1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍቃኒስታን ሌላ ዘመን፤ አሮጌ ጦርነት

ሰኞ፣ ነሐሴ 22 2009

አስራ-ስድት ዓመታት  ባስቆጠረዉ ጦርነት ከ3400 በላይ የተባባሪዎቹ ሐገራት ወታደሮች ተገድለዋል።ሁለት ሺሕ ሁለት መቶ ሰባ-አንዱ ሟች ወታደር አሜሪካዊ ነዉ።22 ሺሕ የአፍቃኒስታን መንግስት ወታደሮች፤ ከ31 ሺሕ በላይ ሰላማዊ ሰዉ ተገድሏል።ከ25ሺሕ የሚበልጥ ሸማቂ ተገድሏል።

https://p.dw.com/p/2izO8
USA Fort Myer Trump Rede Afghanistan Strategie
ምስል picture-alliance/Pool via CNP/MediaPunch/M. Wilson

አፍቃኒስታን፤ ሌላ ዘመን፤ አሮጌ ጦርነት

 

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የሐገራቸዉ ጦር አፍቃኒስታን ዉስጥ የሚያደርገዉን ጦርነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታዉቀዋል።ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት አፍቃኒስታን የሠፈረዉን የአሜሪካ ጦር ለማስወጣት የገቡትን ቃል ሽረዉ አዲስ ባወጁት ሥልት ፓኪስታንንም ክፉኛ ወቅሰዋል። እጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ 20016።
                         
«አፍቃኒስታን ሙሉ በሙሉ ጥፋት ነዉ።ምንድነዉ እዚያ የምንሰራዉ።ከአፍቃኒስታን እንዉጣ።»
ደጋፊዎቻቸዉ አደነቁ፤ አጨበጨቡ፤ አፀደቁትም።
                    
ፕሬዝደንት ትራምፕ ባለፈዉ ሳምንት።

                 
«ከአፍቃኒስታንና አካባቢዉ የሚገጥመዉን የፀጥታ ሥጋት ከፍተኛ ነዉ።»አፍቃኒስታን፤-አስራ-ስድስት አመት ጦርነት።ዩናይትድ ስቴትስ ሰወስት ፕሬዝደንቶች።ሰወስተኛ ሥልት።ቀጥሎስ? አብረን እንጠይቅ።
                       
ቻይናዊዉ የፖለቲካ ፕሮፌሰር  ሺ ይንሆንግ እንደሚሉት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት በየጊዜዉ ስትራቴጂ (ሥልታቸዉን) ይቀያይራሉ።ሥልቱን የሚለዋዉጥ ፖለቲከኛ ደግሞ ሥልት የለዉም።
                              
«ትራምፕ ያላቸዉ አንድ ገፅታ፤ ከሐገር ዉስጥ በርካታ ፖለቲካዊ ፈተና የገጠማቸዉ መሆኑ ነዉ።ይሕ የዉጪ መርሐቸዉን ይጫነዋል።አንዳዴ የሐገር ዉስጡን የትኩረት አቅጣጫ እና የፖለቲካ ችግራር አቅጣጫ ለማስቀየር የዉጪዉ ጉዳዮች ፈጣን እርምጃ ይወስዳሉ።በሌላ በኩል ትራምፕ የኮሪያ ልሳነ ምድርን፤ መካከለኛዉ ምሥራቅ፤ አሁን ደግሞ አፍቃኒስታንን በሚመለከት የወሰዱት እርምጃ ባጠቃላይ ዓለም አቀፋዊ ወጥ ሥልት እንደሌላቸዉ አመልካች ነዉ።ሥልታቸዉን እና  ትኩረታቸዉን በየጊዜዉ ይቀያይራሉ።የዚሕ አንዱ ምክንያት ሥልት አዋቂ አለመሆናቸዉ ነዉ።ሌላዉ ሐገር ዉስጥ የሚገጥማቸዉ ፈተና የዉጪ መርሐቸዉን ክፉኛ መዘወሩ ነዉ።»
ትራምፕ አምና ይኸኔ ለፕሬዝደንትነት ሲወዳደሩ ሐገራቸዉ ማብቂያ ለሌለዉ ለመካከለኛዉ ምሥራቅ ጦርነት የከሰከሰችዉ ገንዘብን  ለራስዋ  ልማት አዉላዉ ቢሆን ኖሮ አሜሪካ አሁን ካለችበት በሁለት እጥፍ ትከብር ነበር ብለዉ ነበር።
                              
