1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አበረታች ንጥረ-ነገር በኢትዮጵያ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 25 2009

አዲስ አበባ ዉስጥ አበረታች ንጥረ ነገሮች ለአትሌቶች ሸጧል ተብሎ የተጠረጠረ መድኃኒት መደብር ሰሞኑን ለሦስት ወር ተዘግቷል። መድኃኒት መደብሩ ካለ ሐኪም ትዕዛዝ ኃይል ሰጪ መድሐኒቶችን እንደሚሸጥ ያጋለጡት ሽያጩን በስዉር ሲከታተሉ የነበሩ የዉጪ ጋዜጠኞች ናቸዉ። ጋዜጠኞቹ ኢትዮጵያ ዉስጥ በአትሌቶች ላይ በቂ ምርመራ እንደማይደረግም ዘግበዋል።

https://p.dw.com/p/2j9wr
Welt Anti Doping Agentur
ምስል picture-alliance/dpa/J.C.Bott

በዓለም ዙሪያ ዝናቸው የናኙ ዕውቅ አትሌቶችን ጨምሮ ስድስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በአበረታች ንጥረ ነገር መጠርጠራቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ከተነገረና የስፖርቱን ቤተሰብ ካስደነገጠ ሁለት ዓመት ግድም ሆኖታል። ዛሬም ድረስ ግን የአበረታች ንጥረ ነገር ጉዳይ ለኢትዮጵያ ስፖርት በተለይም ለአትሌቲክሱ ራስ ምታት የሆነ ይመስላል። አዲስ አበባ ውስጥ የተከለከሉ አበረታች ንጥረ ነገሮችን ያለ ሐኪም ፈቃድ ሲሸጥ ነበር የተባለ መድኃኒት ቤትም የውጭ ሃገር መገናኛ ዘዴዎች ምርመራ (ዘገባ)ውጤትን ተከትሎ እስከመዘጋት ደርሷል። ለሦስት ወራት ያህል እንዲዘጋ ቅጣት የተላለፈበት ግሸን መድኃኒት ቤት  በዓለም አቀፍ ጸረ አበረታች ንጥረ ነገር ኩባንያ የተከለከለ መድሃኒት መሸጡ ተዘግቧል። 

ዶ/ር አያሌው ጥላሁን፦ በፌዴራል ወጣቶችና ስፖርት ሚንስቴር የስፖርት ሕክምና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው። በውጭ ሃገራት የመገናኛ አውታሮች ዘገባ የተጠቀሰው መድኃኒት ለተለያዩ የኅመም አይነቶች እንዲውል በተለያዩ መድኃኒት መደብሮች ውስጥ በሃኪም ትእዛዝ የሚሸጥ መሆኑን ተናግረዋል። ችግሩ የተከሰተውም ይላሉ። 

Russland Doping
ምስል Reuters/S. Karpukhin

«አሁን ችግሩ በምን ተከሰተ? መድኃኒቱ በግሸን ፋርማሲ ይገኛል። ይኼ መድኃኒት ከፍተኛ አቅም ካላቸው ትላልቅ ቅመሞች አንዱ ነው። እንዴት እንደሚሰጥ? በማን እንደሚታዘዝ ወዴት እንደሚሄድ የተመዘገበ ነው። አሁን ጉዳዩ በምንድን ነው የተከሰተው? ያለምንም ማዘዣ እና ሰዎች ነጮቹ  ማለት ነው፤ መጥተው  ተራ በተራ ወደ ዘጠኝ  ብልቃጥ ገዙ።  ዘጠኝ ብልቃጥ ሲገዙ እነኚህ ነጮች  ስለስፖርት የነቃ ግንዛቤ ያላቸው፤  ከፍተኛ አቅም ያላቸው ናቸው።  እነኚህ ቅመሞች ደግሞ ወደ አትሌቶች ከሄዱ ችግር እንደሚፈጥሩ ስለሚያውቁ  ስህተት ተሠርቷል አሉ።  አንኳኩት በቃ።» 

ሆኖም በኢትዮጵያ የጸረ አበረታች ንጥረ ነገር ዘመቻው ከፍተኛ ነው ሲሉ ዶ/ር አያሌው ተናግረዋል። በውጭ ሃገራት የመገናኛ አውታሮች የቀረቡት የሰሞኑ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ግን ኢትዮጵያ በጸረ አበረታች ንጥረ ነገር ዘመቻ ዙሪያ የምታደርገው እንቅስቃሴ ጥያቄ የሚያጭር ነው። እንደ ዘ ጋርዲያንን የመሳሰሉ የውጭ ሃገር ጋዜጦች በዓለም አቀፍ ጸረ አበረታች ንጥረ ነገር ኩባንያ የተከለከሉ (EPO)ን የመሰሉ መድኃኒቶች አዲስ አበባ ውስጥ በቀላሉ መግዛት እንደሚቻል ዘግበዋል። 

