1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች በጀርመን

Eshete Bekeleማክሰኞ፣ መስከረም 18 2008

ጀርመን በመገባደድ ላይ በሚገኘው የጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም እስከ 800,000 ስደተኞች ትቀበላለች ተብሎ ይጠበቃል። ከሌሎች የአውሮጳ አባል አገራት አኳያ ለስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች የተሻለ በሯን ክፍት ያደረገችው አገር ፖለቲከኞች ግን ስጋት እየገባቸው ይመስላል።

https://p.dw.com/p/1Gfec
Deutschland Flüchtlinge aus Äthiopien Solomon Mengiste und Yezina Ezezew
ምስል DW/E. Bekele

ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች በጀርመን

በደቡባዊ ጀርመን የባቫሪያ ግዛት ጌፍሪስ ከተሰኘች ከተማ ሰለሞን መንስግስቴና የአምስት ወር ነፍሰ ጡር ባለቤቱ የዝና እዘዘው ከመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ በሚገኝ ለምለም ስፍራ እግራቸውን ያፍታታሉ።

በረጃጅም ዛፎች በተከበበው ውብ አካባቢ አነስተኛ ውኃ ትፈሳለች። ለእነ ሰለሞን ውኃ ለጥም የሚጠጡት፤ ምግብ የሚያበስሉበት አሊያም ልብሳቸውን የሚያጥቡበት ብቻ አይደለም። ከሊቢያ ትርምስ ሽሽት ነፍሳቸውን ሸጠው አውሮጳ የገቡበት መንገዳቸው ጭምር እንጂ።

ጉዞው ወደ አውሮጳ ነው። በተለይም ጀርመን። ከሊቢያዋ የትሪፖሊ ወደብ በመነሳት የሜድትራኒያንን ባህር ለማቋረጥ 3,200 ዶላር ለአሸጋጋሪዎች ከፍለዋል። ፈተናው የጀመረው ግን ገና ከባህር ዳርቻው ነው። ለጉዞ የመረጡት መንገድ በተመሳሳይ ሁኔታ ለመጓዝ የወሰኑ በርካታ መንገደኞችን ህይወት የቀጠፈ ስለመሆኑ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ለሰለሞን ግን ወደ ኋላ መመለስ የሚታሰብ አልነበረም።

Deutschland Flüchtlinge aus Äthiopien Solomon Mengiste und Yezina Ezezew
ምስል DW/E. Bekele

ከጥር ወር ጀምሮ ከ300,000በላይ ስደተኞች የሜድትራኒያን ባህርን በማቋረጥ ወደ አውሮጳ መግባታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን አስታውቋል። ከእነዚህ መካከል 200,000ያህሉ በግሪክ 110,000ደግሞ በጣሊያን በኩል ወደ አውሮጳ የደረሱ ናቸው። ሰለሞን መንግስቴ እና የዝና እዘዘውሌሎች ኢትዮጵያውያን፤ ኤርትራውያንና ሱዳናውያንን ጨምሮ ሰባት መቶ ስደተኞች የጫነችው ጀልባ ጉዞ ሶስት ቀናትን የፈጀ ነበር።

በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም. 219,000ስደተኞች የሜድትራኒያን ባህርን አቋርጠዋል። ይሁንና በሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ለጉዞ ብቁ ባልሆኑ አነስተኛና አሮጌ ጀልባዎች መንገድ የጀመሩ ስደተኞች መካከል ህይወታቸውን ያጡ በርካቶች ናቸው። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ መሠረት በ2014 ዓ.ም. 3,500ስደተኞች በሜድትራኒያን ባህር ላይ ሞተዋል። አልያም የደረሱበት አልታወቀም። እነ ሰለሞንን ጭና ከሊቢያ ወደ አውሮጳ በመጓዝ ላይ የነበረችው የእንጨት ጀልባ ከገጠማት የእሳት አደጋ ብትተርፍም ህይወታቸውን ያጡ ስደተኞችም ነበሩ።

