ ነው። በቅርቡ ኢትዮጵያን ጎብኝተው የተመለሱት የጀርመኑ የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ዲርክ ኒብል ለምሳሌ “አንበሣማ መንግሥታት” ሲሉ ስለ ብዙ የአፍሪቃ ሃገራት የዕድገት እመርታ በአድናቆት ተናግረዋል። ከነገ ይልቅ ዛሬ በክፍለ-ዓለሚቱ መዋዕለ-ነዋይ ማድረግ ጠቃሚ እንደሆነም ነው የመከሩት።
እርግጥ አፍሪቃ ውስጥ የሚታየው ዕድገት ከቦታ ቦታ የሚለያይ ሲሆን ባለፈው አሠርተ-ዓመት የተመዘገበው የኤኮኖሚ ዕርምጃ ወደ ማሕበራዊ ዕድገት በመለወጥ ድህነትን በመቀነሱ ረገድ ያደረገው አስተዋጽኦ ያን ያህል አይደለም። በጎ አስተተዳደር፣ የሲቪሉ ሕብረተሰብ ተሳትፎና የነጻው ኤኮኖሚ ዘርፍ መስፋፋት ዛሬም የሚገባውን ያህል ትኩረት ያልተሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው።

አፍሪቃ ውስጥ በፖለቲካ ረገድ ብዙ በጎ ነገር መከናወኑን መናገሩ አዳጋች ቢሆንም በኤኮኖሚው መስክ ግን ባለፉት ዓመታት ከቦታ ቦታ ጉልህ ስኬት መታየቱ አልቀረም። ለምሳሌ የቴሌኮሙኒኬሺኑ መስክ ነጻ ሆኖ መስፋፋት በርካታ የመዋዕለ-ነዋይ አቅራቢዎችን ለመሳብ በቅቷል። የምጣኔ-ሐብት ጠበብት እንደሚያስረዱት የወቅቱ የዕድገት ሂደት እርግጥ ከአገር ወደ አገር የተለያየ ነው። ቢሆንም አጠቃላዩን ዕርምጃው ተሥፋ ሰጭ አድርገው ይመለከቱታል።
መለስ ብሎ ለማስታወስ አንዳንዶቹ የአፍሪቃ አገሮች ገና ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ከመከሰቱ በፊት ከሚደነቅ ከፍተኛ ዕድገት ላይ ለመድረስ ችለው ነበር። ከዚሁ ሌላ የፊናንሱ ቀውስ በክፍለ-ዓለሚቱ ላይ ያሳደረው ቀጥተኛ ተጽዕኖ ቀደም ሲል የተፈራውን ያህል የከፋ አልሆነም። እናም ዕድገቱ ይቀጥላል ማለት ነው። ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም IMF የሚገምተው የአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም የኤኮኖሚ ዕድገት በዚህ በያዝነው በጎርጎሮሣውያኑ 2011 ዓ.ም. በአማካይ አምሥት ከመቶ እንደሚሆን ነው።
ለንጽጽር ያህል በበለጸገው ዓለም ለምሳሌ በጀርመን በተመሳሳይ ጊዜ ሁለት ከመቶ የሚሆን ዕድገት ነው የሚጠበቀው። የተቀሩት ምዕራባውያን ሀገራት ዕድገት እንዲያውም ከሁለት በመቶ በታች ነው። ታዲያ የአፍሪቃ ዕርምጃ በአንጻሩ የጠነከረ ቢሆንም በአሕጽሮት DEG በመባል የሚታወቀው የጀርመን የመዋዕለ-ነዋይና የልማት ተቋም የረጅም ጊዜ ባልደረባና ደራሲ ቪንፍሪድ ፖልተ የአፍሪቃ ዕድገት አስተዋጽኦ ከወዲሁ ተጋኖ መታየት የለበትም ባይ ናቸው።

“አፍሪቃ ውስጥ እንዳንድ በመጠኑ ሰፊ የሆነ የተፈጥሮ ሃብት ያላቸው አገሮች እንዳሉ እናውቃለን። ይሄው የተፈጥሮ ሃብት ደግሞ ባለፉት ዓመታት ከመቼውም ይበልጥ በጣሙን ተፈላጊ ነበር። እናም ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርት አንጻር እነዚህ አገሮች ታላቅ ዕርምጃ ነው ያደረጉት። ግን ዕድገትን ስንተምን የምንነሣው በጣም ዝቅተኛ ከሆነው የኤኮኖሚው መሠረት ነው። እናም ይሄው ሃቅ ድርሻውን የዚያኑ ያህል አነስተኛ ያደርገዋል”

