1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ፤ ድህነትን ያልገታው የኤኮኖሚ ዕድገት

ሐሙስ፣ ጥቅምት 28 2000

አፍሪቃ ውስጥ ባለፉት አሥር ዓመታት ያልተቋረጠ የኤኮኖሚ ዕድገት መደረጉና ሂደቱ ቀጣይ እንደሆነም በያጋጣሚው ሲነገር ቆይቷል። ይሁን እንጂ በተለይ በአንዳንድ አገሮች ጎልቶ የታየው ዕድገት ብዙሃኑን ሕዝብ አላዳረሰም።

https://p.dw.com/p/E0cZ

የአፍሪቃ ድህነት በርከት ባሉ አገሮች የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ዕቅድ በተጣለለት የጊዜ ገደብ ወደ ሁለተኛ አጋማሹ በተሸጋገረበት በአሁኑ ወቅት እየጨመረ ሄዷል። የአፍሪቃ ልማትና ችግሮቹ በዚህ በቦን በተካሄደ ዓለምአቀፍ የልማት ጉባዔ ላይ ሰሞኑን ሲያነጋግር የሰነበተ ጉዳይ ነበር። ለነገሩ አፍሪቃ ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ የቀረቡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በማድግ ላይ ያለች ክፍለ-ዓለም ናት። ሆኖም እንደ ውስስብነቷና መለያየቷ ሁሉ ዕድገቷም አንድ ወጥ ሆኖ አይገኝ’ም።

የልማቱ ዕርምጃ ጠንከር ብሎ የሚታየው በጥቂት አገሮች፤ ለዚያውም በተወሰኑ ዘርፎች ብቻ ነው። በተለይ ድህነትን በመታገሉ ረገድ ግን የረባ መሻሻል ተደርጓል ለማለት አይቻልም። እንዲያውም ከድህነት መስፈርት በታች የሚኖረው ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መሄዱን ቀጥሏል። ችግሩ ምንድነው? ለምን ብዙሃኑ ተከሰተ የተባለው ዕድገት ተካፋይ ለመሆን አልቻሉም? በቦኑ ጉባዔ የተሳተፉት አፍሪቃዊት Equity Bank የተሰኘ የኬንያ መለስተኛ ብድር አቅራቢ ባንክ ባልደረባ ዊኒ-ካቱሪማ-ኢማንያራ እንደሚሉት ለዚሁ አንዱ ችግር ጊዜው ያለፈበት ቢሮክራሲ ነው።

“እርግጥ ነው ዕድገትን በተመለከተ፤ በኤኮኖሚ፣ በማሕበራዊ ኑሮ፣ በትምሕርትና ሌሎች መስኮችም ብዙ ምሳሌዎች ቀርበዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ጥሩና ፍቱን ዕርምጃዎች ብዙሃኑን የአፍሪቃን ሕዝብ አላዳረሱም። ይህ ለምን ሆነ? አንዱ ምክንያቱ ቢሮክራሲ ነው። እዚህ ላይ በተለይ ከባንክ አሠራር አንጻር ነው የምናገረው፤ በአጠቃላይ ጊዜው ካለፈበት የአሠራር ዘይቤ ለመላቀቅ አልተቻለም”

ኢማንያራ የኬንያን ምሳሌ መሠረት በማድረግ ዘርዝረው እንደሚያስረዱት ለምሳሌ ቁልፍ የሆኑት የንግድ ባንኮች በተለይ ሂሳብ መክፈትን በመሳሰለው ጉዳይ የሚደቅኑት ቅድመ-ግዴታ እጅግ የጠበቀ ነው። ግዴታውን ለማሟላት ብዙ ገንዘብ፤ ቼኮች ያለው ሰው መሆን ያስፈልጋል። አገሬው ድሃ ሕዝብ እንግዲህ ለዚህ አቅሙ የለውም ማለት ነው። ይህ ደግሞ የባንክ አገልግሎትን መጠቀሙን የተገደበ ያደርገዋል። ኤኩዊቲይ ባንክ ያደረገው በዝቅተኛው የሕብረተሰብ ክፍል ላይ ማተኮር፤ ፍላጎቱን በቅርብ ማጤን ነው።

