1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢሬቻ በጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥር አነስተኛ ታዳምያን በተገኙበት ተከበረ

ቅዳሜ፣ መስከረም 23 2013

የኢሬቻ በዓል "አንዳች የጸጥታ ችግር ሳያጋጥም" መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል። በዓሉ ጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥር የነበረበት የታዳሚዎቹም ቁጥር አነስተኛ ነበር። "ምን ዓይነት መረጃ እንዳላቸው አላውቅም። ነገር ግን ፍተሻው እጅግ ብዙ ነው" ሲል ሑሴን የተባለ የበዓሉ ታዳሚ ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግሯል።

https://p.dw.com/p/3jNSn
Äthiopien Oromo Thanksgiving in Addis Abeba 2020
ምስል Addis Abeba City/Press Secretary Office

አመታዊው የኦሮሞ የምስጋና በዓል በጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥር አነስተኛ ታዳምያን በተገኙበት በአዲስ አበባ ዛሬ ተከበረ። የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ያጠለቁ፤ በኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ ያሸበረቁ አልባሳት የለበሱ ታዳሚዎች በዓሉ ወደሚከበርበት ቦታ ሲያቀኑ በትንሹ ስድስት ፍተሻዎች ማለፍ እንደሚጠበቅባቸው አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። በዘገባው መሠረት አነፍናፊ ውሾች ጭምር ሥራ ላይ ነበሩ።

"ምን ዓይነት መረጃ እንዳላቸው አላውቅም። ነገር ግን ፍተሻው እጅግ ብዙ ነው" ሲል ሑሴን የተባለ የበዓሉ ታዳሚ ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግሯል። ሙሉ ስሙን ለደሕንነቱ ሲል መናገር ያልፈለገው ሑሴን "ከኮቪድ19 ወረርሽኝ ጋር ተደማምሮ የበዓሉን ድምቀት አበላሽቶታል" ብሏል።

Äthiopien Oromo Thanksgiving in Addis Abeba 2020
የበዓሉ ታዳምያን- ፎቶ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሴክሬታሪምስል Addis Abeba City/Press Secretary Office

"የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ ክብረ-በዓል የኦሮሞ አባገዳዎች ሕብረት በወሰነው መሠረት በውስን የተሳታፊ ቁጥር በደማቅ ሁኔታ በመዲናችን ተከብሯል" ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር "አንዳች የጸጥታ ችግር ሳያጋጥም" መጠናቀቁን አስታውቋል።

ከተለያዩ የከተማዋ አቅጣጫዎች በዓሉ ወደሚከበርበት አካባቢ ለማቅናት የሞከሩ በርካታ ሰዎች በጸጥታ አስከባሪዎች መከልከላቸውን ዶይቼ ቬለ ከአይን እማኞች አረጋግጧል። የአይን እማኞች እንዳሉት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና መንግሥታቸውን እንዲሁም በስልጣን ላይ የሚገኘውን ብልጽግና ፓርቲ የሚተቹ መፈክሮች የሚያሰሙ ወጣቶች ነበሩ። በማኅበራዊ ድረ ገጾች በተሰራጩ ቪዲዮዎች "ፍትኅ እንፈልጋለን፤  ሁሉም የኦሮሞ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ" የሚሉ መፈክሮች ወጣቶች ሲያሰሙ ታይቷል። 

አሶሼትድ ፕሬስ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ከሌሎች ክልሎች ወደ ዋና ከተማዋ የተጓዙ ሰዎች አዲስ አበባ መግባት እንደተከለከሉ ማረጋገጡን ዘግቧል። የመንግሥት ባለሥልጣናት ክልከላውን ባያረጋግጡም ጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥር መደረጉን ገልጸዋል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር እና የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ ሰንደቅ ዓላማዎችን የሚያውለበልቡ የኢሬቻ ታዳሚዎች በዛሬው የበዓል አከባበር ላይ አልነበሩም።

"ሰዎች ሲሰበሰቡ በአገሪቱ እየሆነ ስላለው የተሳሳተ ነገር ሊያንጸባርቁ ይችላሉ። በዚያ ፍራቻ ገድበውናል" ሲል ጃተኒ ቦነያ የተባለ የ26 አመት ወጣት ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግሯል። ለወጣቱ "መንግሥት እያደረገ ያለው ነገር ትክክል አይደለም።"

Äthiopien Oromo Thanksgiving in Addis Abeba 2020
የበዓሉ ታዳምያን- ፎቶ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሴክሬታሪምስል Addis Abeba City/Press Secretary Office

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ኢሬቻ "ባሕላዊ ሥርዓቱን በጠበቀ እና በሰላማዊ መንገድ" ተከብሮ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

"የጥፋት ሥራን ደግሰው፣ አቅደው፣ አቀናጅተው በጀት መድበው፣ የሰው ኃይል አሰማርተው በብዙ ጥፋት ውስጥ እንድናልፍ ለማድረግ ሰርተው ነበር" ሲሉ "የጥፋት ኃይሎች" ያሏቸውን ኮንነዋል። "የጥፋት ኃይሎች" ያሏቸውን ማንነት አዳነች በስም አልጠቀሱም።

የኢትዮጵያ መንግሥት በኢሬቻ በዓል ታዳሚያን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር አቅደው ነበር ያላቸውን 503 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ባለፈው ሐሙስ አስታውቆ ነበር።  የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ኮማንደር አራርሳ መርዳሳ እንደተናገሩት ከተጠርጣሪዎቹ በተጨማሪ 14 ክላሽንኮቭ፣ 26 ቦምብ እና 103 ሽጉጦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ድምጻዊ ሐጫሉ ሑንዴሳ ባለፈው ሰኔ ከተገደለ በኋላ በኦሮሞ ብሔርተኞች እና ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሚመሩት መንግሥት መካከል ያለው ውጥረት በርትቷል። ከሐጫሉ ግድያ በኋላ በተቀሰቀሰ ኹከት ከ160 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ታዋቂ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞችን ጨምሮ ከ9,000 በላይ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ ይጠቁማል።

የኢሬቻ በዓል በዋናነት ከአዲስ አበባ በ50 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው የቢሾፍቱ ከተማ ይከበራል። ባለፈው አመት በዓሉ በአዲስ አበባ እንዲከበር መንግሥት ሲፈቅድ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታድመው ነበር። ሆራ አርሰዴ በነገው ዕለት በቢሸፍቱ ከተማ ይከበራል።

እሸቴ በቀለ