1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍቃኒስታን የምርጫዋ ተስፋና ቀቢፀ-ተስፋ

ሰኞ፣ ነሐሴ 11 2001

በእጩ ተፎካካሪዎች ክርክር፤ በወጣቶቿ የፖለቲካ ትኩሳት የጋመችዉ፥ በሕዝቧ ተስፋ የደመቀችዉ ካቡል፥ የኻርዛይ አዲስ ሥልት በታወጀባት፥የራስሙስን አዲስ ቃል በተሰማባት በአስረኛዉ ቀን-በቦምብ ፍንዳታ፥ በሽብር-እልቂት-ዋይታ መተረማመሷ ነዉ-ሰቀቀኑ

https://p.dw.com/p/JCy3
የምርጫ ዘመቻዉምስል Farahmand / DW

የአዲሱ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና ፀሐፊ አዲስ ቃል፣ የነባሩ ፕሬዝዳት አዲስ መርሕ፥ የተቃዋሚዎቻቸዉ ክርክር፥ የወጣቱ ስሜት፥ ለዘመናት የአዲስ ተስፋ ብርቀት ባሮጌ ድርጊት ፅልመት ለሚጣፋባት ለዚያች ጥንታዊት ሐገር የብሩሕ ጮራ ፍንጣቂ፥ለሕዝቧ የበጎ ተስፋ ጭላንጭልነቱ በርግጥ አያከራክርም።የብዙዎቹ አዲስ ሁነቶች ምንጭ የትነት፣የብሩሕ ጮራ፥ የበጎ ተስፋ ጭላንጭልነታቸዉ ድምቀት በምርጫ ሒደት ሊበየን ዕለታት ሲቀሩት ቅዳሜ ካቡል ላሮጌ ዛሯ ምሥ በደም-አስከሬን ማደፏ ነዉ ዚቁ።ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ። የአፍቃኒስታንን ምርጫ አስታከን የዚያችን ሐገር የተስፋ-ቀበቢፀ ተስፋ ፍጭት ላፍታ እንቃኛለን አብራችሁኝ ቆዩ።

እርግጥ ነዉ-ጥቅምት ሁለት ሺሕ አራት (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) «ምርጫ» በተባለዉ ሒደት አሽናፊ የተባሉት ሐሚድ ኻርዛይ እስከዚያ ድረስ ለሰወስት አመት የያዙትን ሥልጣን «በአፍቃኒስታን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ» መሪ የሚል ቅድመ ቅፅል ታክሎላቸዉ ፕሬዝዳት እንደተባሉ አሉ።

ለብዙዉ አፍቃናዊዉ በጣሙን ለወጣቱ ግን ያለፈዉ አይደለም ሰሞኑን የሚደረገዉም ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ለመባል ብዙ ይቀረዋል።ይሁንና የሰሞኑ ምርጫ አንድ የሐገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኞችና ወጣቶች የዲሞክሪሲን ስርዓት ምንነት፤ የነፃ ምርጫን አስፈላጊነት የምንልማመድ-የምናስተምርበት አጋጣሚ ነዉ-ባዮች ናቸዉ።

እዚሕ ጀርመን-የሙዚቃ ፍቅር ችሎታ ያላቸዉን ወጣቶች የሚያወዳድሩ-የሚመርጡበት የቴሌቪዥን ዝግጅት-ዝግጅት አለ።Deuschland sucht den super star-ይሉታል።ነገሩ የተጀመረዉ አሜሪካ ነዉ-ይባላል።እነሱ-አሜሪካን አይደል-ነዉ የሚሉት።እዚያ እኛ አገርም ኢትዮጵያን አይድል-አንዴዴ አይዶልም-በሚል ስም ነበረ-አሉ።-የሚያዉቁት።

