1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቃለ-መጠይቅ ከፕሬዝደንት ሽታይንማየር ጋር

ቅዳሜ፣ ጥር 18 2011

«ይሕችን ጥልቅ ትርጉም ያላትን ታላቅ አፍሪቃዊት ሐገር በከፍተኛ ፍላጎት እና በታላቅ አክብሮት የምናያት መሆኑን መናገር እንችላለን።አሁን የሚታየዉ (ለዉጥ) በተለይም የለዉጡ አወንታዊ ዉጤቶች፣ ወደ ዴሞክራሲና ምጣኔ ሐብታዊ መረጋጋት  የሚደረግ በአካባቢዉም የሚንፀባረቅ ፣ለመላዉ አፍሪቃም በጎ አስተምሕሮ ነዉ።» - ፕሬዝደንት ሽታይንማየር

https://p.dw.com/p/3CFB1
DW-Interview mit Frank-Walter Steinmeier
ምስል DW/R. Oberhammer

ቃለ መጠይቅ

የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር፤ ለአፍሪቃ እንግዳ አይደሉም። ኢትዮጵያንም ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር በነበሩበት ዘመን በ2014 እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ጎብኝተዋታል። ያዉቋታል። ኢትዮጵያ ዉስጥ የተደረገዉን ለዉጥም በቅርብ ይከታተላሉ። ለዉጡ እና እርምጃዉን «ከኢትዮጵያ ድንበር አልፎ የሚያንፀባርቅ፣ ለአፍሪቃ አብዮታዊ ዉሳኔ» ይሉታል። ለዉጡ ፈተና እንዳለዉም አላጡም። «የዋሕ አይደለንም» አሉ -በቀደም። ሙሉ ቃለ ምልልሱን እነሆ፤

DW፦ ክቡር ፕሬዝደንት፣ አፍሪቃን ሲጎበኙ ያሁኑ ሶስተኛዎ ነዉ። ከዚሕ ቀደም ጋና፣ ጋምቢያ፣ ደቡብ አፍሪቃ እና ቦትስዋና ነበሩ። እንደ ጋምቢያ ሁሉ ኢትዮጵያ ዉስጥ አስገራሚ ዴሞክራሲያዊ ለዉጥ ተደርጓል። ኢትዮጵያን እንዴት ነዉ የሚገመግሙት?

ፕሬዝደንት ሽታይንማየር፦ «የተለየ ነዉ። ምክንያቱም ኢትዮጵያን ስጎበኝ የመጀመሪያዬ አይደለም። ሐገሪቱን በተወሰነ ደረጃ አዉቃታለሁ። እርግጥ ነዉ ያየኋት በሌላ ጊዜና ፖለቲካዊ ሁኔታ ዉስጥ እያለች ነበር። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዉስጥ ኢትዮጵያዉያን በአዲሶቹ መሪዎች አማካይነት ወደ አዲስ ሥርዓት በሚያሸጋግር አስደናቂ ለዉጥ እና ተሐድሶ ላይ ናቸዉ። ፕሬዝደንት ሳሕለ ወርቅ ዘዉዴና ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ሐገሪቱን እንድጎበኝ ሲጠይቁኝ ግብዣዉን ሳላመነታ የተቀበልኩትም ለዚሕ ነዉ።
ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገዉን የለዉጥ ሒደት ከሩቅ ሆኖ ክብር መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ እኛ አዉሮጳዊያንና ጀርመናዊያን፣ እዚያዉ ስፍራዉ ተገኝተን የዴሞክራሲያዊውን የለዉጥ ጉዞ ማበረታት ይገባናል ብዬ አምናለሁ። ለዚሕም ነዉ ኢትዮጵያን የምጎበኝበት ትክክለኛዉ ጊዜ አሁን ነዉ የምለዉ።»
DW፦ እንዳሉት ኢትዮጵያን በ2014 እንደ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጎብኝተዋታል። አሁን ደግሞ እንደ ፕሬዝደንት «አዲሲቱን ኢትዮጵያ» ይጎበኟታል። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ በየአካባቢዉ የሚደረገዉ ብሔርን የተላበሰ ግጭት ከፍተኛ ሥጋት አሳድሯል። የበርካታ ብሔረሰብ ሐገር የሆነችዉ ኢትዮጵያ አሳሳቢ ፈተና ዉስጥ ናት። ከፕሬዝደንት ሳሕለ ወርቅና ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ጋር በሚያደርጉት ዉይይት ይሕን ጉዳይ ያነሳሉ?