«አስቡት፤ የሚቃወሙን እነዚዉ ለመካከለኛዉ ምሥራቅ ጦርነት ስድስት ትሪሊዮን ዶላር ያጠፉት ሰዎች ናቸዉ።በዚሕ ገንዘብ ሐገራችንን በሁለት እጥፍ መገንባት እንችል ነበር።»
ሚሊዮኖች ደገፏቸዉ መረጧቸዉ።ዓመት ባልሞላ ጊዜ ግን ተቃዋሚዎቻቸዉን ባወገዙበት ጦርነት ቀጠሉ።ኢራቅ ቀዳሚዋ አብነት ናት።የኢራቅን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ሞስልን እራሱን እስላማዊ መንግስት (ISIS) ብሎ ከሚጠራዉ ቡድን ለማስለቀቅ በተደረገዉ ጦርነት ከግራም ከቀኝም ያለቀዉ አብዛኛዉ ኢራቃዊ ነዉ።

Afghanistan nach Anschlag auf Moschee in Kabul
ምስል Getty Images/AFP/S. Marai

ጠቅላይ ሚንስትር ሐይደር አል-አባዲ ከሳምንታት በፊት ሞሱል፤ ትናት ደግሞ ታል አፋር ላይ ድል ያደረገዉ ጦር ጠቅላይ አዛዥ በመሆናቸዉ የድል ነጋሪት ያስጎስሙ ይሆናል።ከኢራቅ መንግሥት ጦር ጋር አብረዉ  ISISን የሚወጉት የኢራን ሚሊሺያዎች፤ የኩርድ (ፔሽ ሜርጋ) ታጣቂዎች፤ የኢራቅ ሺዓ ሚሊሺያ አዛዦች ከአባዲ እኩል በድል አድራጊነት ይፈነድቁ፤ይኮሩ፤ይፎክሩ ይሆናል።   

ከISIS ጋር የሚዋጋዉን የኢራቅ መንግስትን ጦር የሚረዳ ተጨማሪ ጦር ያዘመቱት የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ለድሉ ባደረጉት አስተዋፅኦ ስማቸዉ ይጠቀስ ይሆናል።ትራምፕ ባለፈዉ ሳምንት እንደነገሩን ግን በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት የተቃወሙትን ጦርነት በድል ያጠናቀቁት እሳቸዉና ሥልታቸዉ ነዉ። 

                          
«በግምባር በሚዋጉት ላይ ያለዉን ገደብ ሥናነሳ እና ሥልጣን ሥንሰጣቸዉ አስገራሚ ዉጤት እንደሚገኝ ISISን ለማሸነፍ ባደረግነዉ ዘመቻ አይተናዋል።የኢራቅዋን ሞሱልን ነፃ ማዉጣቱ አንዱ ነዉ።»
ድል በርግጥ ባለቤትዋ ብዙ ነዉ።ሽንፈት ደግሞ ሰበቧ እጅግ ነዉ።ፕሬዝደንት ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት የተቃወሙትን ጦርነት ለመቀጠል የወሰኑበት ምክንያት ፕሬዝደንት ሲኮንና ፕሬዝደንት ለመሆን ሲፈለግ የሚባልና የሚደረገዉ የተለያየ መሆኑ አንዱ ነዉ።ዋናዉ ምክንያታቸዉ ግን በአፍቃኒስታኑ ጦርነት ተሸናፊ እንጂ አሸናፊ አለመኖሩ ነዉ።
ዩናይትድ ስቴትስና ተከታዮችዋ በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ጦራቸዉን አፍቃኒስታን ካዘመቱ ጥቅምት 16ተኛ ዓመታቸዉን ይደፍናሉ።አስራ-ስድት ዓመታት  ባስቆጠረዉ ጦርነት ከ3400 በላይ የተባባሪዎቹ ሐገራት ወታደሮች ተገድለዋል።ሁለት ሺሕ ሁለት መቶ ሰባ-አንዱ ሟች ወታደር አሜሪካዊ ነዉ።22 ሺሕ የአፍቃኒስታን መንግስት ወታደሮች፤ ከ31 ሺሕ በላይ ሰላማዊ ሰዉ ተገድሏል።ከ25ሺሕ የሚበልጥ ሸማቂ ተገድሏል።
ጥናቶች እንደሚጠቁሙት አንዲት ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ወደ ሁለት ትሪሊዮን የሚጠጋ ዶላር ከስክሳለች።16 ዓመት።ምርጥ የጦር መሳሪያ፤ ጥብቅ ሥልጠና፤ ረቂቅ ሥልት፤ ትሪሊዮን ዶላር የታጠቀዉ የዓለም ጦር በየጢሻ፤ጎሬ፤ ሸለቆዉ የሚሽሎከሎኩትን ሽፍቶች ማሸነፍ ግን አልቻለም።
                                   
