1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያና የስደተኞች መስተንግዶ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 15 2006

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ባለፈው ወር ማለቂያ ገደማ የስደተኞችን መስተንግዶ በተመለከተ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ክፍለ ዓለም በዚህ ረገድ ከኬንያ ልቃ መገኘቷን ከሰሞኑ በሰጠው መግለጫ ላይ ይፋ አድርጓል።

https://p.dw.com/p/1Cyvw
ምስል Nichole Sobecki/AFP/Getty Images

ኢትዮጵያ በተጠቀሰው ጊዜ 629,718 የተመዘገቡ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ መሆኗ የተነገረ ሲሆን ኬንያ 575,334 ስደተኞችንና የፖለቲካ ተገን ጠያቂዎች መጠለያ እንዲያገኙ አብቅታለች። በኢትዮጵያ እንዲህ መጠለያ ፈላጊ የውጭ ተወላጆች መበራከት የሚያስከትለው ጫና ምን ይሆን ? በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ጽ/ቤት ቃል አቀባይ አቶ ክሡት ገ/እግዚአብሔር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ከምታስተናግዳቸው ስደተኞች መካከል ከሞላ ጎደል ገሚሱ ደቡብ ሱዳናውያን ናቸው። ባለፈው ታኅስስ በሥልጣን ላይ በሚገኙት ፕሬዚዳንት ሳልባ ኪርና ቀደም ባለው ጊዜ ምክትላቸው በነበሩት ሪኤክ ማቻር መካከል ተፈጠረ የተባለው የሥልጣን ሽኩቻ ባስከተለው በዲንካና ኑኤር ብሄራት አባላት መካከል በተቀሰቀሰ የእርስ በርስ ውጊያ ሳቢያ በሺ የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያን መገደላቸውና 1,59 ሚሊዮን በመፈናቀል ፤ ቤት ንብረታቸውን ለቀው መሰደዳቸው አልቀረም። በሀገር ውስጥ ከተበተኑት ሌላ ወደ ጎረቤት ሃገራትም የሚሰደዱት ጥቂቶች አይደሉም።

UNHCR Flüchtlingslage in Gambella Äthiopien
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

አብዛኞቹ ደቡብ ሱዳናውያን የተሰደዱት ወደ ኢትዮጵያ ሲሆን የሠፈሩትም በጋምቤላ ነው፤ እነዚህን ሰዎች አገሪቱ ስታታደግ የሚያጋጥማት ጫና ቀላል አይደለም፤ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን ጽ/ቤት ቃል አቀባይ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሱዳናውያን ሌላ 245 ሶማሌዎችና 99 ሺ ኤርትራውያን ስደተኞችም ተጠልለዋል። UNHCR እንዳለው በ 23 መጠለያ ሠፈሮችና 5 መተላለፊያ ጣቢያዎች ፣በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠሩ ስደተኞች የኢትዮጵያ መንግሥት የተለያዩ ተባባሪዎችና UNHCR ሰብአዊ ርዳታ ያቀርባሉ።

ችግሩ ሰፋ ያለ ነው። የጤና ጣቢያዎች፤ ት/ቤቶችና የመሳሰሉ ለስደተኞች ያስፈልጋሉ። በዛ ያሉት ስደተኞች በሚገኙበት በጋምቤላ ፣ ኢትዮጵያ፣ ብርቱ ዝናም ፣ በመጠለያ ድንኳኖች ላይ ሳንክ ከማስከተሉም ጎርፍና የሚቋር ውሃ የጤና እክል ይፈጥራል። በዚህ ሳቢያ ሊያጋጥም የሚችለውን ኮሌራንም የመሳሰለ ለመከላከል ኮሚሽኑ የቱን ያህል ዝግጅት አድርጎ ይሆን!

Eritreas-Flüchtlinge in Nord-Äthiopien
ምስል DW/Getachew Tedla Hailegeorgis

የደቡብ ሱዳን ውዝግብ በድርድር ፤ በዕርቀ ሰላም እልባት ያገኝ ዘንድ፤ በምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት በኩል ጥረት እንደሚደረግ ይሰማል። ለሶማልያ ውዝግብም በአፍሪቃ ሕብረት በኩል የተወሰደ ርምጃ አለ። እስካሁን የታሰበውን ውጤት ባያስገኝም። በኤርትራና ኢትዮጵያ በኩል ሰላምም ጦርነትም ባይኖርም ውጥረት አልተለየም ፤ የስደተኞች ቁጥር ደግሞ በመጨመር ላይ መሆኑ ነው የሚነገረው፤ በአጠቃላይ በአፍሪቃም ሆነ በሌላው የዓለም ክፍል ውዝግብ እንዳይፈጠር ቅድመ ግዴታዎች ቢሟሉ ሰዎች ለስደት ሊዳረጉ ባልቻሉም ነበር። UNHCRም ባላስፈለገ ነበር፤ እርግጥ ነባቤ ቃልና ገሐዳዊ ይዞታ ይለያያሉ ። ያም ሆኖ ኮሚሽኑ ሰዎች ለስደት እንዳይዳረጉ አስቀድሞ የሚተባበርበት ሁኔታ ይኖር ይሆን? አቶ ክሡት ገ/እግዚአብሔር--

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