1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪካዊ ሰላም አስከባሪ ኃይል

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 29 1998

በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ እየተባባሰ የመጣዉ ወታደራዊ ዉጥረት ያሳሰበዉ 53 አባል አገራት ያሉት የአፍሪካዉ ህብረት በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የጋራ ሰላም አስከባሪ ኃይል ባፋጣኝ ሊያደረጅ መሆኑ ተገለፀ።

https://p.dw.com/p/E0jN

ህብረቱ እዚህ ዉሳኔ ላይ እንዲደርስ የገፋዉ በተለይ በምስራቅ አፍሪካ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎች ያለቁበት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ተካሂዶ የነበረዉ ጦርነት ዳግም ይቀሰቀሳል ከሚል ስጋት ነዉ።
በምዕራባዉያን አገራት ድጋፍ የአፍሪካ ዝግጁ ሰራዊትን የማቋቋሙ ሃሳብ የቀረበዉ ጦርነት ባጠቃት የአፍሪካ አህጉር ወታደራዊና የሰላም ተልዕኮ እንዲያከናዉን ታስቦ ነዉ።
ዋሽንግተን የሚገኘዉ ትራንዝ አፍሪካ የተሰኘዉ መድረክ ፕሬዝደንት ቢል ፍሌትሸር እንደሚሉት በአፍሪካ ህብረት ስር የሚንቀሳቀስ አዲስ የሰላም አስከባሪ ጦር ባስቸኳይ የማቋቋሙ ነገር የሚያጠያይቅ አይደለም።
እንዲህ ያለዉን ኃይል ለማደራጀት ደግሞ የገንዘብም ሆነ የስንቅና ትጥቁ ድጋፍ የሚገኘዉ አፍሪካዊ ካልሆኑ አገራት በተለይም ከምዕራብ ነዉ እንደእሳቸዉ እምነት።
ይህን መሰሉን ድጋፍ ማድረግ ማለት ግን የሚደራጀዉን ኃይል ለፈለጉት ዓላማ በፈለጉት መንገድ የመጠቀም መብት ማግኘት ማለት እንዳልሆነ ያስጠነቅቃሉ ፍሌትሸር።
በሌላ አነጋገር ይላሉ የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ኃይል የአፍሪካ አገራትን ሉዓላዊነት ለመቀልበስ የሚያልሙ ድርጅቶችና አገራት ምኞት የሚያሟላ አዲስ የቅኝ አገዛዝ ስልት ማስፈፀሚያ አይሆንም።
አንድ አፍሪካዊ ዲፕሎማት ለIPS የዜና ወኪል እንደገለፁት የአፍሪካ ዝግጁ የጦር ኃይል ተቋቁሞ መንቀሳቀስ ከጀመረ ኢትዮጵያና ኤርትራን ጨምሮ ግጭት በሚታይባቸዉ በተለያዩ አገራት የተሰማራዉን የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ጦር ይተካል።
በአሁኑ ወቅት 16ቱ የመንግስታቱ የሰላም አስከባሪ ቡድን ከተሰማራባቸዉ አገራት መካከል ስምንቱ የሚገኙት በአፍሪካ ነዉ።
አገራቱም በሴራሊዮን፤ በዲሞክራቲክ ኮንጎ፤ ላይቤሪያ፤ ኮት ዴቩዋር፤ በኢትዮጵያና ኤርትራ፤ ቡሩንዲ፤ ሱዳን እንዲሁም በምዕራብ ሰሃራ ናቸዉ።