DW-Interview mit Frank-Walter Steinmeier
ምስል DW/R. Oberhammer

ፕሬዝደንት ሽታይንማየር፦ «ከፍተኛ ጉጉት አለን። ግን የዋሕ አይደለንም። ምክንያቱም ጠቅላይ ሚንስትር (ዐብይ) እና ኢትዮጵያዊቱ አቻዬ (ሳሕለ ወርቅ) ያለባቸዉን ፈተና እና ኃላፊነት እናዉቃለን። አፍሪቃን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር በነበረበት ዘመን እንደሚያዉቅ ሰዉ፣ እንደ ፕሬዝደንትም በተወሰነ ደረጃ እንደጎበኛት ሰዉ ለዉጡ ምን ማለት እንደሆነ መገመት አያዳግተኝም።

የረጅም ጊዜ ጠላት ከነበረችዉ ኤርትራ ጋር ሠላም ማዉረድ፣ለአስርተ ዓመታት ተዘግቶ የነበረዉን ድንበር መክፈት፣ በአሸባሪነት ተወንጅለዉ የነበሩ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ከወንጀል ነፃ ማድረግ (መማር)፣ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ ሰላማዊዉን ሕዝብ ለማፈን የዋሉ ሕጎችን ለማሻር ማቀድና ከዚሁ ጋር ካቢኔዉ ዉስጥ የሴቶች እና የወንዶች ዉክልናን ማመጣጠን፣ ይሕ ሁሉ በርግጥ ከኢትዮጵያ ድንበር አልፎ የሚያንጸባርቅ፣ ለአፍሪቃ አብዮታዊ ዉሳኔ ነዉ። እነዚሕ ሁሉ ለዉጦች ግን የሒደቱ መጨረሻ ናቸዉ ማለት አይደለም።

ኢትዮጵያን በመሰለች ትልቅ ሐገር፣ የአሮጌዉ ሥርዓት ቅራኔ አሁንም በሚታይባት፣ ባለፈዉ ጊዜ የተፈጠሩ ልዩነቶች ባልጠበቡባት ሐገር፣ ለዉጡን ከግብ ለማድረስ ፅናት ያስፈልጋል። ሕዝቡም ሊታገስ ይገባል። ለዉጡ መላዉ ሕዝብ የሚቋደሰዉ ፍሬ እስኪፈራ ድረስ  ጊዜ ይጠይቃልና። ሕዝቡ ይታገሳል የሚል ተስፋ አለኝ። አመራሩም በፅናት ይቆማል የሚል ተስፋ አለኝ።»

DW-Interview mit Frank-Walter Steinmeier
ምስል DW/R. Oberhammer

DW፦ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለተያዘዉ ለዉጥ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ግንባር ቀደሙ ተምሳሌት ናቸዉ።ይሁንና በየዕለቱ ከምናነጋግራቸዉ ኢትዮጵያዉን ብዙዎቹ በአንድ ግለሰብ ላይ ይሕን ያክል ኃላፊነት መጣሉ ያሳስባቸዋል። ከዚሕ ይልቅ ተቋማት መጠናከር አለባቸዉ ይላሉ። እንደሚታወቀዉ ኢትዮጵያ በፌደራዊ ሥርዓት የምትተዳደር በመሆንዋ የክልል መንግሥታት ሊጠናከሩ ይገባል ይላሉ። ጀርመን ራስዋ በፌደራዊ ሕገ-መንግሥት የምትመራ በመሆንዋ ለረጅም ጊዜ ወዳጅዋ ለኢትዮጵያ የምታጋራዉ ልምድ ምንድነዉ? 

