1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ፤ ድርቅ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 6 2007

አርብቶ አደሮች በብዛት በሚኖሩባቸዉ በቆላማዉ ትግራይ፤ በአፋር፤ በሶማሌ መስተዳድሮች እና በአንዳድ የኦሮምያ ወረዳዎች እስካሁን ቁጥራቸዉ በዉል ያልተነገረ ከብቶች እና የቤት እንስሳት ሞተዋል።ሰዎችም እየተፈናቀሉ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1GECk
ከክምችት የተወሰደ
ምስል picture-alliance/dpa

ባለፈዉ በልግ ወቅት ይጠበቅ የነበረዉ የዝናብ መጠን በመቀነሱ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተመረተዉ የእሕል መጠን አነስተኛ ነዉ።የመሕሩ ዝናብም በተለይ በምሥራቅ፤ ሠሜን ምሥራቅና በደቡብ ኢትዮጵያ ባብዛኛዉ በመሳቱ በመጪዉ ዓመት ይመረታል ተብሎ የሚጠበቀዉ የእሕል መጠን ማሽቆልቆሉ እንደማይቀር የግብርና ባለሙያዎች እየተናገሩ።በቆላማ አካባቢዎች ደግሞ ባሁኑ ወቅት ከብቶችና ሌሎች እንስሳቶች በብዛት እየሞቱ ነዉ።ሰዎችም እየተፈናቀሉ ወይም ዉሐ ወዳለበት አካባቢ እየተሰደዱ ነዉ።የድርቁ ምክንያት፤ መጠኑና ድርቁን ለመከላከል የተደረገዉና ሊደረግ የሚገባዉ ጥንቃቄ የዛሬ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁን አምሹ።

ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ይባል-ሰዉ ሠራሽ ለድርቅና ረሐረብ አዲስ አይደለችም።ከ1950ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ዓመት እየተጠበቀ በአብዛኛዉ በየአስር-አስራ ሁለት ዓመቱ፤ የሚከሰተዉ ድርቅና ረሐብ አንዳዴ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ይቀጥፋል።1977ቱ የረሐብ እልቂት በእስካሁኑ የኢትዮያ ታሪክ አቻ አልተገኘለትም።

በድርቁ ወይም በረሐቡ የሚያልቀዉ ሰዉና እንሰሳ ቁጥር ይቀንስ እንጂ ከ1977 በሕዋላም ሐገሪቱ በድርቅና ረሐብ ከመመታት አልዳነችም።በ1995 የተከሰተዉ ድርቅ በርካታ ኢትዮጵያዉያንን ለረሐብ ካጋለጠ ወዲሕ የኢትዮጵያ መንግሥት ወትሮም ልዩ ትኩረት እሰጠዋለሁ ለሚለዉ ለግብርናዉ ክፍለ-ኤኮኖሚ ይበልጥ ትኩረት እንደሚሰጥ ቃል ገብቶ ነበር።

ከክምችት የተወሰደ
ምስል AP

መንግሥት አዲስ ቀየስኩት ባለዉ ሥልት አዳዲስ የአስተራረስ ና የከብት አረባብ ዘዴዎችን፤ የአዝዕርት ጥበቃ፤ የዉሐ አጠቃቀም፤ እና ድርቅን የሚቋቋሙ አዝዕርትን ለገበሬዉ ማስተዋወቁን፤ በተለይ የመስኖ ግብርናን ማስፋፋቱን በተደጋጋሚ መግለፁ አልቀረም።ገበሬዉ ወይም አርብቶ አደሩ አስቀድሞ እንዲጠነቀቅ፤ መጠባበቂያ ሠብሉን በአግባቡ እንዲይዝ የሚያስተምሩና የሚያስተባብሩ ባለሙያዎችንም በየወረዳዉ መመደቡን እንሰማለን።

ይሁንና ዘመን እያሰላ የሚከሰተዉን ድርቅና ጉዳቱን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ቀርቶ ማቃለልም አልተቻለም።ኢትዮጵያዊ ዉ የግብርና ኤኮኖሚ አጥኚና አማካሪ ዶክተር ደምስ ጫን ያለዉ እንደሚሉት ተፍጥሮ የሚያስከትለዉን ድርቅ ማስወገድ በርግጥ አይቻልም።ድርቁ አደጋ እንዳያደርስ መጠንቀቅ-ግን አይገድም።