አፍቃኖች ዘንድሮ ይሕን መሰሉን ዝግጅት ለፖቲካ አዋሉት።ናዝማድ-አሉቱም-በቋንቋቸዉ።«እጩዉ» እንደማለት።

ዉድድሩ ለፕሬዝዳትነት-የሚደረግ ነዉ።ተወዳዳሪዎቹ ልክ እንደ እጩ ፕሬዝዳንቶች አለማ-ፕሮግራሜ የሚሉትን መርሕ ያስተዋዉቃሉ።አድማጭ-ዳኞች ለተሻለዉ እጩ ድምፅ ይሰጣሉ።የናዝማድ ጥቅል አለማ-የዝግጅቱ መሪ ጋዜጠኛ እንደሚለዉ የወጣቱን ፖለቲካዊ ፍላጎት ማቅረብ፤ ዲሞክራሲን ለሕዝብ ማስተዋወቅ ነዉ።
«የዚሕ ትርዒት መሠረታዊ አላማ ለዝቡ ሥለ ዴሞክራሲና ሥለ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማሳወቅ ነዉ።ከዚሕም በተጨማሪ አፍቃኒስታን ዉስጥ ብዙ ተሰሚነት የሌለዉ የወጣቱ ትዉልድ ድምፅ እንዲሰማ ማድረግ ነዉ።እነዚሕ ወጣቶች ድምፃቸዉን ለማሰማት ወደኛ ይመጣሉ።»

ከታላቁ አሌክዛንሰር-እስከ ፋርሶች፥ ከሞንጎሎች እስከ ቻይኖች፥ ከሩሲያዎች እስከ እንግሊዞች፥ ከሶቬት ሕብረቶች እስከ አሜሪካኖች በየዘመኑ አለምን ለገዙ ሐይላት አልገዛም እያለ ገድሎ እየሞተ-ሐገር ሉአላዊነቱን ያስከበረዉ ያ ሕዝብ የጀግንነት ተጋድሎዉን የሚመጥን ዕድገት፥ ነፃነት፥ ፍትሕ ኖሮት አያዉቅም።አሚሮች፥ ባላባቶች፥ የጦር አለቆች እንዳመቻቸዉ እብዙ ቦታ ሸንሽነዉ ሲገዙት አንዳዴም በዉጪ ሐይላት ሲያስገብሩት ኖረዉ የኋላ ኋላ አንድነቱን ቢያስከብርም ከነገስታቱ አገዛዝ ማምለጥ አልቻለም።

የጨቋኝ ነገሥታቱን አገዛዝ ለማስወገድ በተደጋጋሚ ያደረገዉ አመፅ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ለዉጤት በቅቷል።ይሁንና አመፁን በማስተባበር ሥም ሥልጣን የያዙት የጦር መኮንኖች ሐገሪቱን ለሶቬት ሕብረት አሳልፈዉ ሕዝባቸዉን ላዲስ ግን ለከፋ ጭቆና ነበር-የዳረጉት።ከ1973 ወዲሕ ሪፐብሊካዊ ሥርዓት የታወጀባት አፍቃኒስታን በጦርነት እንደደቀቀች፥በእልቂት እንደወደመች፥በዉጪ ሐይላት እንደተተራመሰች ፕሬዝዳት የሚባሉ አስር መሪዎች እንደተለዋወጡባት መስከረም-2001 ላይ ደርሳለች።

በዚያ መስከረም ታሊባን ያስጠጋዉ አልቃኢዳ ዩናይትድ ስቴትስን ማሸበሩ ሰበብ ሆኖ ኻሚድ ኻርዛይን ከካቡል ቤተ-መንግሥት ዶሏል።

እንደ ፓሽትን-ዘመናይ ባላባት ካባ ቆብ የሚያዘወትሩት፥ ኢራኖችን በፋርስኛ ሕንዶችን፣ በሒንዲኛ፥ፓኪስታኖችን በኡርዱኛ፥ እንግሊዝ-አሜሪካኖችን በአሜሪካ-እንግሊዝኛ የሚያነጋግሩት ሐሚድ ኻርዛይ-በአሜሪካኖች ድጋፍ የመሪነቱን ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ የአሜሪካኖች አሻንጉሊት የሚል ወቀሳ-ትችት ተለይቷቸዉ አያዉቅም።

የናጂቡላሕን ኮሚንስታዊ ሥርዓትና ሥርዓቱን ለማስከበር አፍቃኒስታንን የወረረዉን የሶቬት ሕብረትን ጦር ለማስወጣት ይዋጉ የነበሩ ሙጃሒዲያን የተቀየጡት ኻርዛይ ሙጃሒዲያኑን ከሚያስተባብሩት ከዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ጋር በ1980ዎቹ የመሥረቱት ግንኙነት የኋላ ኋላ አሁን ለያዙት ሥልጣን እንዳበቃቸዉ ወቃሽ-ተቺዎቻቸዉ አይደሉም እሳቸዉም አይክዱትም።

