1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ተቀስቅሶ ለነበረው ተቃውሞ ማረሳሻ የታቀደ ነው-ኢትዮጵያውያን

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 25 2009

በሙስና ተጠርጥረው የሚታሰሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ሹማምንት ቁጥር እያሻቀበ ነው። አዲስ የተጨመሩትን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ጨምሮ 45 ግለሰቦች በእስር ላይ ይገኛሉ። የመንግሥት እርምጃ እንዲቀጥል የሚሹ የመኖራቸውን ያክል "ሕዝቡን ለመደለል" የተወሰደ ያሉትም አልጠፉም።

https://p.dw.com/p/2hWWw
Symbolbild Korruption Handschellen auf US Dollar
ምስል Fotolia/ia_64

ኢትዮጵያውያን ምን ይላሉ?

ወደ 4 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ጉዳት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ አድርሰዋል የተባሉት ተጠርጣሪ ሹማምንት እና ነጋዴዎች ቁጥር 45 ደርሷል። ለገዢው ግንባር ቅርበት ያለው ራዲዮ እንደዘገበው ሶስት የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ፅ/ቤት ኃላፊዎች እንዲሁም ሶስት የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ባለሙያዎች በሙስና ተጠርጥረው ታስረዋል።

ተጠርጣሪዎቹን ለፍርድ ቤት ያቀረበው ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በፍርድ ቤት ተፈቅዶለታል። የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ፌዴራል ፖሊስ "በቅንጅት" እያደረጉት ነው በተባለው ዘመቻ የሚታሰሩ ተጠርጣሪዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል መንግሥት ይፋ አድርጓል። የኢትዮጵያ መንግሥት የዘመቻ እርምጃ ግን ወቀሳ እና ድጋፍ እያስተናገደ ነው። እርምጃው በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ተቀስቅሶ ለነበረው ተቃውሞ ማረሳሻ የታቀደ ነው የሚሉም አልጠፉም። 

"በአማራ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል የተነሳበትን አመፅ ለመግታት የታለመ ነው የሚመስለው። እነሱ በአፋቸው እና በወረቀት ሙስናን እንዋጋለን ይላሉ። ተግባር ላይ ግን የለም። በሙስና የተነሳ አገሪቱ በጣም ተጎድታለች። ስለዚህ ለፖለቲካ ፍጆታ ያዋለው ነው የሚመስለው" ይላሉ አንድ ኢትዮጵያዊ። ይኸንንው ኃሳብ የሚጋሩ ሌላ ግለሰብ "ታሰሩ ከተባለ በሙስና ማን እንደተዘፈቀ፤ማን የሀገሪቱን ኃብት እና ንብረት እየበዘበዘ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ የሚያውቀው ይመስለኛል" ሲሉ ያክላሉ። ግለሰቡ የጠቅላይ ሚኒሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መንግሥት የወሰደውን እርምጃ "ማስቀየሻ እና አቅጣጫ የማስለወጥ ሥራ" ሲሉ ይገልጡታል። 

ሊታሰሩ ይገባል የሚሏቸውን ከፍተኛ የመንግሥት ሹማምንት ስም እየጠሩ የአሁኑን እርምጃ የሚያኪያኪሱ አልጠፉም። "የኢትዮጵያ መንግሥት ትንንሾችን ሌቦች ነው ያሰራቸው። ትልልቆቹስ? አገር የዘረፉ ሕዝቡን እያስራቡ፤ሕዝቡን እየዘረፉ ያስቀመጡ ብዙዎች ናቸው። ከትልልቆቹ ከአንበሶቹ ቢጀመር ደስ ይለን ነበር።" ይላሉ የመንግሥት የእስር ዘመቻዎች አልዋጥላቸው ያለ ሌላ ኢትዮጵያዊ። 

የኢትዮጵያ ጠቅላይ አቃቤ-ሕግ በምርመራ ተወስዷል ያሉትን እርምጃ "አህያውን ፈርቶ ዳውላውን" ሲሉ የሚገልጹ ኢትዮጵያዊት በበኩላቸው "ኢሕአዴግ ድራማውን ትንሽ ቆም አድርጎ ይቺን አገር ከችግር ቢያድናት ምንአለበት?" ሲሉ ይማጸናሉ። 
የጠቅላይ ሚኒሥትር ኃይለማርያም መንግሥት የጀመረውን የዘመቻ እስር አምረው የሚተቹ የመኖራቸውን ያክል ይበል ያሉም አልጠፉም።  እነዚህ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው እንደሚሉት "የጸረ-ሙስናው ዘመቻ" ወደ ክልል መንግሥታት እንዲሁም የዞን እና የወረዳ መዋቅሮች ሊወርድ ይገባል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ሹማምንቱን ከነጋዴዎች ጋር በሙስና ወንጀል ጠርጥሮ ሲያስር ይኸ የመጀመሪያው አይደለም። ከአራት አመታት በፊት የገቢዎች እና ጉሙሩክ ሹመኞች እና ነጋዴዎች በተመሳሳይ የጸረ-ሙስና ዘመቻ ታስረው ነበር። የኢትዮጵያ ጠቅላይ አቃቤ-ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ሐምሌ 22/2009 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ‹‹ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች የፖለቲካ ተሿሚዎች ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በዚህ ጉዳይ የሉበትም ባይባልም እንኳን፣ ዋነኛ ሥራቸው ፖለቲካዊ አቅጣጫ መስጠት ነው›› ሲሉ ተናግረው ነበር። 

እሸቴ በቀለ 

አርያምተክሌ