1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አበረታች መድኃኒት እና የኢትዮጵያ ቅጣት

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 21 2009

ኢትዮጵያ አበረታች መድኃኒት ተጠቃሚዎችን እድሜ ልክ ከውድድር እንደምታግድ አስታወቀች። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አትሌት ኃይሌ ገብረ ስላሴ በአበረታች መድኃኒት ላይ ትዕግስት የለንም ብሏል። 

https://p.dw.com/p/2V4Kx
አበረታች መድኃኒት እና የኢትዮጵያ ቅጣት
ምስል Getty Images

Ethiopia set to impose lifetime bans on athletes who fail doping tests - MP3-Stereo

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኃይሌ ገብረ ስላሴ አበረታች መድኃኒቶች  የሚጠቀሙ አትሌቶችን እድሜ ልክ ከውድድር እንደምታግድ አስታውቋል። ስኬታማ የረጅም ርቀት ሯጮችን በማፍራት የምትታወቀው ኢትዮጵያ በአበረታች መድኃኒት ምርመራ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማኅበራት ፌዴሬሽን በዓይነ ቁራኛ ከሚከታተላቸው አገሮች መካከል አንዷ ናት። አዲሱ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ለአበረታች መድኃኒት ተጠቃሚ አትሌቶች ትዕግስት የለንም ሲል ተናግሯል። ኢትዮጵያ አበረታች መድኃኒቶች የሚጠቀሙ አትሌቶችን የሚቀጣ ጠንካራ ህግ እንዳላት የሚናገረው ጋዜጠኛ ኤልሻዳይ ነጋሽ እርምጃውን መልካም ብሎታል።
የኢትዮጵያ ውሳኔው አበረታች መድኃኒቶች በተጠቀሙ አትሌቶች ላይ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማሕበራት ፌዴሬሽን ከሚጥለውም ቅጣት የከፋ ነው። ዓለም አቀፉ አስተዳዳሪ አካል አበረታች መድኃኒት መጠቀማቸው በምርመራ የተረጋገጠባቸውን አትሌቶች ለአራት አመታት ከውድድር ያግዳል። አትሌቶቹ ቅጣታቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ ውድድር መድረክ መመለስ ይመለሳሉ። ኢትዮጵያ የሽንት እና የደም ናሙናዎችን ከአትሌቶች መሰብሰብ ብትችልም መመርመር አትችልም። ጋዜጠኛው ኤልሻዳይ ነጋሽ ይሕ ፈተና እንደሚሆን ይናገራል። 
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክ ማኅበራት ፌዴሬሽን የአበረታች መድኃኒትን ቁጥጥራቸው ልል ነው ካላቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ ይገኙበታል። የአበረታች መድኃኒት ምርመራ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ ሲሆን ብሪታኒያ እና ዩናይትድ ስቴትስን የመሳሰሉ አገራት በተደጋጋሚ በአትሌቶቻቸው ላይ ምርመራ ያደርጋሉ። ዓለም አቀፉ የአበረታች መድኃኒቶች ቁጥጥር ድርጅት ለ31 ላብራቶሪዎች ምርመራ የማድረግ እውቅና የሰጠ ሲሆን አንዳቸውም በአፍሪቃ ውስጥ አይገኙም። 


እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