1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ከባህርዳሩና ከአዲስ አበባው የባለሥልጣናት ግድያ በኋላ

ሰኞ፣ ሐምሌ 1 2011

መንግሥት በግድያው እጃቸው አለበት ብሎ የጠረጠራቸውን ግለሰቦች በጅምላ እያሰረ መሆኑ ይሰማል።ፍርድ ቤት የቀረቡም አሉ።ይህም ባለፈው አንድ ዓመት በሀገሪቱ በወንጀል የሚጠረጠሩ ለምን አይያዙም ለሚሉ ተደጋጋሚ አቤቱታዎች«ሳናጣራ በጅምላ አናስርም» ይል የነበረውን መንግሥት ለትችት መዳረጉ አልቀረም።ጥቃቱን የተከተለው የመንግሥት እርምጃ እያነጋገረ ነው

https://p.dw.com/p/3LhPX
Äthiopien Amhara | Beerdigung in Bahrdar
ምስል DW/A. Mekonnen

ኢትዮጵያ ከባለሥልጣናቱ ግድያ በኋላ

ከሁለት ሳምንት በፊት በባህርዳር እና በአዲስ አበባ የተፈጸመው የከፍተኛ ባለሥልጣናት ግድያ  ባለፈው አንድ ዓመት ኢትዮጵያ  ውስጥ በነበረው አንጻራዊ ነጻነት ላይ ጥላ ያጠላ ይመስላል።ግድያው ያስከተለው ድንጋጤና እና አለመረጋጋት ከቀን ወደ ቀን እየቀነሰ በመሄድ ላይ ቢሆንም ስጋቱ ግን የጠፋ አይመስልም።መፈንቅለ መንግሥት የተባለው የባህር ዳሩ ግድያ እና የአዲስ አበባው ጥቃት ግንኙነት አለው ሲሉ የነበሩት የመንግሥት ባለሥልጣናት ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ግን ግንኙነት ይኑረው አይኑረው እየተጣራ ነው ብለዋል።ይሁንና የዛሬ 15 ቀን ስለሆነው ብዙ መልስ ያላገኙ ጥያቄዎች እና መላ ምቶችም በየአቅጣጫው መሰንዘራቸው ቀጥሏል።መንግሥት በግድያው እጃቸው አለበት ብሎ የጠረጠራቸውን ግለሰቦች አማራ ክልል እና አዲስ አባባን ጨምሮ ከተለያዩ አካባቢዎች በጅምላ እያሰረ መሆኑ ይሰማል።ፍርድ ቤት የቀረቡም አሉ።ይህ ደግሞ ባለፈው አንድ ዓመት በሀገሪቱ በወንጀል የሚጠረጠሩ ለምን አይያዙም ለሚሉ ተደጋጋሚ አቤቱታዎች«ሳናጣራ በጅምላ አናስርም» ይል የነበረውን መንግሥት ለትችት መዳረጉ አልቀረም።የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው እንደተናገሩት መንግሥት አሁን ትዕግስቱ አልቋል።እርምጃውም እንደበፊቱ ለዘብተኛ ሳይሆን ይጠናከራል።ከዛሬ ሁለት ሳምንቱ ጥቃት በኋላ መንግሥት በመውሰድ ላይ ያለው  እና ወደፊትም እወስደዋለሁ የሚለው  እርምጃ እያነጋገረ ነው።ከዛሬ ሁለት ሳምንቱ ግድያ በኋላ የተከተሉ ሁነቶች እና አንድምታቸው የመወያያ ርዕሳችን ነው። ሦስት እንግዶች ጋብዘናል፣እነርሱም አቶ መሱድ ገበየሁ የኢትዮጵያ የመብት ድርጅቶች ህብረት ሃላፊ እና የሕግ ባለሞያ፣አቶ ፍስሀ ተክሌ በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳዮች ተመራማሪ እንዲሁም  አቶ ያሬድ ጥበቡ አሜሪካን የሚኖሩ የፖለቲካ ተንታኝ ናቸው።

Abiy Ahmed Äthiopien
ምስል picture-alliance/AP Photo

ሙሉውን ውይይት ለማዳመጥ ከታች የሚገኘውን የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ   

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