ዘላቂዉ ጥንቃቄ ለአርሶ አደሩም ለአርብቶ አደሩም ዘመናዊና ሳይንሳዊ አሰራርን ማስተዋወቅ ገቢር እንዲያደርገዉ መደገፍ ነዉ።ባጭሩ። የ1995ቱ ድርቅ መንግስትን ለአዳዲስ አርምጃዎች ማነሳሳቱ ሲነገር እርምጃዎቹ ዘመናዊ ወይም ሳይንሳዊ የተባሉ የአመራረት ዘዴዎችን ለገበሬዉና ለአርብቶ አደሩ ከማስተዋወቅ ያለፈ ነዉ ብሎ ማሳብም አይቻልም።

የኢትዮጵያ መንግሥት ዘመናዊዉን አሰራር ለገበሬዉ ማስተዋወቁ፤ አዳዲስ ስልቶች መንደፉ በተነገረ በስምንተኛዉ ዓመት-2003 አስር ሚሊዮን የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ሐገራት ሕዝብ ለረሐብ ወይም ለምግብ እጥረት ተጋልጦ ነበር።ሶማሊያ፤ ኢትዮጵያ፤ ኬንያና ጅቡቲን ያዳረሰዉ ረሐብ በርካታ ሕዝብ የገደለና ያሰደደዉ በርስ በርስ ጦርነት በወደመችዉ ሶማሊያ በመሆኑ በሌሎቹ ሐገራት ያደረሰዉ ጉዳት የሶማሊያዉን ያሕል የዓለም መገናኛ ዘዴዎችን ትኩረት አልሳበም።ከሶማሊያ ቀጥሎ በርካታ ሕዝብ የተረባዉ ግን ኢትዮጵያ ዉስጥ ነበር።በአራተኛ ዓመቱ ዘንድሮ እንደገና ሌላ ድርቅ።ዳግም ችግር።

#አርብቶ አደሮች በብዛት በሚኖሩባቸዉ በቆላማዉ ትግራይ፤ በአፋር፤ በሶማሌ መስተዳድሮች እና በአንዳድ የኦሮምያ ወረዳዎች እስካሁን ቁጥራቸዉ በዉል ያልተነገረ ከብቶች እና የቤት እንስሳት ሞተዋል።ሰዎችም እየተፈናቀሉ ነዉ።

በተለይ በአፋር መስተዳድር የሚያልቀዉ እንስሳ ለመንገደኛ እንደተጣለ ፍሪዳ በየአስፋልቱ ግራና ቀኝ ተደርድሮ ተጓዡን ያዉካል።ጉዳተኞቹ እንደሚሉት የኢትዮጵያ የፌደራዊም ሆነ አካባቢያዊ መንግሥታት ችግረኛዉን ለመርዳት እስካሁን የወሰዱት እርምጃ የለም።የግብርና ምጣኔ ሐብት አጥኚዉ ዶክተር ደምስ እንደሚሉት መንግሥት ቢዘገይም ጨርሶ ሳይመሽ ችግሩን ለማቃለል መጣር አለበት።

ዘንድሮ የተከሰተዉ ድርቅ እንስሳት ከመግደል፤ ሰዎችን ከማፈናቀሉና ሰብል ከማሳት ወይም ከመቀነሱ አልፎ የሰዉ ሕይወት ማጥፋት ደረጃ አልደረሰም።አነሰም በዛ አሁን የሚወሰደዉ እርምጃም አደጋዉ የሰዉ ሕይወት ወደ መቅጠፍ ከመናሩ በፊት ለመቆጣጠር የሚቻል ይመስላል-እንደ ዶክተር ደምስ እምነት።ሕይወትን ለማቆየት ግን አሁንም የዉጪ ርዳታ ማግኘት ግድ ነዉ።