ቪንፍሪድ ፖልተ እንደሚሉት ከዚሁ በተጨማሪም በአፍሪቃ ከፍተኛ የሆነው የሕዝብ ቁጥር ዕድገትና አብዛኛው ድሃ የሆነ ሕዝብም በአገሩ የአዲሱ ጸጋ ተካፋይ ለመሆን አለመቻል ዓቢይት ችግሮች ናቸው። የሆነው ሆኖ አፍሪቃ ለጊዜውም ቢሆን ይበልጡን በጥሬ ሃብቷ ላይ ጥገኛ ሆና በመቀጠሏ የኤኮኖሚ ጠበብት ይስማማሉ። እርግጥ ጊዜው ሌሎች ዘርፎችም በኤኮኖሚው ዕድገት ላይ ጠቃሚ ድርሻ ሲኖራቸው የሚታይበት መሆኑ አልቀረም። ለምሳሌ የሞባይል ስልክና የባንኩ ዘርፎች ወይም የኤነርጂው መስክ ዛሬ ብዙ የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶችን በመሳብ ላይ ናቸው። የጀርመን ምጣኔ-ሐብት ዘርፍ የአፍሪቃ ማሕበር አፈ-ቀላጤ ሚሻኤል ሞነርያህን እንደሚያስረዱት በአፍሪቃውያን መንግሥታት መካከል የሚካሄደው ንግድም እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው።

“አፍሪቃ ውስጥ አንዳንድ በታላቅ ግብ ላይ ያለሙ የኤኮኖሚ ማሕበረሰቦች አሉ። ከነዚሁ መካከል ለምሳሌ የምሥራቅ አፍሪቃው ማሕበረሰብ EAC ወይም የደቡባዊው አፍሪቃ የልማት ማሕበረሰብ SADC ይገኙበታል። እነዚሁ በከፊል ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ የሚያስከፍሉትን ቀረጥ በሰፊው በመቀነስ ለንግዱ የሚበጅ ጠቃሚ ሁኔታን አመቻችተዋል። እናም በነዚህ ተራማጅ በሆኑት ማሕበረሰቦች ውስጥ የአካባቢው ውስጣዊ ንግድ እንደሚዳብር ዕምነታችን ነው። ይህ ለአካባቢው ኢንዱስትሪዎች ዕድገትም የሚጠቅም ሲሆን ወደፊት አፍሪቃ ወደ ሌላ ክፍለ-ዓለማት በምትሸጠው ጥሬ ዕቃ ላይ ያለባትን ጥገኝነትም የሚቀንስ ነው የሚሆነው”

ሞነርያህን አክለው እንደሚያስረዱት በዚህ ሂደት እርግጥ ጥሬ ሃብትና ጥሩ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ያላቸው የአፍሪቃ ሃገራት ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ጠቃሚ ዕርምጃ ሊያደርጉ ይችላሉ። ለምሳሌ ጋናን ብንወስድ የሕዝቧ አንድ ክፍል ከአሁኑ የመንግሥቱ የምጣኔ-ሐብት መርህ ተጠቃሚ እየሆነ ነው። በቦትሱዋናና በአንዳንድ መሰል አገሮች ደግሞ የመግዛት አቅሙ እየጨመረ የሚሄድ መካከለኛ የሕብረተሰብ ክፍል በማደግ ላይ መሆኑ ይታያል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንግዲህ ለውጭ ምርትም በአፍሪቃ ማራኪ ገበያ ሊስፋፋ ይችላል ማለት ነው።

የውጭውን ዓለም የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች በተመለከተ በፍጆት ዕቃዎችና በአጠቃላይ በንግድ ረገድ አፍሪቃ ውስጥ ለመሰማራት የሚያቅዱት ኩባንያዎች ቁጥር ገና ከዛሬው እየጨመረ ሲሄድ ይገኛል። ከዚሁ ተያይዞ በአፍሪቃውያኑ መንግሥታት ዘንድም የኤኮኖሚ አቋም ለውጥ መታየቱ አልቀረም፤ የጀርመኑ የኤኮኖሚ ዘርፍ የአፍሪቃ ማሕበር ባልደረባ እንደሚሉት!

“እነዚህ መንግሥታት ጥንቁቅ እንበል ወግ አጥባቂ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ ነው። በረጅም ጊዜ ትርፍ ማግኘት የሚቻልበትን ሁኔታ በሚያረጋግጥ መንገድም ጥሬ ሃብትን ያከማቻሉ። ከዚህ አንጻር የኤኮኖሚው ፖሊሲ በሚቀጥሉት ዓመታት የተረጋጋ ሆኖ እንደሚቀጥልና እንዲያውም የመሻሻል ሂደት እንደሚታይበት ነው የምናምነው። ለመንግሥታቱ መሪዎች ጠቃሚው ነገር ተጨማሪ የልማት ዕርዳታ ገንዘብ ማግኘቱ ሣይሆን ለኩባንያዎች ወይም ለግሉ መወዕለ-ነዋይ አመቺ ሁኔታ መፍጠሩ እንደሆነ ይበልጥ ግልጽ ሆኗል”

