ኢትዮጵያዊው ተመራማሪ ዓለም አቀፍ ሽልማት አገኙ

አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:57 ደቂቃ
09.01.2019

ዶ/ር እንዳወቀ የጠፈር ሳይንስ በአዳጊ አገራት በማስፋፋት ይታወቃሉ

መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉት ኢትዮጵያዊው ተመራማሪ ዶ/ር እንዳወቀ ይዘንጋው በጠፈር ሳይንስ በርካታ ምርምሮች አድርገዋል። የጠፍር ሳይንስ ዘርፍ በአዳጊ ሀገራት እንዲስፋፋም የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። የኢትዮጵያዊውን ሳይንቲስት አበርክቶት የገመገመው የአሜሪካ ጂኦፊዚካል ዩኒየን ከወር በፊት የሜዳልያ ሽልማት አበርክቶላቸዋል።

ልጅ እያሉ ነው። በተወለዱበት እና ባደጉባት በሰሜን ኢትዮጵያ፤ አምበር በተባለች አነስተኛ ከተማ አቅራቢያ፤ እረኛም፣ ተማሪም ነበሩ። እስከ አራተኛ ክፍል ከዘለቁ በኋላ ግን ቤት እንዲውሉ የሚያደርጋቸው የቤተሰብ እክል ይፈጠር እና ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ይገደዳሉ። ሁለት የቀበሌ ገበሬ ማህበር ታጣቂዎች እናት እና አባታቸውን አስገድደው አዳጊውን ትምህርት እንዲቀጥሉ ያደርጓቸዋል። በታጣቂ ግፊት ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ የተደረጉት ባለታሪክ ዶ/ር እንዳወቀ ይዘንጋው ይባላሉ።

ደብረማርቆስ አቅራቢያ ከምትገኝ አነስተኛ መንደር ተነስተው ከሰሜን እስከ ደቡብ ዋልታ ያካለሉ ዕውቅ የጠፈር ሳይንስ ተመራማሪ ናቸው። በኖርዌይ እና አውስትራሊያ የሁለተኛ እና የዶክትሬት ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ዶ/ር እንዳወቀ ዛሬ በአሜሪካ ቦስተን ኮሌጅ ይመራመራሉ። 

በጠፈር ሳይንስ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በርከት ያሉ ሽልማቶች ያገኙት ተመራማሪው ባለፈው ታህሳስ ወርም ተመሳሳይ ክብር አግኝተዋል። የአሁኑን ሽልማት አበርካች የአሜሪካ ጂኦፊዚካል ዩኒየን ነው። ዶ/ር እንዳወቀ ሽልማቱን ስለበረከተላቸው ማህበር እና ስለሽልማቱ ምንነት ያስረዳሉ። 

ዶ/ር እንዳወቀ ያገኙት ሽልማት ጆአኒ ሲምሰን በተሰኘችው የመጀመሪያዋ አሜሪካዊት የሜትሮሎጂ ዶክትሬት ተመራቂ ስም የተሰየመ ነው። ኢትዮጵያዊው ተመራማሪ ከ36 ዓመት እስከ 50ዎቹ መጨረሻ የዕድሜ ክልል ውስጥ ላሉ ተመራማሪዎች የሚሰጠውን ይህን ሽልማት ያገኙት እስከዚያን ጊዜ ድረስ በሰሩት ስራ እና ባሳተሟቸው የምርምር ውጤቶች ታይተው ነው። ለሽልማቱ በዋነኛነት ያስመረጣቸው ግን የጠፈር ሳይንስ ትምህርት እና ምርምር በአዳጊ ሀገራት እንዲስፋፋ በማድረጋቸው ነው።

የእርሳቸው ጥረት ተቋዳሽ ከሆኑ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያም እንደምትገኝበት ዶ/ር እንዳወቀ ይናገራሉ። ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት እንዲተከሉ የተደረጉት መሳሪያዎች ምን አይነት ናቸው? የመሳሪያዎቹ ጠቀሜታስ ምንድነው? ዶ/ር እንዳወቀ ምላሽ አላቸው።  

የጠፈር ወይም ህዋ ሳይንስ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደቅንጦት ይወሰዳል። ዶ/ር እንዳወቀ ግን ሳይንሱ ከእኛ ህይወት ርቆ ያለ ነገር ብቻ ሳይሆን ከህዋ ላይ ያለው ነገር በዕለተ ተዕለት ህይወታችን ላይ የሚሳድረውን ተጽዕኖ ጭምር የሚያጠና መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ይላሉ። ጥናቱ የመፍትሄ ሀሳቦችንም ጭምር ያካተተ እንደሚሆንም ይገልጻሉ። አንድ ሀገር ወደፊት ህልውናውን ማስቀጠል ከፈለገ ለጠፈር ሳይንስ ትኩረት መስጠት እንዳለበትም ያስገነዝባሉ። 

ተስፋለም ወልደየስ 

አርያም ተክሌ 


ተዛማጅ ዘገባዎች

ተከታተሉን