ከተመፅዋችነት ተላቀቀ የሚባለዉ ሕዝብ ዛሬም እርዳታ ይጠብቃል።በምጣኔ ሐብት ዕድገት የአፍሪቃ ተምሳሌት የምትባለዉ ሐገር ዛሬም ሕዝቧን መቀለብ አልቻለችም።ደጋግመን እንዳል ነዉ ኢትዮጵያና ሕዝቧን ከዕርዳታ ጠባቂነት አዙሪት የሚደፍቀዉን ድርቅ ማስወገድ በርግጥ አይቻል ይሆናል።የማይቻለዉ ችግር ሲከሰት የከፋዉን ጥፋት እንዳይደርስ በመፍጨርጨር ደግሞ ብልሕነት ነዉ።ዘንድሮ የተከሰተዉ ድርቅ እስካሁን ካደረሰዉ ጉዳት በላይ እንዳያደርስ ለመከላከል መንግሥትና የሚመለከታቸዉ ወገኖች የሚያደርጉት ጥረት ዶክተር ደምስን ያረካ ይመስላል።

ከክምችት የተወሰደ
ምስል DW

ኢትዮጵያ በድርቅ የተመታችዉ ወይም ለስለስ ባለዉ አገላለፅ ለዝናብ እጠረት የተጋለጠችዉ ፈጣን የምጣኔ ሐብት ዕድገት ማሳየቷ መዓልት ወሌት-በሚነገርበት፤ ላለፉት አምስት ዓመታት ሥራ-ላይ ዋለ የተባለዉ የዕድገትና የለዉጥ ዕቅድ (GTP) በሚጠናቀቅበት ዓመት ነዉ።ዕቅዱ በታሰበዉ መሠረት ገቢር አለመሆኑን መንግሥትም አልካደም።ገቢራዊ የሆነበት ወይም ያልሆነበት መጠንና ደረጃ ግን መንግሥትን ከባለሙያዎች እያወዛገበ ነዉ።

በዉዝግቡ መሐል በመጠናቀቅ ላይ ያለዉን ዕቅድ የሚተካ GTP-2 የተሰኘዉ ሌላ ዕቅድ መነደፉ ይፋ ሆኗል።አዲሱ ዕቅድ በተለይ በግብርናዉ ዘርፍ የመስኖ እርሻን ለማስፋፋት ከቀዳሚዉ የተሻለ ትኩረት መስጠቱ ተነግሯል።ያም ሆኖ አሁን የተከሰተዉ ድርቅ አጠቃላይ የምጣኔ ሐብት ዕድገቱን ማደናቀፉ የማይቀር ነዉ።እንደገና ዶከተር ደምስ።

የድርቁ መነሻ ይታወቃል።የሚደጋገምበት ጊዜም ሲያጥር በአምስት ዓመቱ፤ ሲረዝም በየአስራ-ሁለት ዓመቱ እንደሆነ ከቅርብ ጊዜዉ ክስተት መገንዘብ አይገድም።ችግሩ ሲከሰት እንደ እሳት አደጋ መከላከያ መሯሯጥ ዘላቂ መፍትሔ አይሆንም።ከተመፅዋችነትም አላላቀቀም።

የረጅም ጊዜ ሥልት ቀይሶ ከተፈጥሮ ጥገኝነት ለመላቀቅ መታገል እንጂ-አብነቱ።የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲሕ አይነቱን መርሕ እንደሚከተል በተደጋጋሚ አስታዉቋል አንዳድ አካባቢዎችም መርሑ ተጨባጭ ለዉጥ ማምጣቱ እየተነገረ ነዉ።ይሁንና ለዉጡ የሚፈለገዉን ያክል እንዳልሆነ ያሁኑ ድርቅ ግልፅ ምስክር ነዉ።ዶክተር ደምስ እንደሚሉት መንግሥት የትኩረት አድማሱን በማስፋት ይበልጥ ዉጤማ የሆኑ ሳይንሳዊ አሰራሮችን በአምራቹና በግብራናዉ መስክ በሚሰማሩ ባለሐብቶች ዘንድ ማስረፅ አለበት። ዶከተር ደምስ ጫንያለዉ ለሰጡን አስተያየት አመሰግናለሁ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ደሕና አምሹ።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