1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ፤ የኑሮ ውድነትና የድህነቱ ማየል

ረቡዕ፣ ነሐሴ 7 2000

በዓለም ላይ የምግብ ዋጋ ከመጠን በላይ እየናረ መሄድ በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠር ሕዝብ ፈታኝ ጉዳይ መሆኑን ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/EwVV
የዋጋ ንረትና የሕዝብ ተቃውሞ በግብጽ
የዋጋ ንረትና የሕዝብ ተቃውሞ በግብጽምስል picture-alliance/ dpa

በተለይ በታዳጊው ዓለም ሙስና፣ የልማት እጦትና የአስተዳደር ጉድለት ታክሎበት ሁኔታው ሲባባስና አደገኛ የሆነ አዝማሚያ ሲይዝ ነው የሚታየው። ድርቅና ረሃብም እንዲሁ ለችግሩ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉ አልቀረም።

በአፍሪቃ ጥቂትም ቢሆን የመግዛት አቅሙ ሻል ያለው ለዚያውም ካለ በቁጥሩ ዝቅተኛ የሆነው መካከለኛ የሕብረተሰብ መደብ ይብሱን እየመነመነ በመሄድ ላይ ነው። በእጣት የሚቆጠሩት ከመጠን በላይ ይካብታሉ፤ የከፋ ድህነት የተጠናወተው አብዛኛው ድሃ ሕዝብ ግን ይበልጥ እየተበራከተ ይገኛል። ይሄው ያስከተለው የማሕበራዊው ሰላም ዝቤት በያለበት ሕብረተሰብን የሚያናውጽ የቁጣ ማዕበልን እንዳያዛምት የሚሰጉት ታዛቢዎች ጥቂቶች አይደሉም።

የምግብና የነዳጅ ዋጋ ከመጠን በላይ እየናረ መሄድ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዓለም ኤኮኖሚ ላይ የከፋ የቀውስ አደጋን የደቀነና በተለይም በታዳጊው ዓለም ከዕጅ ወደ አፍ የሆነች ኑሮ የሚገፋውን ምልዓተ-ሕዝብ የሕልውና ትርጉም አሳጥቶ ነው የሚገኘው። ከሚሊያርድ የማያንስ የምድራችን ሕዝብ ከአንዲት ዶላር ባነሰች የቀን ገቢ በሚኖርበት በደቡቡ ዓለም፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአፍሪቃ ዛሬ በቀን ከአንዴ በላይ የሚቀመስ ማግኘቱ ለብዙዎች የማይቻል ነገር እየሆነ ሄዷል። የረሃብ አዙሪት ጊዜውን ጠብቆ እንደገና ብቅ ብሏል፤ የከፋ ጉስቁልና ነው የሚታየው።

ለነገሩ አፍሪቃ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ከዓለም ባንክ ባለሥልጣን እስከ ሌሎች ዓለምአቀፍ ባለሙያዎች ድረስ ብዙዎች ደግመው ደጋግመው እንደሚናገሩት ያለማቁዋረጥ የኤኮኖሚ ዕድገት እያደረገች ነው የመጣችው። ይህ የብዙዎቹ ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኙ አገሮች ሃቅ ነው። ይሁንና ታየ በተባለው ዕድገት የሕዝብ የኑሮ ሁኔታ እምብዛም መሻሻል ወደሚንጸባረቅበት ማሕበራዊ ልማት ተቀይሯል ለማለት አያስደፍርም። የዜጎች የምግብ ዋስትና አልተረጋገጠም። ዛሬም እንደ ትናንቱ ጥቂት ተፈጥሮ በተቆጣ ቁጥር ሁሉ የውጭ ዕርዳታ መለመኑ ባለበት ቀጥሏል። ይህ በወቅቱ በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢም የምንታዘበው ነው።