«ከመስከረም አንዱ ጥቃት ከአስራ-ስድስት ዓመታት በኋላ፤ከፍተኛ የደምና የሐብት መስዋዕትነት ከተከፈለ በኋላ፤ በጦርነቱ ድል አለመገኘቱ የአሜሪካ ሕዝብን ሲበዛ አስጭንቋል።ይሕ ደግሞ ከአፍቃኒስታኑ ጦርነት ሌላ ሌላ አይደለም።በአሜሪካ ታሪክ እጅግ ረጅሙ ጦርነት ነዉ።17 ዓመት።»
ሽንፈት ብዙ ሰበብ እና ወቃሽ እንጂ ባለቤት የላትም።ዩናይትድ ስቴትስ በታሪኳ ለረጅም ጊዜ በተዋጋችዉ ጦርነት ላለማሸነፏ ብዙዎች ብዙ ምክንያት ይሰጣሉ።ፕሬዝደንት ትራምፕም ሁለት ምክንያት አላቸዉ።
የቀዳሚዎቻቸዉ ፕሬዝደንቶች ሥልት የተሳሳተ መሆኑ ቀዳሚዉ ነዉ።ትክክለኛዉ ሥልት የሳቸዉ ነዉ።የአሜሪካ ዓላማ ጠላትን መግደል እንጂ ሐገር መገንባት አይደለም።ሁለተኛዉ ጠላቶቻችን ትደግፋለች ያሏትን ፖኪስታን ማስፈራራት ነዉ።
                                 
«ሐገር ገንቢዎች አይደለንም።አሸባሪ ገዳዮች እንጂ።አዲሱ ሥልታችን ከፓኪስታን ጋር ያለንን ግንኙነት መቀየር ነዉ።ፓኪስታን  ለታሊባን እና ለሌሎች አሸባሪ ድርጅቶች ከለላላ ሥለመስጠትዋ ከእንግዲሕ ዝም አንልም።»
የአዲሱ ፕሬዝደንት አዲስ ሥልት ሐገር ግንባታ እና ልማትን ደፍቆ፤ መግደልን የሚያበረታታ፤ ፓኪስታንን አርቆ፤ የፓኪስታን ቀንደኛ ጠላት ሕንድን የሚያስጠጋ ነዉ።ፓኪስታን በራቀች ቁጥር አስራ-ስድት ዓመት ባልጠፋዉ ጠላት ላይ አዲስ ጠላት መጨመር መሆኑን እስካሁን በግልፅ ያስተነተነ የለም።
ትራምፕ አዲሱ ሥልታቸዉ የሚጀመር እና የሚያበቃበትን ጊዜ «የዉጊያዉ ዉጤት» ይወስነዋል ነዉ ያሉት።እርግጥ ነዉ የአሜሪካዉ መከላከያ ሚንስቴር ሰሞኑን አራት ሺሕ አምስት መቶ ተጨማሪ ወታደሮች ወደ አፍቃኒስታን እንደሚያዘምት አስታዉቋል።ፕሬዝደንቱ ግን እንደ ጊዜዉ ሁሉ የሚዋጋዉን ሠራዊት ቁጥር፤ የመሳሪያና የገንዘቡን መጠን አላስታወቁም።
በጊዜ እና በመጠን ያልተወሰነ ነገርን «ሐሳብ እንጂ ሥልት፤ ያዉም የጦር ሥልት ሊባል አይችልም ባዮች ብዙ ናቸዉ።ጥቅምት ሁለት ሺሕ 2001  አፍቃኒስታን እንድትወረር ያዘዙት ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽም ጦርነቱ የሚጀመርበትን እንጂ የሚያበቃበትን አልተናገሩም ነበር።
                                
