1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ከድጡ ወደ ማጡ

Negash Mohammedሰኞ፣ ነሐሴ 30 2008

የሐይሉ እርምጃ እስካሁን ካደረሰዉ የበለጠ ጉዳት እንዳያደርስ ብዙዎች ይፀልያሉ።ይመክራሉ።መፍትሔም ይጠቁማሉ።አቶ ግርማ ከመፍትሔ ጠቋሚዎቹ አንዱ ናቸዉ። መፍትሔዉም አቶ ግርማ እንደሚሉት ቀላል ነዉ።የመብት ተሟጋች ያሬድ ሐይለ ማርያምም መፍትሔዉ «በመንግሥት እጅ» ነዉ ባይ ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/1Jw6u
Äthiopien Protest
ምስል Reuters/T. Negeri

ኢትዮጵያ፤ ከድጡ ወደ ማጡ

ኢትዮጵያ፤ እንደ ሐይማኖታዊዉ ስንክሳር፤ ከብዙዉ ዓለም ቀድማ ሰወስቱን ትላልቅ ሐይማኖቶች የተቀበለች፤ የሐይማኖተኞች ሐገር ናት።በቅርብ ዘምን ታሪኳ ሐይማኖተኛ፤ ደካማ፤ ትጥቅ አልባ፤ አንዳዴም ክፉ-ደጉን ያለዩ ዜጎችዋ ሲገደሉ፤ ሲቆስሉ፤ ሲጋዙ ግን «ሐይ» ባይ የሐይማኖት መሪ አልነበራትም፤ የላትምም።ካለም አልተሰማም።ኢትዮጵያ፤ እንደ ፖለቲካዊዉ ታሪክ፤ ለዓለም ሠላም «የቆሙ» የተባሉ፤ ከሊግ ኦፍ ኔሽንስ እስከ የተባበሩት መንግሥታት ማሕበራትን የመሠረተች፤ ከኮሪያ ልሳነ-ምድር እስከ ደቡብ አፍሪቃ ለዓለም ሐያላን ጥቅም መከበር የተዋጋች፤ለጭቁኖች ነፃነት የታገለች ሐገር ናት።ዜጎችዋ ሲገዳደሉ ወይም ሲገደሉ ግን የደረሰላቸዉ አልነበረም።የለምም። ኢትዮጵያዉያን እራሳቸዉስ?

ሕዳር የጀመረዉ የአደባባይ ሰልፍ፤ አድማ፤ ተቃዉሞ ጥያቄ ሥፍራ-መልኩን እየቀያየረ ቀጥሏል።እሳቸዉ ጡረተኛ ሐምሳ አለቃ ናቸዉ።ተቃዉሞዉ ከቀጠለባቸዉ ያንዷ ከተማ ነዋሪ።

የፀጥታ አስከባሪዎች የሐይል እርምጃም ጡረተኛዉ አባት እንዳሉት እየከፋ መጣ።

Girma Seifu von der UDJ-Partei in Äthiopien
ምስል DW/G.T. Hailegiorgis

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ሥለ ጉዳዩ እስተያየት እንዲሰጡትን ያደረግነዉ ሙከራ አልተሳካልንም።ለኢትዮጵያ መንግሥት ጠንካራ ድጋፍ የምትሰጠዉ የዓለም ብቸኛ ልዕለ ሐያል ሐገር ዩናይትድ ስቴትስ ግን ልክ እንደ ጡረተኛዉ ሽማግሌ ሁሉ «አስጊ» ብላዋለች።አሳሳቢ፤ በጣም አሳሳቢ፤ አስጊ፤ በጣም አስጊ እጅግ በጣም አስጊ የሚሉ ቃላትን ከዋሽግተን ወይም ብራስልስ መስማት በርግጥ ብርቅ አይደለም።ግን እስከ መቼ?

