1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ቀዉስ እና ኢሕአዴግ

ሰኞ፣ መጋቢት 17 2010

ከሰማይ በታች ያሉ ችግሮችን የሚፈታ ዉሳኔ የፀደቀበት፤ ልዩነቶችን ያጠበበ መንፈስ የሰፈነበትን ስብሰባ የመሩት፤ የስብሰባዉን ጥሩ ዉጤት የነገሩን ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ያሉት በርግጥ እንዳሉት ከነበረ ወር ሳይቆዩ ሥልጣን መልቀቅ ነበረባቸዉ? ሰሚ በሌላባት ሐገር ጥያቄ እንጂ በርግጥ መልስ  የለም።

https://p.dw.com/p/2v1n0
Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Englisch

የኢትዮጵያ ቀውስ እና ኢህአዴግ

የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ኢሕአዴግ መሪዎች ክረምቱ ላይ ተሰብስበዉ ነበር።ጥልቅ ያሉትን ተሐድሶ ለማድረግ ወሰነዉ ስብሰባዉን አበቁ።ታሕሳስ ላይ እንደገና ተሰበሰቡ።አስራ ሰባት ቀን። ስብሰባዉን ሲያበቁ «ከሰማይ በታች» ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ተስማማን አሉ።ሐገሪቱ ሕጋዊ መሪ የላትም።መሪ መምረጥ ወይም መሰየም የሚገባቸዉ ሹማምንት ከታሕሳሱ ስብሰባቸዉ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመደንገግ «እረፍት» ካደረጉ በኋላ እንደገና ስብሰባ ተቀመጡ።መጋቢት ሁለት።ሰዎች ከሞያሌ እስከ ነቀምት ይገደላሉ።ይሰደዳሉ።ከወሊሶ እስከ ባሕርዳር፤ ከድሬዳዋ እስከ አዲስ አበባ ይታሰራሉ።ኢትዮጵያ የስብሰባ-እስራት፤ የፍርሐት መሸመቃቂያ ምድር ሆነች እንበል ይሆኝ?።

                                  

አዲስ አበባ በርግጥ የስብሰባ ከተማ ናት።የአፍሪቃ ሕብረት ስብሰባ፤ የኢጋድ ስብሰባ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ።የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሥብሰባ።ብዙ ነዉ።የኢትዮጵያ መንግስትን በመቃወም  ሕዝባዊ አመፅ በይፋ  ከተቀሰቀሰ ከሕዳር 2008 ወዲሕ ግን እንደ ኢሕአዴግ መሪዎች በስብሰባ ማግስት ስብሰባ የተቀመጠባት የለም።

እንደ በፊቱ ሁሉ 2009 ማብቂያ ስብሰባ ነበር።የኢሕአዴግ መሪዎች ስብሰባ።2010 አዲስ አመት ሲባል አዲስ ዉሳኔ ወይም ቃል ነበር።መልካም አስተዳደር የማስፈን፤ የተሐድሶ ለዉጥ ያዉም ጥልቅ ለዉጥ የማድረግ ቃል።ቃል ገቢር ሳይሆን ሌላ ስብሰባ ተጠራ።ታሕሳስ።ከአስራ-ሰባት ቀናት በኋላ ሌላ ቃል ሰማን።

Äthiopien Addis Abeba Mahnwache nach Protest
ምስል DW/G. Tedla

                                       

ከሰማይ በታች ያሉ ችግሮችን የሚፈታ ዉሳኔ የፀደቀበት፤ ልዩነቶችን ያጠበበ መንፈስ የሰፈነበትን ስብሰባ የመሩት፤ የስብሰባዉን ጥሩ ዉጤት የነገሩን ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ያሉት በርግጥ እንዳሉት ከነበረ ወር ሳይቆዩ ሥልጣን መልቀቅ ነበረባቸዉ? ሰሚ በሌላባት ሐገር ጥያቄ እንጂ በርግጥ መልስ  የለም።የታሕሳሱ ስብሰባ አሥራ-ሰባት ቀን መቆየቱ ጉድ አሰኝቶ ነበር።መጋቢት 2 የተጀመረዉ ያሁኑ ስብሰባ ደግሞ አንዴ ስራ-አስፈፃሚ ሌላ ጊዜ ምክር ቤት እያለ እነሆ ዛሬ አስራ-አምስተኛ ቀኑን ያዘ።የተለመደዉ ቃል፤ተስፋ እንኳን የለም።ምክንያት?