የተፈጥሮን ቁጣ ካነሣን ለመሆኑ ለአፍሪቃ የረሃብ አዙሪትና በተመጽዋችነት ላይ የሙጥኝ ማለት መሠረታዊ መንስዔው የዝናብ እጦት ወይም የጎርፍ መከሰት ነወይ? እርግጥ በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ በሚገኙት በነዚህ አገሮች ይህን መሰሉ ሁኔታ የሚያስከትለው ችግር ቀላል አይደለም። ሆኖም ግን ለአጠቃላዩ ቀውስና ለብዙሃኑ ለድህነት መጋለጥ ዋናው ምክንያት አይደለም። የብዙሃኑን አርሶ-አደር ሕዝብ የማምረት ፍላጎት በመሬት ባለቤትነትና አግባብ ባለው የገበያ ተጠቃሚነት ለማዳበር የተደረገው ጥቂት ነው። ጨርሶ ያልተሞከረበትም ቦታ አለ። በመሆኑም ትርፉ ዛሬ የባሰ መከራ፣ ብሶትና ምሬት ሆኗል። የምግብ ዋጋ መናር በአደባባይ የሕዝብን ቁጣ ከቀሰቀሰባችው የአፍሪቃ አገሮች አንዷ ግብጽ ናት። ከግል ታታሪው እስከ ዝቅተኛው የመንግሥት ተቀጣሪ የዕለት ኑሮውን መግፋት እየተሳነው የሄደው ዜጋ ብዙ ነው። በመንግሥት ላይ ያለው ቁጣም በዚያው መጠን እየጨመረ መሄዱን ቀጥሏል።

“ዋጋው እሣት እየሆነ ነው። ግን ማንም የሚረዳን የለም። ቤንዚን በወቅቱ ከመጠን በላይ ከመወደዱ የተነሣ ጠቅላላ ገቢያችንን ለሱው እንድናፈስ አድርጎናል”

ይህ የአንድ ታክሲ ዘዋሪ ብሶት የብዙዎች ዜጎችንም ምሬት የሚያንጸባርቅ ነው። አንድ ሊትር ቤንዚን በወቅቱ 130 ኪሪሽ፤ ማለት በአውሮ 25 ሣንቲም ገደማ ያወጣል። በዚህ የነዋሪው ገቢ ከፍተኛ በሆነበት በአዉሮፓ ቢሆን ኖር ይህ እንደ ሽልማት ወይም ስጦታ በተቆጠረ ነበር። ግን ግብጽን በመሰለ ከነዋሪው ግማሹ በቀን ከሁለት ኤውሮ የበለጠ ገቢ በማያገኝባት አገር 25 ሣንቲም ብዙ ገንዘብ ነው። የአንጋፋ ዕድሜ የእንክብካቤ ዋስትናና ፍቱን የሆና የጤና ጥበቃ ስርዓት በሌለባት አገር እያንዳንዷ ሣንቲም ትልቅ ክብደት አላት። ስለሆነም እንደ ታክሲ ዘዋሪው እንደ አሊ የመሰሉ አምሥትና ስድሥት ልጆች መቀለብ ያለባችው ዜጎች ኑሯቸው እንዴት ሊቀጥል እንደሚችል ግራ ገብቷቸው ነው የሚገኙት።

“በሁኔታው እጅግ ተወጥሬ ነው የምገኘው። 55 ዓመቴ ነው። እስከመቼ እንዲህ እየሰራሁ ልቀጥል እችላለሁ? መኪናዬን ሙሉ ቤንዚን ብሞላ ምናልባት መቶ የግብጽ ፓውንድ ላገኝ እችላለሁ። ግን ይህ ለቤት ኪራይና ለኤሌክትሪክ ይፈሣል። ከዚያም በተጨማሪ ግብር መክፈል አለብኝ። እና ምን ሊተርፈኝ ይችላል”

የግብጽ መንግሥት የተራ ቤንዚን ዋጋን በሩብ ያህል ከፍ አድርጓል። ፕሬዚደንት ሆስኒ ሙባራክ ከዚሁ የሚገኘውን ተጨማሪ ግብር በቅርቡ 80ኛ ዓመት ልደታቸውን ሲያከብሩ ግዙፍ ሆኖም ፍቱን ላልሆነው የመንግሥት ተቁዋም ተቀጣሪዎቻቸው ሰፊ የደሞዝ ጭማሪ ለማድረግ ሊጠቀሙበት ነው የሚያስቡት። በዚሁ የጃጀ አገዛዛቸውን ዕድሜ ለማራዘም እንደሚችሉ ያምናሉ። ሆኖም ከኑሮው ውድነት መባባስ መቀጠል አንጻር ሃሣባቸው ፍሬ መስጠቱ የሚያጠራጥር ነው።