በኢትዮጵያና በኤርትራ የተሰማራዉ የመንግስታቱ የሰላም አስከባሪ ኃይል አዛዥ ጀነራል ራጂንደር ሲንግ በሁለቱ አገራት መካከል አዲስ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸዉ ባለፈዉ ሳምንት ገልፀዋል።
እንደሳቸዉ ስጋት ከሆነ እልባት ያላገኘዉና ተዳፍኖ የሚታየዉ በሁለቱ አገራት መካከል ያለዉ የድንበር ጥያቄ ከአምስት ዓመታት በኃላም እንደገና አዲስ ጦርነት ይጭራል።
ከሶስት ዓመታት በፊት በአፍሪካ ህብረት እንዲፈጠር ታስቦ የነበረዉ የአፍሪካ ዝግጁ ጦር ምስረታ ዓላማም የሰላም ተልዕኮን ለመደገፍ ብቻ ሳይሆን ይቀሰቀሳሉ ተብለዉ በሚሰጉ ግጭቶችም ጣልቃ እንዲገባ ታስቦ ነዉ።
ማንኛዉም የሚደረገዉ የጦር ጣልቃ ገብነት ግን በአፍሪካ ህብረት ጠቅላላ ጉባኤ ዉሳኔ መደገፍ ይኖርበታል።
ባለፈዉ መስከረም በተካሄደዉ የተባበሩት መንግስታት ጋዜጣዊ መግለጫ የአፍሪካ ዝግጁ ጦር በመጪዉ የፈርጆቹ ዓመት ዕዉን ይሆናል ብለዉ እንደሚጠብቁ የብሪታኒያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሊየር ገልፀዉ ነበር።
ዩናይትድ ስቴትስም ሆነች 25 አባል አገራት ያሉት የአዉሮፓዉ ህብረት በጥቅሉ መጠኑ ይፋ ያልሆነ ገንዘብ አዲስ ለሚገነባዉ የአፍሪካ ዝግጁ ጦር ድጋፍ ለመስጠት በወቅቱ ቃል ገብተዋል።
በሌላ በኩል የአፍሪካ ጉዳይ ፖሊስ ትንተናና የመገናኛ ዘዴዎች የተሰኘዉ ተቋም ዳይሬክተር አን-ሉዊስ ኮልጋን ጦሩን ለማደራጀት የሚደረገዉ ድጋፍ በዲፕሎማሲዉም ሆነ በሌላዉ ዘርፍ መሆን ይኖርበታል ይላሉ።
ጨምረዉ ሲያብራሩም በሱዳን ዳርፉር ግጭቱ እንደተቀሰቀሰ የአፍሪካ ህብረት የሰጠዉ ምላሽና ጠንካራ አመራር ገንቢ ቢሆንም እልቂቱን ብቻዉን ለማስቆም አቅም ማጣቱን ጠቅሰዋል።
ምዕራባዉያን አገራት የአፍሪካ ህብረትን በዚህ ረገድ በመደገፍ በዳርፉር የሚረግፈዉን የሰዉ ህይወት ለማዳን ቁርጠኞች ከሆኑ ዓለም ዓቀፍ ተቀባይነትና ስልጣን ባለዉ ኃይል የህብረቱን ጦር ሊያጠናክሩት ይገባል።
በአሁኑ ወቅት በዳርፉር የሚገኘዉ 6,000 የሚሆነዉ የአፍሪካ ህብረት ኃይል ታዛቢ እንጂ ሰላም አስከባሪ እንዳልሆነ የገለፁት ኮልጋን አዲስ የሚቋቋመዉ ዝግጁ ኃይል ህዝቡን ለመከላከል የሚችል የተጠናከረና ሙሉ ኃላፊነት የተሰጠዉ ሊሆን እንደሚገባዉ ጠቁመዋል።
በአፍሪካ በተለያዩ አገራት በዜጎች ላይ የሚፈፀመዉ ግድያ የአህጉሪቱ ችግር ብቻ ሳይሆን በሰዉ ህይወት ላይ የሚፈፀም ወንጀል በመሆኑ ዓለም ዓቀፍ ፍትህና ምላሽ የሚጠይቅ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
እንዳለመታደል ሆኖ ግን ይላሉ ዳይሬክተሯ በዚህ ረገድ የሚጠበቀዉ ዓለም ዓቀፍ ምላሽ በዳርፉርም ሆነ የህዝብ ሰላም እየደፈረሰ በሚታይባቸዉ አገራት ሁሉ እንደሚገባዉ ሲሰጥ አልታየም።