ይህ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎችና በስፍራው የሚገኙት መሰሎቻቸውም የበለጠ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይበልጥ የሚያደፋፍር ሂደት ነው። ከነዚሁ ሁኔታዎች መካከል ደግሞ አንዱና ምናልባትም ዋነኛው የፖለቲካ መረጋጋት ይሆናል። በጥቅሉ ሲታይ የክፍለ-ዓለሚቱ ጦርነቶችና ውዝግቦች ባለፉት ሰላሣ ዓመታት ውስጥ በሰፊው ቀንሰዋል። ይሁንና ሂደቱን በጥርጣሬ ዓይን የሚመለከቱት የጀርመን የመዋዕለ-ነዋይና የልማት ተቋም ባልደረባ ፖልተ እንደሚሉት በብዙ አገሮች ዛሬም ሁኔታው ከእርጋታ ርቆ እንደቀጠለ ነው።

“ይህ የሚያሳዝን ሆኖ በብዙዎች የአፍሪቃ አገሮች አጠቃላይ ብሄራዊ ጥቅምን ዒላማው ያደረገ ጤናማና አስተማማኝ ፖለቲካ መጉደሉ የሚከሰትበት አንዱ ማዕከላዊ ችግር ነው። ስለዚህም አሁን ከቀውሱ በኋላ ለታዳጊ አገሮች የተገኘውን ጥሩ ዕድል ሙሉ በሙሉ መጠቀሙ የማይቻል ነገር ይሆናል”

ሌላው ቀርቶ በዕድገትና በፖለቲካ ለውጥ በአርያነት የሚታዩት አገሮች እንኳ ድንገት ሳይታሰብ ቀውስ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ። ይህ ደግሞ በሕብረተሰብና በኤኮኖሚ ላይ የሚያስከትለው ችግር ቀላል አይሆንም። ኬንያን እንደ ምሳሌ ብንወስድ ከሶሥት ዓመታት በፊት የአገሪቱን ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ተከትሎ ከባድ ዓመጽ መስፈኑ ይታወሣል። በዚሁ ሳቢያ ታዲያ የአገሪቱ ብሄራዊ ኤኮኖሚ በ 2,2 ከመቶ መጠን ነበር በጊዜው ያቆለቆለው። ከዚህ ልምድ አንጻር በአፍሪቃ በያዝነው አዲስ ዓመትም የሚጠበቀውን የዕድገት ሂደት ቀጣይ ለማድረግ የፖለቲካው ዕርጋታ አማራጭ የሌለው ቅድመ-ግዴታ ይሆናል። አለበለዚያ የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶችን መሳቡ ከባድ ነገር ሆኖ ነው የሚቀጥለው።

ለጊዜው ቢቀር በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚገኙት የአፍሪቃ አገሮች የውጭ ባለሃብቶችን በመማረክ ላይ ናቸው። የተፋጠነው ዕድገት የሚጠይቀው የሥራ ሃይል ወይም ጉልበት በብቃት ሲኖር ከሣሃራ በስተደቡብ የአፍሪቃ አገሮች ምርታማነት እየጨመረ መሄዱም ይጠቀሳል። በመሆኑም የማክ-ኪንዚይ ተቋም ሃላፊ ሚሻኤል ክሎስ ለምሳሌ ከፖለቲካ መረጋጋት ጋር ለአፍሪቃ ትልቅ ዕድል ነው የሚታያቸው።

“ዕድሉ ትልቅ የሚሆነው የንግዱ መጠን አፍሪቃ ውስጥ ሰፊ በመሆኑና ክፍለ-ዓለሚቱም በዕድገት ላይ በመገኘቷ ነው። ግዙፉ ጥሬ ሃብት፣ በአፍላው ላይ የሚገኘው መዋቅራዊ ግንባታና የእርሻ ልማት፤ እነዚህ ሁሉ የወደፊቱ ማተኮሪያዎች ናቸው”

ይህን መሰሉ መንገድ ከተከፈተባቸው አገሮች መካከል ለምሳሌ በወቅቱ ሩዋንዳ ትገኝበታለች። የአገሪቱ ዓመታዊ ዕድገት በዘጠናኛዎቹ ዓመታት 0,4 ከመቶ ቢጠጋ ነበር። የእርስበርስ ጦርነቱ ካበቃ ወዲህ በአዲሱ ምዕተ-ዓመት ግን በያመቱ 7,3 በመቶ የተፋጠነ ዕድገት እየተደረገ ነው። የኤኮኖሚው ዕድገት ወደ ማሕበራዊ ልማት ሊለወጥ ከቻለ ወደፊት ጠቃሚ አርያነት ይኖረዋል።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