1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

  አፍቃኒስታን ግዞትና ፍንዳታ

ሐሙስ፣ ግንቦት 24 2009

ከ2001 ጀምሮ በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ የሐገሪቱ ዜጎች አልቀዋል።ሚሊዮኖች ተሰደዋል።መቶ ሺዎች ተፈናቅለዋል።አብዛኞቹ ተፈናቃዮች እና ከስደት ተመላሾች የሚሰፍሩት ካቡል ነዉ።ካቡል በነዋሪዎች፤በጦር ኃይሎች፤  በርዳታ ሰጪዎች በተፈናቃዮች፤ በከስደት ተመላሾች ተጨናንቃለች።በቦምብም ትረባያለች።

https://p.dw.com/p/2dzem
Deutschland Demonstrationen gegen Abschiebungen am Flughafen in München
ምስል picture-alliance/ZUMA Wire/S. Babbar

Afghanistan-Abschiebung - MP3-Stereo

ካቡል-አፍቃኒስታንን ትናንት ያሸበረዉ የቦምብ ጥቃት እዚሕ ጀርመን የሚኖሩ ሕገ-ወጥ የአፍቃኒስታን ስደተኞች ወደ አፍቃኒስታን ይመለሱ- አይመለሱ የሚለዉን ክርክር እንደገና ቀስቅሶታል።የትናንቱ አደጋ እንደደረሰ ከጀርመን ወደ አፍቃኒስታን ሊጠረዙ ተዘጋጅተዉ የነበሩ የአፍቃኒስታን ስደተኞች  ጉዞ ለጊዜዉ እንዲዘገይ ተደርጓል።የጀርመን ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና የመብት ተሟጋቾች አፍቃኒስታን እስክትረጋጋ ድረስ ስደተኞቹን ወደሐገራቸዉ መመለሱ መቆም አለበት ይላሉ።ወግ አጥባቂዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን አንድ ቀን አደጋ ደረሰ ተብሎ ስደተኞችን ማጋዙ መቋረጥ የለበትም ባይ ናቸዉ።ነጋሽ መሐመድ ዝርዝር ዘገባ አለዉ

እንደ ኒዮርክ-ዋሽግተን፤ ፓሪስ-ለንደን፤ በርሊን-ማንቸስተር አበባ ጉንጉን የከመረ፤ ያለቀሰ፤ የጮኸ፤ አጥፊዎችዋን ሊያጠፋ የዛተ የፎከረላት የለም።ካለም ድምፁ የሠለለ፤ አቅም፤ ጉልበቱ የላሸቀ የደከመ በመሆኑ አይሰማም።ለነገሩ ልማዷ ነዉ።ካቡል-አፍቃኒስታን።ቦምብ-ሚሳዬል፤ መድፍ-ታንክ እና በማያባራ እልቂት። አስራ-ስድት አመቷ።
ወጣቱ አፍቃናዊ ረሕመት (የሽፋን ሥም ነዉ) ጀርመን በተሰደደበት ስድት ዓመት  ተንፈስ ብሎ፤ የሕይወትን ጥሩ ጎን አሻግሮ ማየት ጀምሮ ነበር።ግን «ሕገ-ወጥ » ተብሎ ወደ ካቡል ተጋዘ።«እፈራለሁ፤ እዚሕ ሰላም አይሰማኝም።አላዉቅም ግን እዚሕ መኖር አልችልም» አለ ረሕማ በቀደም ላነጋገሩት ጋዜጠኞች።ከትናንቱ አደጋስ ተርፎ ይሆን? አናዉቅም።የምናዉቀዉን እንቀጥል።23 ዓመቱ  ነዉ።ፍራንክፈርት-ጀርመን ዉስጥ ስድስት አመት ኖሯል።የጀርመን መንግስት የጥገኝነት ጥያቄያቸዉ ተቀባይነት ያላገኘ የአፍቃኒስታን ስደተኞችን ወደ ሐገራቸዉ ሲመልስ ከመጀመሪያዎቹ ተጋዦች አንዱ ሆኖ ካቡል ገባ።አምና ታሕሳስ።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ካቡል ነዉ።ተወልዶ ያደገዉ ግን ፓንድሽታር ከተማ ነበር።አሁን ወደ ትዉልድ መንደሩ መሔድ አይፈልግም።«እንኳን እዚያ ሔጄላቸዉ» ዓይነት ይላል ወጣቱ «ለምን» ሲሉት።
 «አባቴ ጄኔራል ነበር። የዛሬ ስምንት ዓመት ታሊባኖች ገደሉት።እኔንም  ቢያገኙኝ አይምሩኝም።» ጀርመን የገባዉ ኢራንን፤ ቱርክን፤ ግሪክን፤ ኢጣሊያን እና ፈረንሳይን አቋርጦ ነበር። እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር በ2011። ከ10 ሺሕ ዶላር በላይ ፈጅቷል።ሲጋዝ ግን 700 ዩሮ ተወረወረለት፤ ካቡል ተወረወረ።
የጀርመን መንግስት ከአፍቃኒስታን መንግሥት ጋር ባደረገዉ ሥምምነት መሠረት ካለፈዉ ታሕሳስ እስከ እስካለፈዉ ሚያዚያ ማብቂያ ድረስ የጥገኝነት ማመልከቻቸዉ ተቀባይነት ያላገኘ 107 የአፍቃኒስታን ስደተኞች ወደሐገራቸዉ መልሷል።ለአያንዳዱ በረራ 3መቶ ሺሕ ዩሮ ይከሰክሳል።