                               

ይላሉ ፕሮፌሰር መሐመድ አባጀበል ጣሒሮ።የቀድሞዉ የሕዝባዊ ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሐት) መስራች እና የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ የምክር ቤት አባል ዶክተር አረጋዊ በርሔ በበኩላቸዉ የትርምስ ጊዜ ይሉታል።የትርምስ ስብሰባ።

 የኢሕአዴግ መሪዎች በየስብሰባቸዉ ማብቂያ አማላይ ተስፋ ከሰጡ በኋላ ተመልሰዉ ለሌላ ስብሰባ በር የሚዘጉበት ምክንያት ዶክተር አረጋዊ እንደሚሉት ሐገር የመምራት፤ ችግር የመፍታት፤ የሕዝብ ጥያቄን የመመለስ ፍላጎትም አቅምም  ስለሌላቸዉ ነዉ።

 ታዛቢዎች እንደሚሉት ስብሰባዉ የኢትዮጵያን ሕዝብ የዴሞክራሲ፤የፍትሕ፤ እኩልነት፤ በነፃነት የመኖር እና የመናገር መብት ጥያቄን  ለመመለስ የሚረዱ ዉሳኔዎች ይተላለፉበታል ብሎ የሚጠብቅ የለም።ይሁንና መሪዎቹ ቢያንስ እንደ ሊቀመንበር የሚመራቸዉ እና ሐገሪቱን እንደጠቅላይ ሚንስትር የሚወክል ፖለቲከኛ ይሰይማሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነዉ።ሊቀመንበር እና ጠቅላይ ሚንስትር መሰየሙ ዘግይቷል ግን የሚቀር አይደለም።

የሚመረጠዉ ጠቅላይ ሚንስትር ማንነት ተሰብሳቢዎችን ማወዛገቡ ለስብሰባዉ መራዘም እንደዋና ምክንያት የሚጠቅሱ ተንታኞች አሉ።በተለይ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለዉጥ አራማጅ ከሚባሉት ከኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ  ድርጅት ኦሕዴድ እንዲሰየም ይፈልጋሉ በሚባሉት የኦሕዴድ መሪዎች እና በሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሐት) መሪዎች መካከል የተፈጠረዉ ዉዝግብ መካረሩን የሚጠቁሙም በርካታ ናቸዉ።

Äthiopien - Proteste gegen die Besitzstände im Land
ምስል Reuters/T. Negeri

በዉዝግቡ ለዉጥ አራማጅ የሚባሉት የበላይነት አግኝተዉ ከመሐላቸዉ አንዱ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን ከያዘ የሕዝብን ጥያቄ ሊመልስ ይችላል የሚል ተስፋ ያላቸዉም አሉ። ፕሮፈሰር መሐመድ አባጀበል ጣሒሮ እንደሚሉት ግን መሠረታዊ የመዋቅር ለዉጥ ካልተደረገ የሕዝብ ጥያቄም፤ የኢትትዮጵያ ችግርም ተገቢ መልስ አያገኙም።

                                            

ዶክተር አረጋዊ በርሔም በተለይ በጦር እና በፀጥታ ኃይሉ አደረጃጃት ላይ መዋቅራዊ ለዉጥ ካልተደረገ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ከየትም ይመረጥ ከየት ለዉጥ ሊመጣ አይችልም።

                                    

ፕሮፌሰር መሐመድ እንደሚያምኑት  ሕዝብን ባሁኑ ወቅት በጣም የሚያሳስበዉ ጠቅላይ ሚንስትር መመረጥ አለመመረጡ አይደለም።በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰበብ የሚደርስበት ግድያ፤ አፈና፤ እስራት እና በሳቸዉ አገላለፅ «ሽብር» እንጂ።ዶክተር አረጋዊ ደግሞ ባአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሙሉ ሥልጣን የተሰጠዉ የጦር  እና የፀጥታዉ ኃይል አሕዝብን መበደል፤ ማሸማቀቅ እና ማዋከቡ መቀጠሉ አይቀርም ባይ ናቸዉ።ፕሮፈሰር መሐመድም አሁን የሚወደዉ እርምጃ መጪዉንም ጊዜ  አስፈሪ ያደርገዋል።

                                       

ግን እስከ መቼ? ተቃዋሚ የሚባለዉ ኃይል ሁነኛ እርምጃ እስኪወስድ ይላሉ-ዶክተር አረጋዊ።ኢትዮጵያን ካለችበት ፈተና ለማዉጣት እብዙ ሥፍራ የተከፋፈለዉ ተቃዋሚ ኃይል ፈጥኖ የመንቀሳቀስ አቅም፤ ሁነኛ ሥልት ከሁሉም በላይ መሠረታዊ ፍላጎት እና አንድነት መፍጠር መቻሉን ብዙዎች ይጠራጠራሉ።ሕዝብ በተለይ ወጣቱ በየአካባቢዉ የራሱን ተቃዉሞ እና አድማ ማድረግ የጀመረዉም ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች ለበርካታ አመታት የጠበቀዉን ባለማግኘቱ ነዉ።በዚሕም ምክንያት ፕሮፈሰር መሐመድም  እንደሚሉት ኢሕአዴግ የሕዝብ ጥያቄ መመለስ አይፍልግም።ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም ለዉጥ ለማምጣት አቅም የላቸዉም።                                                    

Äthiopien Protest
ምስል Reuters/T. Negeri

«ያሳዝናል።» ግን ምን ማድረግ ይቻላል? ተወያዩበት ።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