ፕሬዝደንት ሽታይንማየር፦ «በመጀመሪያ ደረጃ ልንገረም አይገባም። እኛ አዉሮጳዉያንና ጀርመናዉያን ለለዉጥ በሚደረግ ጥረትና የለዉጡን ምርት በመሰብሰብ መካከል ያለዉን ልዩነት እናዉቀዋለን። አዉሮጳና ጀርመን ዉስጥ ያሉ መንግሥታትም ልዩነቱን ለማስወገድ ለረጅም ጊዜ ስንታገል ነበር፤ አሁንም እየታገልን ነዉ። ስለዚሕ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚታይ ብቻ አይደለም። በተለይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይን በተመለከተ የሚገጥማቸዉ ፈተና አለ። አዉሮጳና ጀርመን ወደ ጨዋታዉ የሚገቡትም በዚሕ ወቅት ነዉ፣ የሩቅ ተመልካች ብቻ መሆን የለብንም። ዐብይ የሚከተሉት መንገድ ተገቢ ነዉ ብለን ካመንን ይሕን የእርሳቸዉን መንገድ ማገዝ አለብን።

ጀርመን ከአዉሮጳ ጠንካራ ምጣኔ ሐብት ያላት በመሆንዋ ድጋፍ ማድረግ ከፈለገች ድጋፉ በፖለቲካዊ ትብብር አማካኝነት፣ በማማከርና ተቋማትን በመገንባት ሊደረግ ይችላል። ይሁንና ከዚሕም በተጨማሪ ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ መንግሥታቸዉ፣ ባጠቃላይ ሐገሪቱ የምጣኔ ሐብት ማነቃቂያ ያሻታል። ለዚሕም ነዉ አሁን የምጓዘዉ ብቻዬን ሳይሆን ከኩባንያና ከንግድ ተቋማት ባለቤቶችና ኃላፊዎች ጋር የሚሆነዉ። ከእነዚህ መሐል ገሚሶቹ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸዉ አዉቃለሁ።ይሕም ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በጀመሩት እንዲቀጥሉ ይረዳቸዋል የሚል ተስፋ አለኝ።»

DW፦ የጀርመንን ሚና በተመለከተ፣ ባለፈዉ ሳምንት የፌደራል ጀርመን ምክር ቤት (Bundestag)፣ የሐገሪቱ መንግሥት፣ የኢትዮጵያና የኤርትራን የሠላም ሒደት ለማገዝ የሚያደርገዉን ጥረት እንዲያጠናክር ጠይቋል። አፍሪቃዉያንን ጨምሮ ብዙ ታዛቢዎች፣ ጀርመን አፍሪቃ ዉስጥ እስካሁን ከምታደርገዉ የበለጠ አስተዋፅኦ ማድረግ ትችላለች ብለዉ ያምናሉ።ይሕንን ፍላጎት ለማርካት ጥረታችንን የማናጠናክርበት ምክንያት ምንድነዉ? ለምድነዉ አፍሪቃዉያን ከእኛ የሚጠብቁትን ገቢር ማድረግ ያቃተን?