ዛሬ አብዛኛው ግብጻዊ ዜጋ ከሚያገኘው ገንዘብ ያወጣውን አውጥቶ የሚተርፈው ነገር የለውም። ከገቢው ሲሶው በቤንዚንና በአውቶቡስ ቲኬት ያልቃል። ግዙፉ ሁለት ሶሥተኛው ደግሞ የሚፈሰው ለምግብ ነው። ሃያ በመቶ የሚሆነው የዋጋ ንረት ሰፊውን የሕብረተሰብ ክፍል የሕልውና መሠረት እያሳጣ ሲሆን ለዚያውም በሁለት እግሩ ያልቆመውን ማሐራዊ ሰላም ጨርሶ ሊያፋልስ የሚችል ነው። የግብጽ ገዢዎች የአገሪቱ ነጻ የማሕበራዊ ጉዳይ ጥናት ኢንስቲቲቱት ባልደረባ ጣሄር አሊ እንደሚሉት ሊፈነዳ የሚቃጣው እያበጠ የሚሄድ የሕዝብ ቁጣ ተደቅኖባቸው ነው የሚገኘው።

“የችግሩ አንዱ ምልክት የመሃከለኛው የሕረተሰብ ክፍል መፈረካከስ ነው። ይሄው የሕብረተሰብ መደብ በሰፊው የግብጽ ድሃ ሕዝብና በጥቂቶቹ ሃያል ሃብታሞች መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ ነበር የቆየው። ግን አሁን እየጠፋ ነው”

ብዙ ብትጨናነቅም በሰብዓዊነት ገጽታዋ ስትኮራ የቆየችው ዋና ከተማይቱ ካይሮ ዛሬ በዓለምአቀፉ የምግብ ዋጋ ንረትና የኤነርጂ ቀውስ ሳቢያ ጭካኔ የሰፈረባት ሆናለች። ሞቶ የወደቀ ሰው እንኳ ከምንም አይቆጠርባትም። አላፊ-አግዳሚው እንዳላየ አይቶ የሚያልፍባት መሆን ከያዘች ሰንበት ብላለች’። ሁኔታው የማሕበራውን ጉዳይ ባለሚያ ጣሄር አሊን እንኳ ማስደንገጡ አልቀረም።

“እንዲህ ዓይነቱ ነገር ከዚህ ቀደም አይቼው የማላውቀው ነው። ይህ ግድ የለሽነት በመሠረቱ የግብጻውያንን ባሕርይ የሚያንጸባርቅ አይደለም። ግን ጊዜው ሁሉም ለራሱ ብቻ የሚያስብበት ከባድ እየሆነ ሄዷል። ፖሊስ ቢጠራም ትርፉ ችግር ላይ መውደቅ ነው። ለዚህም ነው ሰዉ ሌላው አይመለከተኝም፤ የራሴ ጉዳይ ብቻ ማለት የጀመረው”

የግብጽ መንግሥት ሕዝቡን ለአያሌ ዓመታት ጸጥ አሰኝቶ መግዛቱ ሆኖለታል። በአንድ በኩል ፕሬዚደንቱን መቃወም የሞከሩትን በመጨቆንና ለረጅም ጊዜ ወህኒቤት በመጣል፤ በሌላም በድጎማ ፖሊሲ የሥልጣን መዋቅሩን ሚዛን ጠብቆ በማራመድ! የዳቦ፣ የቤንዚንና የናፍታ ዋጋን ዝቅ አድርጎ ለማቆየት በሚሊያርድ ዶላር የሚገመት ድጎማ ፈሷል። ይሁን እንጂ ይህ በተለመደ መልኩ ለመቀጠሉ አስተማማኝ ዋስትና የለም። የወቅቱ ዓለምአቀፍ የዋጋ ንረት የመንግሥቱን የእስካሁን የፖለቲካ ስሌት የሚያዛባ ብርቱ አደጋ ነው የደቀነው።