Anschlag in Afghanistan
የቦምቡ ፍንዳታምስል AP

ኻርዛይ በ2008 መጀመሪያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ «ከአሜሪካኖች ጋር ጥብቅ ወዳጅነት መመስረቴ የአሜሪካ አሻንጉሊት ካስባለኝ-ይሕ ቅፅል ስሜ ይሆን ነበር ያሉት።የፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ መስተዳድር ሥልጣን ከለቀቀ ወዲሕ የኻርዛይ ዋሽንግተኖች ጥብቅ ወዳጅነት ነፋስ የገባበት አይነት ሆኗል።

ኻርዛይ በርግጥ ዋዛ ፖለቲከኛ አይደሉም። ንፍሳይ ሽዉ ያለበት የዋሽንግተን ግንኙነታቸዉ የሐሙሱን ምርጫ ታኮ ከካቡል ቤተ-መንግሥታቸዉ እንዳሽቀንጥራቸዉ አዲስ መርሕ መከተላቸዉ፥ ወይም የተከተሉ መምሰላቸዉ አልቀረም።ምርጫዉ ሁለት ሳምንት ሲቀረዉ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሐገር-ሕዝባቸዉ ቀንደኛ ጠላቶች ከሚሏቸዉ ከታሊባኖች ጋር መደራደር ዋና አላማቸዉ እንደሆነ አስታወቁ።
«ቅድሚያ የምሰጠዉ አብይ ጉዳይ ከታሊባን፥ ከሒዝቢ ኢስላምና ከሌሎች ቡድናት ጋር የሚደረገዉን የሠላም ሒደት ማጠናከርና ማፋጠን ነዉ።»
ዘገዩ-ስምንት አመት።ግን ዛሬም-ይቻላል።
፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧

የፕሬዝዳት ኦባማ መስተዳድር በቀየሰዉ አዲስ ስልት መሠረት ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ ተጨማሪ ጦር አዝምተዉ ደቡብ አፍቃኒስታን በሸመቁ የታሊባንና የአል-ቃኢዳ ታጣቂዎች ላይ የሚሚደረገዉ ጥቃት ተጠናክሯል።የፓኪስታን ጦር ስዋት ሸለቆ በመሸጉ ታሊባኖች ላይ የተቀዳጀዉ ድል-ፓኪስታንን ከተደጋጋሚዉ የአጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃት ባያስጥላትም-ድሉ የኦባማ መርሕ ዉጤት መሆኑ አያነጋግርም።

የፊታችን ሐሙስ የሚደረገዉን ምርጫ የተሻለ ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ፥ የምርጫዉ ሒደት እንዳይታወክ የኔቶ አባል ሐገራት ተጨማሪ ወታደሮች ማዝመታቸዉ፥ አዲሱ የኔቶ ዋና ፀሐፊ አንደርስ ፎግሕ ራስሙስን እንዳሉት ደግሞ የጦር ተሻራኪዉ ድርጅት አብይ ትኩረት የአፍቃኒስታን ሠላም የሆነበት ምክንያት-የዋሽንግተን አዲስ ሥልት ዉጤት ለመሆኑ እማኝ መቆጠር አያስፈልግም።

«ይሕ እንደ ኔቶ ዋና ፀሐፊ በዉጪ የማደርገዉ የመጀመሪያዉ ጉብኝት ነዉ።አዲሱን ሥልጣኔን እንደተረከብኩ አፍቃኒስታንን በቅድሚያ ለመጎብኘት መወሰኔ ለአፍቃኒስታን ልዩ ትኩረት መስጠቴን ያረጋግጣል።ይሕ ማለት እንደ ኔቶ ዋና ፀሐፊ ከአፍቃኒስታን የማስቀድመዉ እንደሌለለ ምስክር ነዉ-ማለት ነዉ።ኔቶ የአፍቃኒስታን ወዳጅ ነዉ።እኛ በጋራ የአፍቃኒስታንን ጠላቶች እንዋጋለን።»

Hamid Karzai PK in Kabul
ኻርዛይምስል AP

የኻርዛይ ዋሽንግተኞች ጥብቅ ወዳጅነት መላላት-ለመጪዉ ሮብ የተያዘዉ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በ2004 ተደረገ እንደተባለዉ ካርዛይ ብቻቸዉን ወይም ከጥቂት አጃቢዎቻቸዉ ጋር ተወዳድረዉ አሸናፊ የሚባሉበትን መድረክ አጥብቦቻል።ለአፍቃኒስታን ሕዝብ ባንፃሩ የማመረጥ እዱሉን አስፍቶለታል።

