1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ኢትዮጵያዊቷ የላቀ የምርምር ሀሳብ ተሸላሚ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 30 2011

ከበለስ ወይም ቁልቋል ግንድ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት በሚቻልበት መንገድ ላይ ባደረጉት ጥናት መላው የአፍሪካ የገጠሩን ህብረተሰብ ችግር ያቃልላል ተብሎ ይታሰባል።

https://p.dw.com/p/3I7sQ
Dr. Zebib Yenus
ምስል privat

የላቀ ምርምር ሀሳብ አሸናፊ ዶ/ር ዘቢብ የኑስ

በተለያዩ ጉዳዮች የምርምር ሀሳብ ካቀረቡ 700 የአፍሪቃ ተመራማሪዎች መካከል ኢትዮጵያዊቷ ተመራማሪ  ዶ/ር ዘቢብ የኑስ አሸነፉ።  ዶክተር ዘቢብ በአዲግራት ዩኒቨርስቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸዉ። የዶ/ር ዘቢብ የላቀ የተባለው የምርምር ሀሳባቸው  ከበለስ ወይም ቁልቋል ግንድ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት በሚቻልበት መንገድ ላይ ባደረጉት ጥናት ነው። ይህ የምርምር ሀሳባቸው መላው የአፍሪካ የገጠሩን ህብረተሰብ ችግር ያቃልላል ብለውም ያስባሉ። «መጀመሪያ የቀረብነው 700 ሰው ነበርን። ጥሩ የምርምር ንድፈ ሀሳብ ያለው ሰው ነው የነበረው በጣም ፈታኝ ጊዜ ነበር።» የበለስ  ወይም የቁልቋል ግንድ የኤሌክትሪክ ሀይልን በማመንጨት ውድ የሆኑ ዴሚካሎችን ሊተካ የሚችል እንደሆነ በምርምር ሀሳባቸውን ያስረግጣሉ።  
«ንድፈ ሀሳብ ነው ስራው ገና አልተሰራም። በላቦራቶሪ ውስጥ በጣም ውድ የሆኑ ኬሚካሎች እንጠቀማለን። እነዚህን ኬሚካሎች ወጭ ሳናደርግ በለስ የሚባል ተክል አለ። በአዲግራት ከተማ በጣም የታወቀ ፍራፍሬ ነው። ፍሬውን ሳይሆን የምንጠቀመው ግንዱን ነው። ኬሚካሎችን ይተካልናል ብለን ነው ያሰብነው።» የምርምር ሀሳቡ መነሻ ከዚህ ቀደም በጸሀይ ሀይል  ይሰሩ እንደነበር ገልጸው፤ አፍሪካ ባላት የጸሀይ ሀይል ይህን ችግር ሊቀርፍ የሚችል ሀሳብ እንደሆነም ይናገራሉ። የህብረተሰቡን ጤና ከመጠበቅም አንጻር የኤሌክትሪክ ሀይል ንድፈ ሀሳቡ ውጥን ነውም ይላሉ። «የምርምር ሀሳቡ መነሻ ዶክትሬቴን ስሰራ በጸሀይ ዙሪያ ነው የሰራሁት። የጸሀይ ሀይል ያለባት አፍሪቃ፤ ይህ የጸሀይ ሀይል ወደ ተግባር ግን አልዋለም።» በአፍሪካ ገጠር የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍልን ችግር ለመቅረፍ በሚል ሀሳቡን እንደነደፉት ዶ/ር ዘቢብ ይናገራሉ ። 300,000 ፓውንድ (391,275 ግድም የአሜሪካ ዶላር) ሽልማት ያገኙ ሲሆን ለምርምር ድጋፍ እንደሚውልም ገልጸዋል። «ሽልማቱ ለምርምሩ ድጋፍ ይሆናል ተብሎ ነው እንጂ ለግል ጥቅም የሚውል አይደለም።» የኤሌክትሪክ ሀይሉን ለማመንጨት የበለስ ተክል ምርት ብዙ እንደማያስፈልግ ጠቅሰው፤ በአብዛኛው በትግራይ ክልል የሚበቅለው ይሄው ተክል ለስራቸው በቂ ሊሆን እንደሚችል ገልጸውልናል። ይሄው በንድፈ ሀሳብ የተቀመጠው የሀሳብ ፤ ወደ ስራው ለመግባት አምስት ዓመታት እንደሚፈጅ ዶ/ር ዘቢብ ነግረውናል። የምርምር ሀሳቡ መላውን አፍሪቃ ተጠቃሚ ሊያደርግ እንደሚችልም ያምናሉ። 


ነጃት ኢብራሂም

ነጋሽ መሐመድ