እስከ ታህሳስ ወር መጨረሻ ድረስ እስከ 800,000የሚጠጉ ስደተኞች ወደ ጀርመን ሊደርሱ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለስደተኞቹ የሚያስፈልገው ገንዘብ እስከ 10 ቢሊዮን ዩሮ ወይም 11 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተብሏል። የጀርመን መንግስት ለመጪው ጎርጎሮሳዊ 2016 ዓ.ም. 6 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለማድረግ አቅዷል። የጀርመን ኩባንያዎችም ለስደተኞቹ የሥራ እድል ለመፍጠር ፈቃደኝነታቸውን አሳይተዋል። የመኪና አምራቹ ዳይምለር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዲተር ሲትሸ ኩባንያቸው ወጣትና የመሥራት ተነሳሽነት ያላቸውን ስደተኞች ለመቅጠር መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

ከአምስት ወራት በፊት ጣሊያን የደረሱት ሰለሞንና የዝና ለጉዟቿው ማሳረጊያ የመረጡት ጀርመንን ነበር። ከጣሊያን በባቡር ተጉዘው ሙኒክ ከተማ ሲደርሱም መልካም አቀባበል እንደገጠማቸው ሰለሞን ያስታውሳል።

የዝና ከኢትዮጵያ የወጣችው በሱዳን በኩል አድርጋ ነው። በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ለሶስት አመታት የቤት ሠራተኛ ነበረች። ከሰለሞን ጋር ተዋውቀው ትዳር የመሠረቱትም እዚያው ሱዳን ነው። ከባለቤቷ ጋር የሰሐራ በርሃንና የሜድትራኒያን ባህርን አቋርጣ ጀርመን ጊፍሪስ ላይ ኑሮዋን የመሠረተችው የዝና እዘዘው የአምስት ወር ነፍሰ ጡር ነች። በየወሩ የህክምና ክትትልም እያገኘች ነው።

Deutschland Flüchtlinge aus Äthiopien Solomon Mengiste und Yezina Ezezew
ምስል DW/E. Bekele

አሁን በሚኖሩባት የጊፍሪስ አነስተኛ ከተማ ከሌሎች አገር ከመጡ ስደተኞች ጋር የሚኖሩት ጥንዶች የራሳቸው የመኝታ ክፍል አላቸው። የማብሰያና የመመገቢያ አዳራሻቸው ግን በጋራ ነው። ጥንዶቹ የተገን ማመልከቻቸውን አቅርበው የመጀመሪያውን ቃለ መጠይቅ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ናቸው። የጀርመንኛ ቋንቋ ትምህርታቸውን ለመጀመርም በዝግጅት ላይ ናቸው። ወዳጆችችም አፍርተዋል።

ሰለሞንና የዝና ከኢትዮጵያ ተነስተው ጀርመን እስከገቡበት ጊዜ ድረስ ብዙ ውጣ ውረዶች አሳልፈዋል። የመንገድ አጋሮቻቸው ሲሞቱ ተመልክተዋል። መርዶም ሰምተዋል። ያለፉበት አስቸጋሪ ጉዞ ጠባሳ እንዲሁ የሚጠፋ አይመስልም።

በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ስደተኞች ህይወታቸውን አደጋ ላይ በሚጥሉ መንገዶች ወደ አውሮጳና ጀርመን ለድረስ ይጓዛሉ። አላማቸው ጦርነትና ግጭት ሽሽት፤ እንዲሁም የተሻለ የኑሮና የገቢ ሁኔታ ፍለጋ ነው። መንገዶቹ ግን ሁልጊዜም መልካም አይደሉም። ሞት ከሰሐራ በርሃ፤ ሞት ከሜድትራኒያን ባህር አድፍጧል። ይህን መከራ ተሻግረው ጀርመን የደረሱት ሰለሞን መንግስቴና የዝና እዘዘው ለአዲስ ህይወት ተስፋ ሰንቀዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