1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞች መጨመር

ሐሙስ፣ ጥቅምት 28 2006

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በምህፃሩ «ዩ ኤን ኤች ሲ አር» በጎርጎሮሳውያኑ 2013 ዓም ከጎረቤት ሃገራት ወደ ኢትዮጵያ የፈልሱ ስደተኞች ቁጥር መጨመሩን አስታወቀ ።«ዩ ኤን ኤች ሲ አር» እንደሚለው የስደተኞቹ ቁጥር ወደፊትም ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል ።

https://p.dw.com/p/1ADpx
ምስል DW/Getachew Tedla Hailegeorgis

በኢትዮጵያ የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ክሱት ገብረ እግዚአብሔር ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ወደ ኢትዮጵያ የሚፈልሱት ስደተኞች ቁጥር ከፍ እያለ የመጣው በአካባቢው ሃገራት በሚከሰቱ ግጭቶችና አለመረጋጋት ምክንያት ነው ። «ዩ ኤን ኤች ሲ አር» እንደሚለው ከጎረቤት ሃገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚፈልሱ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ የመጣው በተለይ ባለፉት 2 ዓመታት ነው ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከ 100 ሺህ በላይ የሶማሊያ ስደተኞች ኬንያ ድንበር ላይ ወደ ሚገኘው የዶሎ አዶ የስደተኞች መጠለያ ገብተዋል ። በዚሁ ጊዜ ወደ አፋርና ትግራይ የፈለሱ የኤርትራ ስደተኞች እንዲሁም በአሶሶ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የሱዳን ስደተኞች ቁጥርም ከፍተኛ ነው ። አቶ ክሱት ገብረ እግኢአብሔር በኢትዮጵያ የ«ዩ ኤን ኤች ሲ አር» የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ከጎረቤት ሃገራት የመጡ ስደተኞች ቁጥር ከአምናው በጣም ከፍ ማለቱን ነው የሚናገሩት ። ፍልሰቱ በዚህ መልኩ ከቀጠለ በጎርጎሮሳውያኑ 2013 መጨረሻ ፣ ከአካባቢው አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት ስደተኞች ቁጥር ከፍ እንደሚል ይጠበቃል ። እንደ አቶ ክሱት በጎርጎሮሳውያኑ 2013 ዓም ከሌሎቹ ዓመታት በተለየ ባልተለመደው ወቅት ሁሉ በርካታ ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ ተሰደዋል ። ከሶማሊያና ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የገቡትም ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም ። የሶማሊያና የሱዳን ህዝብ የሚሰደደበት አብዩ ምክንያት ግጭትና አለመረጋጋት መሆኑን የተናገሩት አቶ ክሱት ለግጭቱ አካባቢያዊ ና አህጉራዊ ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊፈለግለት እንደሚገባም ጠቁመዋል ። በርሳቸው አስተያየት ዘላቂው መፍትሄ ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ ነው ።

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