Deutschland Polizeieinsatz bei Schülerdemo gegen Abschiebung in Nürnberg
ምስል picture-alliance/dpa/Nürnberger Nachrichten/ARC/M. Matejka

ከጦርነት እና ሽብር ያመለጡ ሰዎችን እልቂት መሐል መልሶ መዶል ተገቢ አይደለም በማለት የመብት ተሟጋቾች እና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ሲከራከሩ ነበር።ትናንት ካቡልን ባሸበረዉ አደጋ ከ90 በላይ ሰዎች መገደላቸዉ የስደተኞችን መጋዝ ለሚቃወሙ  ክርክር እዉነትነት ማረጋገጪያ፤ ጥሪያቸዉን ዳግም ለማሰማት ምክንያትም ነዉ የሆነዉ።ወግ አጥባቂዎቹ የክርስቲያን ሶሻል ሕብረት (CSU) ፖለቲከኞች ግን ሕገ-ወጥቶች ይጋዛሉ እንዳሉ ነዉ።

Afganistan Deutsche Botschaft bei Anschlag in Kabul massiv beschädigt
ምስል REUTERS/O. Sobhani

«ጥገኝነት በተሰጣቸዉን እና ባልተሰጣቸዉ መካከል ልዩነት መኖር አለበት።ጥገኝነት ተሰጥሕም አልተሰጠሕ ጀርመን ዉስጥ መኖር ትችላለሕ የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም።»
ይላሉ የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ሽቴፋን ማየር።

አሜሪካ መራሹ ጦር አፍቃኒስታንን ከወረረበት እንደ ጎርጎሪያን አቆጣጠር ከ2001 ጀምሮ በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ የሐገሪቱ ዜጎች አልቀዋል።ሚሊዮኖች ተሰደዋል።መቶ ሺዎች ተፈናቅለዋል።አብዛኞቹ ተፈናቃዮች እና ከስደት ተመላሾች የሚሰፍሩት ካቡል ነዉ።ካቡል በነዋሪዎች፤በጦር ኃይሎች፤  በርዳታ ሰጪዎች በተፈናቃዮች፤ በከስደት ተመላሾች ተጨናንቃለች።በቦምብም ትረባያለች።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