ፕሬዝደንት ሽታይንማየር፦ «የሚጠበቅብንን አላሟላንም ብዬ አላስብም። ኢትዮጵያ አሁን የጀመረችዉ መንገድ ሊደገፍ ይገባል። የምንሰጠዉ ድጋፍ ምጣኔ ሐብታዊ ይሁን፣ ፖለቲካዊ ይሁን ወይም የኢትዮ-ኤርትራን ግንኙነት ለማጠናከርና የአፍሪቃ ቀንድ አጎራባች ሐገራትን ጨምሮ ለዘላቂ ሠላም የሚጠቅም ይሁን- አይሁን መጀመሪያ ማጤን (መወሰን) ያለበት የኢትዮጵያ አመራር ራሱ ነዉ። ሁለተኛ፣ ከእነዚህ ጉዳዮች ለአንዱ፣ ለሁለቱ ወይም ለሌላዉ የሚያስፈልገዉ ዕርዳታ ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት መለየት ያለባቸዉም የኢትዮጵያ አመራሮች ናቸዉ። በጀርመን በኩል ዝግጅነቱ አይኖርም ብዬ አላስብም።»

DW-Interview mit Frank-Walter Steinmeier
ምስል DW/R. Oberhammer

DW፦ በአሁኑ ጉብኝትዎ ከአፍሪቃ ሕብረት ባለሥልጣናት ጋርም ይነጋገራሉ። ጀርመን ለረጅም ዓመታት የአፍሪቃ ሕብረትን የሠላም እና የፀጥታ ምክር ቤት ትረዳለች። ይሁንና የአፍሪቃ ሕብረት አባል ሐገራት ሠብአዊ መብትን እንዲያከብሩ፣ ምርጫ እንዳያጭበረብሩ፣ (ኮንጎን ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል) የሚቀርብላቸዉን ጥያቄ አይቀበሉትም የሚል ትችት ይሰነዘራል። የለዉጥ ሒደቱም ቅሬታ ይቀርብበታል፤ የገንዘብ አጠቃቀምም ችግር አለበትም ይባላል። እርስዎ ከኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ጋር በሚያደርጉት ዉይይት ይሕን ጉዳይ ያነሳሉ?

ፕሬዝደንት ሽታይንማየር፦ «የአፍሪቃ ሕብረት ከአዉሮጳ ሕብረት ጋር ተመሳሳይ ነዉ። የጋራዉ ተቋም ጠንካራ የሚሆነዉ አባላቱ ጠንካራ ሲያደርጉት ብቻ ነዉ። በዚህም ምክንያት ባለፉት ዓመታት በአፍሪቃ ሕብረት ላይ የሚሰነዘረዉን ትችት እገነዘባለሁ። የዚያኑ ያህል አባላቱ ተገቢዉን ኃላፊነት ካልሰጡት ሕብረቱ ማከናወን ያለበትን ጉዳይ በተገቢዉ መንገድ ማከናወን እንደማይችል ገልጫለሁ። ያም ሆኖ የአፍሪቃ ሕብረት በተለይ በዉጪና ፀጥታን በማስከበር መርሆዎች በኩል ትርጉም የምሰጠዉና የምቀበለዉ መሻሻል እያሳየ ነዉ፣ መሻሻሉ  እንቅፋት እንደማይገጥመዉ ተስፋ አደርጋለሁ። በተለይ ሠላምን በማስከበር ረገድ ሕብረቱ ከ10 እና 20 ዓመታት በፊት ከነበረዉ ጋር ሲነፃፀር በጣም ዉጤታማ እየሆነ ነዉ።»

DW፦ በቅርብ ዓመታት ዉስጥ፣ አፍሪቃ የተሻለ ዕድል አህጉር ናት የሚል አባባል በሰፊዉ እየተሰማ ነዉ። አምና ጀርመን የቡድን 20-የአፍሪቃ ዓመት የተባለዉን ጉባኤ አስተናግዳ ነበር።በዚሁ ጉባኤ ላይ ´ከአፍሪቃ ጋር-ኮምፓክት´ (Compact with Africa) የተባለዉን ጨምሮ የአፍሪቃን ምጣኔ ሐብት ለማሳደግ ይረዳሉ የተባሉ ዕቅድ እና ሐሳቦች ቀርበዋል። የዚያኑ ያሕል ዓለም ስለ አፍሪቃ ያለዉ አመለካከት፣ ኮንጎ ዉስጥ ተከሰተ የተባለዉ የምርጫ ማጭበርበር፤ የደቡብ ሱዳን የርስበርስ ጦርነት፤ ስደተኝነት ናቸዉ። አፍሪቃን በእኩል ዐይን የምናየዉ እንዲያዉ መቼ ይሆን?

