1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

Merga Yonas Bula
ረቡዕ፣ ግንቦት 16 2009

ባለፈዉ ሳምንትም በኢትዮጵያ በተካሄደዉ 46ኛዉ የአትሌትክስ ሻምፕዮን በ84 አትሌቶች ላይ ምርመራ ተደርጎ የደም ናሙና  ተወስዷል።  እስካሁን በዚህ ዓመት ባጠቃላይ ከ350 በላይ አትሌቶች በምርመራ ላይ እንደሚገኙ የመስሪያ ቤቱ ስራ አስኪያጅ ለዶይቸ ቬሌ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/2dWh8
Deutschland Beschlagnahmte Dopingware von der Zollfahndung in Köln
ምስል DW/L. Binder

Ethiopian Athletes Doping Test - MP3-Stereo

የኢትዮጵያ አትሌቶች አበረታች ንጥር ነገር ይጠቀማሉ በሚል ጥርጣሬ የተሰማው ባለፈዉ ዓመት ነበር። ይህን ጥርጣሬ ያሰሙት የዓለም አቀፉ የፀረ-ሐይል ሰጪ መድሐኒት ተቆጣጣሪ ተቋም /WADA/ እና ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማህበር /IAAF/ ኢትዮጵያ በአትሌቶችዋ ላይ ሰፊ ምርመራ እንድታደርግ ጠይቀው፣ ይህን የማታደርግ ከሆነ ከአትሌትክስ ዉድድሮች እንደምትታገድ አስጠንቅቀው ነበር።

ይህንንም ተከትሎ እንደ አዲስ የተዋቀረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-ሐይል ሰጪ መድሐኒት ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት /NADO/ ረቅቅ ሕግ ማዘጋጀቱን፣ ለምሳሌ አትሌቶች ህመም ወይም ጉዳት ሲያጋጥማቸዉ በተከለከሉ መዲሃኒት ጭምር መጠቀም የሚችሉበትን ስርዓት መዘርጋቱን የመስሪያ ቤቱ ስራ አስከያጅ አቶ መኮንን ይደርሳል ለዶይቸ ቬሌ ተናግረዋል።

አቶ መኮንን ባለፈዉ ሳምንት በተካሄደዉ በ46ኛዉ የኢትዮጵያ አትሌትክስ ቻምፕዮን ላይ ከማክሰኞ እስከ እሁድ ከ84 አትሌቶች ለምርመራ የተወሰደው የደም ናሙና ፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ወደሚገኘዉ ቤተ ሙከራ ተልኮ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን እና ዉጤቱ ከ10 የስራ ቀናት በኋላ እንደሚታወቅ አቶ መኮንን አስታውቀዋል። 
የመስሪያ ቤቱ መቋቋምና እያካሄደው ያለው ስራም ጥሩ ጅማሮ ነዉ ያሉት የስፖርት አማካሪዉ አቶ ኤልሻዳይ ነጋሽ ዉድድር እስካለ ድረስ የፀረ-ሐይል ሰጪ መድሐኒት ምርመራ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል። ከደም ናሙና መዉሰድ እስከ ዉጤት ማሳወቅ ድረስ ያለዉ የምርመራ ሂደት እንዴት እንደሚከናወን አቶ ኤልሻዳይ አስረድተዋል።

የዓለም አቀፉ የፀረ-ሐይል ሰጪ መድሐኒት ተቆጣጣሪ ተቋም /WADA/ ባላፈዉ ዓመት በዘጠኝ ኢትዮፕያውያን አትሌቶች ላይ ምርመራ ማድረጉ ይታወሳል። ከነዚህም መካከል ሶስቱ አበረታች ንጥር ነገር መጠቀማቸዉን ተረጋግጦባቸው ከዉድድር እንደታገዱ በወቅቱ የወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ።

መርጋ ዮናስ

አርያም ተክሌ