1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢሕአዴግና ደኢሕዴን የጠቅላይ ምኒስትሩን መልቀቂያ ተቀበሉ

ሐሙስ፣ የካቲት 8 2010

ጠቅላይ ምኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ያቀረቡትን የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ ኢሕአዴግ እና ደኢሕዴን ተቀበሉ። ጠቅላይ ምኒስትሩ "ሕዝቡ ለሚያነሳቸው በርካታ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ተገቢ እና አስፈላጊ ነው" ብለዋል።

https://p.dw.com/p/2slz9
Äthiopischer Premierminister Hailemariam Desalegn beim Interview mit Reuters in Addis Ababa (Reuters/T. Negeri)
ምስል Reuters/File Photo/T. Negeri

ጠቅላይ ምኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ያቀረቡትን የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ መቀበሉን የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አስታወቀ።

የኢሕአዴግ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ "አገሪቱንና ድርጅቱን መምራት ያለበት ሌላ ሰው መምጣት አለበት ብለው ስለወሰኑ" አቶ ኃይለማርያም በትናንትናው ዕለት ለደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የስራ መልቀቂያ ጥያቄያቸውን ማቅረባቸውን ተናግረዋል። ደኢሕዴን "የለውጥ እንቅስቃሴውን ለማገዝ ያለውን አስተዋጽዖ በዝርዝር ከመዘነ በኋላ ጥያቄያቸውን ተቀብሎታል" ሲሉ አቶ ሽፈራው አክለዋል።

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ዛሬ የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. የቀረበለትን የጠቅላይ ምኒስትሩን የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ መቀበሉን አቶ ሽፈራው አረጋግጠዋል። ጠቅላይ ምኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ "የደኢሕዴን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴም ሆነ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጥያቄዬን በአዎንታዊ መንገድ ተቀብለውታል። ይኸ ጥያቄ የመጨረሻ ውሳኔ የሚያገኘው በኢሕአዴግ ምክር ቤት ይሆናል" ሲሉ ተናግረው ነበር። የጠቅላይ ምኒስትሩ ጥያቄ በኢሕአዴግ ምክር ቤት መፅደቅ ይኖርበታል።

ጠቅላይ ምኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሥራ መልቀቂያ ጥያቄውን ያቀረቡት "ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ለማድረግ የመፍትሔው አካል መሆን አስፈላጊ ነው ብዬ ስላመንኩኝ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

በብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ በቀጥታ በተላለፈ ንግግራቸው "ሕዝቡ ለሚያነሳቸው በርካታ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ተገቢ እና አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ" ያሉት አቶ ኃይለማርያም  "የመልቀቂያዬ የመጨረሻ ውሳኔ በሚመለከታቸው አካላት ይሰጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉም አክለዋል።

ኢሕአዴግ አዲስ ሊቀ-መንበር መርጦ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እስኪጸድቅ ድረስ ጠቅላይ ምኒስትሩ በሥልጣናቸው ይቆያሉ። አቶ ኃይለማርያምም "በእነዚህ ተቋማት ውሳኔው እስኪጸድቅ ድረስ የተሰጠኝን ኃላፊነት የምቀጥል ይሆናል" ሲሉ ተናግረዋል።

የጠቅላይ ምኒስትሩ ውሳኔ ከተሰማ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የኢሕአዴግ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ "አዲስ ነገር" አልተፈጠረም ሲሉ በአፅንዖት ተናግረዋል። አቶ ሽፈራው በ"ኢሕአዴጋዊ ባሕል እና ሒደት በፍጹም ዴሞክራሲያዊ ሒደት ከኢሕአዴግ እህት ድርጅቶች መካከል" የድርጅቱን ሊቀ-መንበር እና የአገሪቱን ጠቅላይ ምኒስትር እንደሚመርጥ አስረድተዋል።  

የአቶ ኃይለማርያም ተተኪ የሚመረጥበት የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ መቼ እንደሚካሔድ ባይታወቅም የግንባሩ የፌስቡክ ገፅ "በቅርቡ" መሆኑን አትቷል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