ጊዜዉ ደግሞ ይሮጣል።2008ን ልንሰናበት ዕለታት ቀሩን።የቀድሞዉ የምክር ቤት እንደራሴ አቶ ግርማ ሰይፉ አሮጌዉን ዘመን «ኢሕአዴግ የዘራዉን ያጨደበት» ይሉታል።

አጨዳዉ የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት፤ አካል ማጥፋቱ ነዉ አሳዛኙ።ይላሉ የማሕበር ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ኃይለማርያም።ቂሊጦ ወሕኒ ቤት የታሰሩ ሳይቀሩ በቃጠሎ ሰበብ በጥይት ተደብድበዉ ተገድለዋል።የሟቾቹን ቁጥር አንዳዶች አርባ፤ ሌሎች ሃያ ይሉታል።

በእስካሁኑ ተቃዉሞ እና ግጭት የደረሰበት ያልታወቀ፤ የቆሰለ፤የታሰረዉን ሰዉ በትክክል የቆጠረዉ የለም።የሳቸዉ ልጅ ግን ከቆሰሉት አንዱ ነዉ።የዘጠኝ ዓመት ልጅ።

ቃዉሞ፤ግድያ፤ እስራቱ የሚቆምበት ሥልት፤ይቆማል የሚለዉም ተስፋ ላሁኑ ተስፋ የሚጣልበት አይደለም።የሚታወቀዉ የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ «ብር» ምናልባትም «ዶላር በጆንያ ይታደላቸዋል» ያሏቸዉ ወገኖች ይጭሩታል ያሉትን ተቃዉሞ ለማስቆም ጦር ሐይላቸዉን ማዘዛቸዉ ነዉ።የሚታወቀዉ፤ ለተቃዉሞ የታደመዉ ሕዝብ ጥያቄ ሁነኛ መልስ አለማግኘቱ ነዉ።

Äthiopien - Proteste gegen die Besitzstände im Land
ምስል Reuters/T. Negeri

የወልቃይ ጠገዴ ወረዳ በአማራ መስተዳድር እንዲካለል የሚጠይቀዉ ኮሚቴ ጊዚያዊ ሰብሳቢ አቶ ተሻገር ወልደሚካኤል እንደሚሉት የጠቅላይ ሚንስትሩ ትዕዛዝ እና ቢያንስ የሳቸዉ ኮሚቴ ያቀረበዉ ጥያቄ ሁነኛ መልስ አለማግኘቱ ተቃዉሞዉን አጠናክሮታል።ግጭት ግድያዉንም እንዲሁ።የቀድሞዉ የምክር ቤት እንደራሴ አቶ ግርማ ሰይፋ «የማሪያም መንገድ ሲዘጋ፤ የገብሬል መንገድ ይከፈታል» ይላሉ።

የሐይሉ እርምጃ እስካሁን ካደረሰዉ የበለጠ ጉዳት እንዳያደርስ ብዙዎች ይፀልያሉ።ይመክራሉ።መፍትሔም ይጠቁማሉ።አቶ ግርማ ከመፍትሔ ጠቋሚዎቹ አንዱ ናቸዉ። መፍትሔዉም አቶ ግርማ እንደሚሉት ቀላል ነዉ።የመብት ተሟጋች ያሬድ ሐይለ ማርያምም መፍትሔዉ «በመንግሥት እጅ» ነዉ ባይ ናቸዉ።የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ብሔርተኝነት ኮሚቴ አባል አቶ ሙላዉ ከበደ ግን ተስፋ የቆረጡ ይመስላሉ።

መፍትሔዉ በዘገየ ቁጥር ግድያ፤እስራት፤ አፈናዉ እየቀጠለ፤ ተቃዉሞዉ እየተጠናከረ ምናልባትም እንዲሆን የማይፈለገዉ የሚሆንበት ጊዜ እንዳይቃረብ ያሰጋል።በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እየተደጋገሙ የመጡት ዘርን የተላበሱ ፖለቲካዊ ትችት፤ ወቀሳ፤ ተራ ስድብ፤ ቧልቶች ጤናማ መልዕክት የላቸዉም።አቶ ግርማ ሰይፉ ዘርን ለተላበሰዉ ጥላቻ-እንኪያ ሰላንቲያ ዋና ተጠያቂዉ ሕወሐት ነዉ-ይላሉ።ለጊዜዉ ፆም-ፀሎቱ፤ ምልጃ-ምክር-የመፍትሔዉ ሐሳብም ሰሚ አላገኘም።ግን እስኪ ደጉን እንመኝ።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