ብዙሃኑ የአፍሪቃ ሕዝብ የሚገኝበት ሁኔታ በአጠቃላይ ይህን የመሰለ ነው። በተለይ የግል ባለሃብቶችን በመሳቡና ሰፊውን ሕዝብ የዕድገት ተጠቃሚ በማድረጉ በኩል ገና ብዙ ነው የሚቀረው። የኬንያው አበዳሪ ባንክ ባልደረባ የሚያሳስቡት መሰል የገንዘብ ተቋማትና ሌሎች ድርጅቶች የርሳችውን ባንክ አርአያ በመከተል በየመንደሩ ተመልሰው እንዲሰፍሩ፣ የሕዝቡን ፍላጎት እንዲያጤኑና መስለውትም እንዲኖሩ ነው። በሌላ በኩል አፍሪቃ ውስጥ እስካሁን ቀጥተኛ ዓለምአቀፍ መዋዕለ-ነዋይን መሳብ የተቻለው ጥቂት ነው። የተገኘውም የማዕድን ሃብት ባላቸው ጥቂት አገሮች ላይ አተኮረ እንጂ ብዙውን አላዳረሰም።
ሙስናና ቢሮክራሲ ለዚህ የራሳችው አስተዋጽኦ ሲኖራችው ለባለሃብቱ ዋስትና የሚሰጡ ፍቱን ወይም አስተማማኝ ደምቦች መጉደላቸውም ጉዳዩን ቀላል አያደርገውም። በሌላ በኩል አፍሪቃውያን መንግሥታት ገበዮቻቸውን ማራኪ በማድረጉ በኩል ተገቢውን ሁኔታ አመቻችተዋል ለማለት አይቻልም። ብዙ ቅስቀሣ፤ ብዙ የገበያ ጥረት መደረግ ይኖርበታል። ብዙዎቹ እነዚህ አገሮች የተፈጥሮ ሃብት የላቸውም። በአንጻሩ ኢማንያራ እንደሚሉት ለምሳሌ ቱሪዝምንና እርሻን የመሳሰሉትን መስኮች ብንመለከት ሰፊ ዕድል ነው ያለው። ኢማንያራ የውጭ ባለሃብቶችን አስመልክተው ሲናገሩ “አንድ ትልቅ ድርጅት ዛሬ ቱሪዝምን ለማዳበር ወይም ካፒታሉን በሥራ ላይ ለማዋል ወደ አፍሪቃ ቢመጣ ከማዕድኑ ዘርፍ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆን አልጠራጠርም። ምክንያቱንም አፍሪቃ ገና ከአሁኑ አብዛኛውን ገቢ የምታገኘው በቱሪዝም ነው። በእርሻው መስክም ባለሃብቶች ገንዘባቸውን በሥራ ላይ ቢያውሉ ብዙ ሊጠቀሙ ይችላሉ። ሆኖም የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች ይህን በሚገባ የተገነዘቡ አይመስለኝም። በአውሮፓ ወይም በሌላው የበለጸገ የዓለም ክፍል ተቀምጠው ከርቀት በሚቀርብላቸው መረጃ መመራት የለባቸውም። ቀጥተኛ ተሳትፎ መኖሩ ተገቢ ነው” ይላሉ።

በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም መዋዕለ ነዋይን ሥራ ላይ በማዋሉ ረገድ ቁጥብነትና ስጋቱ ይበልጥ ጎልቶ የሚታየው በጀርመናውያን ዘንድ ነው። ኬንያዊቱ የባንክ ባለሙያ በቦኑ የልማት ኮንፈረንስ አጋጣሚ ከጀርመን የኤኮኖሚ ዘርፍ ተጠሪዎች ተገናኝተው ሲወያዩ የአፍሪቃ ምስቅልቅል ታሪክም በሁኔታው ላይ አስተዋጽኦ አድርጓል ባይ ናቸው። “ችግሩን እረዳለሁ። የጀርመን ዝንባሌ በአጠቃላይና በተለይም የመንግሥቱ የኤኮኖሚ ዘርፍ ሲበዛ ቁጥብነት የተመላው ነው። ሁሉም ነገር ምን ችግር ሊኖረው እንደሚችል በቅድሚያ ነው የሚጤነው። አደጋው፣ የቁጥጥሩ ሁኔታ፣ ሂደቱ ትርፍ አለው የለውም፤ ለአጋጣሚ አይተውም። ይህም የጀርመን ባሕል በጠቅላላው በኤኮኖሚው ዘርፍ ውስጥ ሥር የሰደደ ነገር ይመስላል። በዚህ እርግጥ አንወቅሳቸውም። ምክንያቱም አፍሪቃን ስንመለከት የጦርነት፣ የበሽታ፣ የረሃብ፣ የሙስና ወዘተ. ነውና! በአጠቃላይ ጀርመን ሙስና፣ ሕገ-ወጥ የመሣሪያና ንግድና የመሳሰሉት ችግሮች ባሉበት ቦታዎች ገንዘብ ማፍሰስ አትፈልግም። ስሟን ለመጠበቅ ትፈልጋለች ብዬ አምናለሁ”

ሃቁ ያም ሆነ ይህ አፍሪቃ ባለፉት ዓመታት በተለይም በተፈጥሮ ሃብቷና ሌላም ስልታዊ ስሌት የምዕራቡን ዓለም ትኩረት እየሳበች መምጣቷ ነው። ቻይናንና ሕንድን የመሳሰሉት የእሢያ ግዙፎች ተጽዕኖ ማየልም ይበልጥ ተፈላጊ እያደረጋት ሄዷል። የአውሮፓ ሕብረት ለምሳሌ በወቅቱ በ ACP ውስጥ ከተሰባሰቡት ታዳጊ አገሮች ጋር የኤኮኖሚ ሽርክና ውል ለማስፈን እየጣረ ሲሆን ስምምነቱ ቢሰፍን ማነው ተጠቃሚ ማነው ተጎጂው ብዙ የሚያነጋግር ጉዳይ ነው። በጉዳዩ ለስምምነት የሚያበቃ ሁኔታ አለ ከሚለው አስተሳሰብ ባሻገር ድርድሩ ተጨማሪ ጊዜ ተሰጥቶት ሊቀጥል ይገባዋል የሚል ሌላ አመለካከትም መስፋፋቱ አልቀረም። እንደ ኬንያዊቱ የባንክ ባለሙያ እንደ ዊኒ ኢማንያራ ከሆነ ግን ሁሉም የአፍሪቃ አገር በአንዴ የውሉ አካል መሆን የለበትም።