በሐሙሱ ምርጫ በራሳቸዉ በኻርዛይ መንግሥት ካቢኔ ዉስጥ ያገለገሉና የሚያገለግሉትን የቀድሞዉን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አብዱላሕ አብዱላሕ፥ እዉቁ ፖለቲከኛ ራምዛን ባሽረዱስት፥ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አብዱል ጀባር ሳቢት፥ ሰፊ የፖለቲካ ልምድ ያላቸዉ አሽራፍን ጨምሮ ሰላሳ-ስምንት እጩዎች ኻርዛይን ይፎካከራሉ።

የተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ፉክክር ማየል፥ የመደገፍ-መቀዋም ነፃነት-ድፍረት መዳበር፥ የወጣቶቹ ተነሳሽነት ለፍቃኒስታን ሕዝብ በርግጥ የተሻለ ተስፋ-ምልክት ነዉ።ለምርጫዉ አለም አቀፉ ማሕበረሰብ ከፍተኛ ድጋፍ እየሰጠ ነዉ።ራስሙሰን ካቡል ላይ እንዳረጋገጡት በምርጫዉ ሒደት ፀጥታ እንዳይታጎል አለም አቀፉ ሠራዊት አስፈላጊዉን ጥበቃ ሁሉ ያደርጋል።
«ኔቶና ISAF የናንተ የምርጫ ሒደት ፀጥታን ለማስከበር እዚሕ ይገኛሉ።በተቻለ መጠን አስተማማኝ ፀጥታ ለማረጋገጥ ይጥራሉ።እኛ የምንፈልገዉ የሕዝቡን እዉነተኛ ፍላጎት የሚያንፀባርቅ ተአማኒነት ያለዉ ምርጫ እንዲደረግ ነዉ።»

በእጩ ተፎካካሪዎች ክርክር፤ በወጣቶቿ የፖለቲካ ትኩሳት የጋመችዉ፥ በሕዝቧ ተስፋ የደመቀችዉ ካቡል፥ የኻርዛይ አዲስ ሥልት በታወጀባት፥የራስሙስን አዲስ ቃል በተሰማባት በአስረኛዉ ቀን-በቦምብ ፍንዳታ፥ በሽብር-እልቂት-ዋይታ መተረማመሷ ነዉ-ሰቀቀኑ።-ቅዳሜ።
«አጥፍቶ ጠፊዉ ከISAF ቅጥር ግቢ እጅግ በቀረበ ሥፍራ ወደ ሰላሳ ኪሎሜትር ከሚርቅ ሥፍራ ሲደርስ በተሽከርካሪዉ ላይ የጫነዉን ቦምብ አፈነዳዉ።የአፍቃኒስታን ብሔራዊ ፀጥታ ሐይል አባላት መኪናዉን ማስቆም ችለዉ ነበር።ቦንቡን የታጠቀዉ (ግለሰብ) መኪናዉን እንዳቆመ (ወዲያዉ) እራሱን አጋይቷል።»
ካናዳዊዉ ወታደር።
በአደጋዉ በትንሹ ሰባት ሰዉ ተገደለ።በርካታ ቆሰለ።በማግስቱ አፍቃኒስታን የሰፈረዉ የብርታንያ ጦር-የሁለተ መቶ አንደኛ ወታደሩን ሞት አረዳ።እሁድ።ትናንትናዉኑ የታሊባን ሐይላት ካንዳሐርን በሮኬት ደበደቡ።ሁለት ሰዉ አቆሰሉ።ይሕ ነዉ-የኦባማ መስተዳድ አዲስ ሥልት፥ አዲሱ ስልት ያስከተላቸዉ ብዙ አዲስ ሁነቶች፥ የሐሙሱ ምርጫ የፈነጠቀዉ አዲስ ብሩሕ-በጎ ተስፋ-በቀቢፀ ተስፋ-የመቃረጡ ድቀት።ነጋሽ መሐመድ ነኝ እስኪ ቸር ያሰማን።

Dw,Agenturen

ነጋሽ መሐመድ/አርያም ተክሌ