በጀርመንኛ ምኅጻሩ ARD የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ የአበረታች ንጥረ ነገር ባለሞያ ሃዮ ዜፕልት ወደ ኢትዮጵያ በማቅናት ባቀረቡት የምርመራ ዘገባ ደግሞ አበረታች ንጥረ ነገር በኢትዮጵያ ዛሬም ድረስ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በድብቅ ካሜራ የቀረጹት መረጃ ምንነትን እንዲህ ያብራራሉ።

«እንደ ምርመራ ዘገባችን ከሆነ ከአፍሪቃ ወደ ጀርመን የመጡ ስፖርተኞች ከአበረታች ንጥረ ነገሮች ጋር የሚያያዙ ፍንጮች በተደጋጋሚ ይታያሉ። የድብቅ መቅረጫ አስይዘን በላክነው ግለሰብ የተቀረጸ በማንኛውም ጊዜ ልናቀርበው የምንችለው መረጃም አለን። የተቀረጸው መረጃ ውስጥ ከዓለም ምርጥ ቁጥር አንድ አትሌቶች አንዷ የሆነች አትሌት አበረታች ንጥረ ነገር መውሰዷን ተናግራለች። ይህች አትሌት የበርሊን ማራቶን አሸናፊ ናት።» 

Hajo Seppelt ARD Reporter
ምስል picture-alliance/dpa/S. Krasilnikov

ሃዮ ዜፐልት ኢትዮጵያ ሄደው ያቀናበሩትና በጀርመንኛ ቋንቋ የተላለፈው የቴሌቪዥን ዘገባ አዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ ከውድድር በኋላ የጸረ አበረታች ንጥረ ነገር ምርመራ ሜዳው ውስጥ እንደማይካሄድ፤ ጽ/ቤቱ ዝግ ሆኖ ከአንድ ጠረጴዛ በስተቀር ምንም እንደሌለበት ያትታል። ተወዳዳሪ አትሌቶችም ከአንዱ በስተቀር ውድድራቸውን ጨርሰው ወደ ምርመራ ቦታ ሳይሆን ወደ ሌላ ቦታ ሲያመሩ ያሳያል። 

ዶክተር አያሌው ጸረ አበረታች ንጥረ ነገር ምርመራ የሚከናወነው በድንገት ሳይታሰብ መሆኑን፣ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች የቡድኑ ዶክተሮች እንኳን ምርመራው መቼ እንደሚካሄድ እንደማያውቁ ተናግረዋል። ሆን ተብሎ ማንም በሌለበት ጊዜ ተጠብቆ የተሠራ ዘገባ ነውም ብለዋል። ምርመራው ኬንያ ከሚገኘው ተቋም ጋር በጋራ እንደሚሠራ የውጭ ጋዜጠኞቹ አላጤኑትም፤ በአንዴ ባዩት ነገር ድምዳሜ ላይ ደርሰዋልም ሲሉ አክለዋል። 

በዘንድሮው የጎርጎሪዮስ ዓመት በኢትዮጵያ ታይቶ በማይታይ መልኩ በርካታ አትሌቶች ላይ አበረታች ንጥረ ነገር ምርመራ እንደተደረገላቸው መነገሩን የስፖርት አማካሪው ጋዜጠኛ ኤልሻዳይ ነጋሽ ይናገራል። በቁጥር፣ በምርመራና ግንዛቤ ማስጨበጥ ዙሪያ በአበረታች ንጥረ ነገር መጠቀም ከተጠረጠሩ ከሌሎች ሃገራት ጋር ሲነፃፀር በኢትዮጵያ ጥሩ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የገለጠው ኤልሻዳይ «ነገር ግን» ይላል።

«ነገር ግን እነዚህ ሥራዎች እየተሠሩ በሌላ መልኩ ደግሞ የተለያዩ አትሌቶች ይኼንን የምርመራ ስልት  በማለፍ በአቋራጭ ውጤት ለማግኘት የሚያደርጉት ሙከራም ደግሞ ይቀጥላል። እና ጸረ አበረታች ንጥረ ነገር ላይ የሚደረገው ሥራ ተከታታይነት ያለው፤ የማይቆም ወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው።»

Doping Symbolbild
ምስል picture-alliance/dpa/P. Seeger

የጸረ አበረታች ንጥረ ነገር ምርመራ ሥራ እልህ አስጨራስ በመሆኑ መቀጠል አለበት ሲልም አክሏል። ዶ/ር አያሌው ጥላሁን በበኩላቸው ዘገባውን ተከትሎ ጉዳዩን በቅርበት ከሚከታተሉ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር መነጋገራቸውን ጠቅሰዋል። ተቋማት ሥራቸው አወድሰው በዛው ቀጥሉ እንዳሏቸው ተናግረዋል። ቀደም ሲል እነዚህ ጸረ አበረታች ንጥረ ነገሮች በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች አይታዩም ነበር ያለው ጋዜጠኛ ኤልሻዳይ ንጥረ ነገሮቹ አሁን በቀላሉ መገኘታቸው አትሌቱ ላይ ምን ያህል የግንዛቤ ጉዳይ መጨመር እንደሚገባ ያመላክታል ብሏል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