1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀናድሪያ ፌስቲቫል ከሚሊዮን በላይ ጎብኚ አለው

ሰኞ፣ የካቲት 19 2010

በሳዑዲ ዓረቢያ መዲና ሪያድ በየዓመቱ የሚከበረው የጀናድሪያ የባህል የታሪክ እና የቅርስ ፌስቲቫል ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ያስተናገዳል፡፡ በዘንድሮው ሰላሳ ሁለተኛው ፌስቲቫል ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሪያድ በሚገኘው ኤምባሲዋ እና በሪያድና አካባቢው በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ተወክላ ለሶስት ቀናት ተሳትፋለች፡፡

https://p.dw.com/p/2tMtf
Saudi Arabien - Janadriyah Festival
ምስል DW/S. Shiberu

የጀናድሪያ ፌስቲቫል ከሚሊዮን በላይ ጎብኚ አለው

በሰሜናዊ ሪያድ አርባ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የጀናድሪያ አካባቢ በሚገኝ እጅግ ሰፊ ቦታ ላይ ነው ዓመታዊው የጀናድሪያ ፌስቲቫል የሚከበረው፡፡ መጠሪያውንም ያገኘው ከሚከበርበት ቦታ ላይ ነው፡፡ አዘጋጆቹ ይፋ እንዳደረጉት እስከ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ጎብኚ በሶስት ሳምንት ቆይታው ጀናድሪያን ተመልክቷል፡፡ በተለይ አስከምሽቱ ስድስት ሰዓት ጀናድሪያ በሰው እንደተጨናነቀች ሶስት ሳምንት ሰንብታለች፡፡ ንጉስ ሰልማን ቢን አብዱል አዚዝም አንዱን ምሽት ከነ ቤተሰቦቻቸው ታዳሚ ነበሩ፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ እንደ ታላቅ ክስተት በምትወስደው ዓመታዊው የጀናድሪያ ፌስቲቫል ጥንታዊ ታሪክ እና ባህሏን ከዘመናዊ ስልጣኔዋ ጋር ጎን ለጎን ይዛ ትቀርባለች፡፡ ከጥንታዊ ግመሎቿ እስከ ዘመናዊ አውቶ ሞቢሎቿ በአካልም በፎቶ ግራፍም ይታደማሉ፡፡ ከጥንታዊው ጦር እና ጎራዴ እስከ ዘመናዊ ሚሳይል እና ብረት ለበስ ታንኮቿ ጭምር የፌስቲቫሉ አካል ነበሩ፡፡ 

Saudi Arabien - Janadriyah Festival
ምስል DW/S. Shiberu

በዲፕሎማሲው መስክ ያለፉባቸውን ጉዞም ሆነ ዛሬ የደረሱበትን ደረጃ ፤ በጉምሩክ እና አደንዛዥ እጽ ቁጥጥር እና ክትትል ከባህላዊው ጀምሮ ዛሬ እስከደረሱበት ስልጡን እና ብቁ የተባሉ አነፍናፊ ውሾቻቸው ድረስ በአካል አቅርበው ለታዳሚው አሳይተዋል፡፡ 

ያለፈው ዓመት የክብር እንግዳ ጀርመን ነበረች ፡፡ የዘንድሮዋ ህንድ ነች ፡፡ የክብር እንግዳው ሰፊ ቦታ ይዞ ሶስቱንም ሳምንት ጎብኚዎችን ይቀበላል፡፡ ሌሎች ሀገሮች ደግሞ እንደየ ቀረቤታቸው ለሶስት ቀናት ቦታ ይሰጣቸዋል ፡፡ ለኢትዮጵያም የመጨረሻዎቹ ሶስት ቀናት ተሰጥተዋታል ፡፡ የመጨረሻዎቹ ቀናት ጎብኚ የሚጎርፍባቸው በመሆኑ ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚ ነበር የሆነላት፡፡ አምባሳደር አሚን አብዱል ቃድር በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ መንግስት ልዩ መልዕክተኛ እና ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ናቸው፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ተሳትፎ ማብራሪያ አላቸው።

አቶ መሀመድ ሀሰን የጀናድሪያ ፌስቲቫል ሲመሰረት ጀምሮ እዚሁ ሪያድ ነበሩ፡፡ ባለፉት 32 ዓመታትም በየ ዓመቱ ይመጡ ነበር ዘንድሮ ኢትዮጵያ ቦታ በማግኘቷ ተደስተዋል፡፡ አቶ ሻወል ጌታሁን ደግሞ ዋና ጽህፈት ቤቱ አዲስ አበባ የሆነውን የቱሪዝም እና የጉዞ ወኪላቸውን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ይናገራሉ፡፡

Saudi Arabien - Janadriyah Festival
ምስል DW/S. Shiberu

በሰላሳ ሁለተኛው የጀናድሪያ ፌስቲቫል ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው ኢትዮጵያም ሪያድ በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማህበርን የኢትዮጵያ ዓለም ዓቀፍ ትምህርት ቤትንም ሆነ በሪያድ እና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር ለሶስት ቀናት ተሳትፎ አድርጓል፡፡ በተለይ የቡና ስነስርዓቱ እና የተማሪዎቹ ባህላዊ ውዝዋዜ የብዙዎቹን ጎብኚዎች ቀልብ የሳበ ነበር ፡፡ 

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ስለሺ ሽብሩ 
ነጋሽ መሐመድ