የምግብና የኤነርጂ ዋጋ ንረት በደቡብ አፍሪቃም በቅርቡ ሁለት ሚሊዮን ለሚሆን ሕዝብ የአደባባይ ተቃውሞ መንስዔ ሆኖ ነበር። ተቃውሞውን የጠራው ደግሞ በአሕጽሮት ኮሣቱ በመባል የሚታወቀው ታላቁ የአገሪቱ የሙያ ማሕበር ነው። ኮሣቱ የአፍሪቃ ብሄራዊ ሸንጎ የ ANC ሕብረት አንድ አካል ሲሆን እንበል በራሱ መንግሥት ላይ መነሣቱ የነገሩን ክብደት ግልጽ ያደርገዋል። ሃያ ሚሊዮን ያህል ሕዝብ በከባድ ችግር ተጠምዶ ነው የሚኖረው። ይህም ሆኖ ግን የፕሬቶሪያ መንግሥት ችግሩን ለመቁዋቁዋም አንዳች ነገር አላደረገም ሲሉ የሚወቅሱት ብዙዎች ናችው። ከተቃዊሚዎቹ አንዱ ሣሚ ሞሼዊ!

“ችግሩን እንዴት መፍታት እንደሚችሉ ማሰብ ይኖርባችዋል። አደባባይ የወጣነው ለመዝናናት አይደለም። ተቃውሟችን የምር ነው። መንግሥት ነገሩን ችላ ካለ በዚምባብዌ አቅጣጫ ማምራታችን አይቀርም። ስለዚህም የዋጋውን ንረት መግታትና ሁሉንም ነገር መለወጥ አለባቸው”

በደቡብ አፍሪቃ የሰንጥረዥ ቢሮ የወጣ የቅርብ መረጃ እንደሚያመለክተው የዕሕል ምርቶች ዋጋ ከዓመቱ መጀመሪያ ወዲህ ሰላሣ ከመቶ ጨምሯል። የምግብ ምርት በአጠቃላይ 21 በመቶ ነው ወደ ላይ የተተኮሰው። የነዳጅ ዘይት ዋጋ ደግሞ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ በእጥፍ ሲያድግ ኤሌክትሪክ 28 በመቶ፤ እንዲሁም የምግብ ማብሰያ ዘይትና ቅቤ 63 በመቶ ንሯል። የብዙሃኑ የአፍሪቃ አገሮች ሁኔታ ከዚህ ከደቡብ አፍሪቃም ሆነ ከግብጽ ሃቅ አይለይም።

ዓለምአቀፉ ሕብረተሰብ ቀደም ሲል በዋጋው ንረት ሳቢያ ይበልጥ ለተጎዱት አገሮች አስቸኳይ ዕርዳታ በማቅረብ ችግሩን ለማለዘብ ሲነሣ ዕርዳታው ቀስ በቀስ መንጠባጠብ መጀመሩም አልቀረም። ይሁንና የተባለው ልገሣ ምናልባት ሕሊናን ከማረጋጋት አልፎ ችግሩን ከመሠረቱ ለማስወገድ የሚረባ እንደማይሆን ሲበዛ ግልጽ ነው። የአፍሪቃን ቀንድ አካባቢ አገሮች እንደ ምሳሌ ብንወስድ በአምሥትና እሥር ዓመቱ የተለመደው የረሃብ አዙሪት ዛሬ እርግጥ ዓለምአቀፉ የምግብ እጥረትና የዋጋ ንረት ታክሎበት ቢባባስም ይሄው የኋለኛው በመሠረቱ በተደጋጋሚ ከአካባቢው እንደሚሰማው የችግሩ መንስዔ ሊሆን አይችልም።

ችግሩ ባለፉት ዓመታት ተገኘ የተባለውን የኤኮኖሚ ዕድገት ለራስ የምግብ ብቃትና ዋስትና፣ ለማሕበራዊ ልማት መጠቀም አለመቻሉ ነው። ችግሩ የመሬት ስሪት በማድረግ አርሶ-አደሩ የመሬቱ ባለቤት እንዲሆን አለመፈለጉ ላይ ነው። ችግሩ ሙስናን አለማስወገድ በአርቆ አስተዋይነት የክፉ ቀን ቀለብ ለማከማቸት አለመቻል ወይም አለመሻት ነው። ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ ውሎ አድሮ የሚወልደው የለየለት የሕዝብን የቁጣ ትሱናሚ ይሆናል።