«በአሸባሪ ላይ የከፈትነዉ ጦርነት ከአል-ቃኢዳ ይጀምራል።ግን እዚያ አያበቃም።ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን በሙሉ እስኪገኝ፤ እስኪቆም እና እስኪሸነፍ ድረስ ጦርነቱ አያበቃም።»
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ዩናይትድ ስቴትስ  ፕሬዝደንቷን ለሰወስተኛ ጊዜ ቀይራለች። ጦርነቱ አፍቃኒስታን፤ ኢራቅ፤ሊቢያ፤ ሶሪያ፤ እያለ እየሰፋ-ዓለምን እያጠፋ፤ ዓለምን እያሸበረ ቀጥሏል።ሰወስተኛዉ ፕሬዝደንት እንደ መጀመሪያዉ ሁሉ ማብቂያዉን ያልወሰኑለት ጦርነት ምናልባት ፓኪስታንን ከለየለት ዉጊያ ይከት ይሆናል።ለአዲሱ ፕሬዝደንት አዋጅ የመጀመሪያዉን ድጋፍ የሰጡት በአሜሪካኖች ድጋፍ የሚተነፍሱት የአፍቃኒስታን መሪ ፕሬዝደንት አሽረፍ ጋኒ ናቸዉ።
                       
«ከእንግዲሕ የጊዜ-ገደብም፤ቅድመ-ግዴታም የለም።አሜሪካ እስከ መጨረሻዉ ከአፍቃኒስታን ጎን ትቆማለች።»
ታሊባን እንደተጠበቀዉ «አፍቃኒስታን እንደከዚሕ ቀደሙ ሁሉ  የአሜሪካ ወታደሮች መቀበሪያ ትሆናለች» በማለት የፕሬዝደንት ትራምፕን አዋጅ አጣጥሎ ነቅፎታል።ቻይና በተለይ በፓኪስታን ላይ የተሰነዘረዉን ወቀሳ ነቅፋዋለች።ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥሎ ከፍተኛዉን የወታደር ቁጥር አፍቃኒስታን ያሰፈረችዉ ጀርመን ለትራምፕ አዋጅ የሰጠችዉ ምላሽ እሁለት የተከፈለ ነዉ።
መከላከያ ሚንስትር ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን የትራምፕን አዋጅ ደግፈዋል።ይሁንና ጀርመን ተጨማሪ ወታደሮች ወደ አፍቃኒስታን እንደማታዘምት አስታዉቀዋል።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሲግማር ጋብርኤል ግን ትራምፕ አዉሮጳን ሳያማክሩ አዲስ የዉጊያ አዋጅ ማዉጣታቸዉን አልደገፉትም። ጋብርኤል እንደሚሉት በጦርነቱ ለሚሰደደዉ የአፍቃኒስታን ዜጋ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል።
አሜሪካ መራሹ ጦር አፍቃኒስታንን ከወረረበት ጊዜ ጀምሮ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ተሰዷል።የአብዛኛዉ ስደተኛ አስተናጋጅ ፓኪስታን ናት።ቀጥሎ አዉሮጳ።የሰሜን አትላቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ዋና ፀሐፊ የንስ ሽቶልትንበርግ እንዳሉት ግን ድርጅታቸዉ የትራምፕን አዋጅ ይደግፋል።
በ2014 ከአሰልጣኝና አማካሪ በስተቀር አፍቃኒስታን የሠፈረዉ የዉጪ ጦር ወደየሐገሩ ተመለሰ ተብሎ ነበር።ግን ከ8500 በላይ የአሜሪካ፤ አስራ-ሰወስት ሺሕ ያሕል የተቀሩት የኔቶ አባል ሐገራት ወታደሮች ዛሬም አፍቃኒስታን ዉስጥ ይዋጋሉ።በአዲሱ የትራምፕ አዋጅ መሠረት ተጨማሪ ወታደር ይዘምታል።ዉጊያዉ ትራምፕ እንዳሉት አሜሪካ እስክታሸንፍ ድረስ ይቀጥላል።ሌላ ፕሬዝደንት፤ሌላ ዘመን፤አሮጌ ጦርነት፤ የእልቂት ዑደት-የዓለም ሥርዓት። ቸር ያሰማን።

Afghanistan Autobomben-Anschlag der Taliban auf einen Militärkonvoi
ምስል Reuters
Afghanistan Anschlag auf Moschee in Kabul
ምስል Reuters/O. Sobhani
Afghanistan Anschlag in Kabul
ምስል Reuters/O. Sobhani

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