ፕሬዝደንት ሽታይንማየር፦ «ማዘዝ አይቻልም። የሚቻለዉ አዉሮጳዉያን ስለ አፍሪቃ ያላቸዉ ግንዛቤ በዕዉቀት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ኃላፊነትን ለመወጣት መሞከር ብቻ ነዉ። ይሕ «አፍሪቃ» የሚለዉን ፅንሰ ሐሳብ ማስረፅን ያካትታል። አፍሪቃ የሚባል አንድ ሐገር የለም። ያሉት የተለያዩ አፍሪቃዉያን (ሐገራት) ናቸዉ። ከዚሕም በተጨማሪ አዉሮጳ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን ከአፍሪቃ ጋር ይበልጥ ማዳበርና ለአፍሪቃ ይበልጥ ደራሽ መሆን አለባት። ለሌለኛዉ ወገን እኩል ክብር የሚሰጠዉ መሆኑን በሚሰማዉ መንገድ የሚደረጉ የትብብር መስኮችን መፈለግና ማጠናከር ያስፈልጋል። በዚሕ ረገድ በአንዳንድ መስኮች ጥሩ ዉጤት አሳይተናል። እንደለመታደል ሆኖ በሌሎች መስኮች አልተሳካልንም።
አዉሮጳዉያን ለመቀራረብና ለመተባበር የሚያደርጉት ጥረት በብዙዎቹ አፍሪቃዉያን በኩልም በወቀሳና ትችት ሳይሆን በመተማመን ፍላጎትና ቁርጠኝነት ይዳብራል የሚል ተስፋ አለኝ። በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነትና የሐሳብ ልዉዉጥ በሁለቱም በኩል የሚደረግ ሒደት ነዉ። ይሁንና ከሁለቱ አንዱ የሆኑት አዉሮጳዉያን የበለጠ አስተዋፅኦ ማድረግ አለባቸዉ።»

DW-Interview mit Frank-Walter Steinmeier
ምስል DW/R. Oberhammer

DW፦ በለዉጥ ዉስጥ ለሚገኘዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለዎት አጭር መልዕክት ምንድነዉ?

ፕሬዝደንት ሽታይንማየር፦-«በመጀመሪያ፣ ለኢትዮጵያዉያን መናገር የምንችለዉ ይሕችን ጥልቅ ትርጉም ያላትን ታላቅ አፍሪቃዊት ሐገር በከፍተኛ ፍላጎት እና በታላቅ አክብሮት የምናያት መሆኑን መናገር እንችላለን።አሁን የሚታየዉ (ለዉጥ) በተለይም የለዉጡ አወንታዊ ዉጤቶች፣ ወደ ዴሞክራሲና ምጣኔ ሐብታዊ መረጋጋት  የሚደረግ በአካባቢዉም የሚንፀባረቅ ፣ለመላዉ አፍሪቃም በጎ አስተምሕሮ ነዉ።ለዚሕም ነዉ አዲሲቱን ኢትዮጵያ ለማጠናከር ኃላፊነታችንን ከተወጣን እዚሕ አዉሮጳ ምናልባትም በአፍሪቃም የሚኖረዉ እድምታ ራሱ ከፍተኛ የሚሆነዉ።ለኢትዮጵያ የምናስተላልፈዉ መልዕክት ደግሞ የተጀመረዉን መንገድ ለማገዝ ዝግጁ ነን።ኢትዮጵያዉያን በጀመሩት መንገድ እንዲቀጥሉ እናበረታታለን።

ሉድገር ሻዶምስኪ እና ነጋሽ መሐመድ

ተስፋለም ወልደየስ