1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ኢንተርኔት በመዘጋቱ ኢትዮጵያ ላይ የደረሰው ኪሳራ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 9 2009

ኢትዮጵያ በአንድ ዓመት ውስጥ ለ30 ቀናት የኢንተርኔት አገልግሎትን በማቋረጧ ወደ 9 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ማጣቷን መቀመጫውን በዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው ብሮኪንግስ የፖሊሲ ጥናት ተቋም ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው ጥናት ጠቋሟል።

https://p.dw.com/p/2RRBo
Computer IP Adressen
ምስል picture- alliance/dpa/F. P. Tschauner

የኢንተርኔት መቋረጥ ኢትዮጵያ ላይ ያደረሰዉ ኪሳራ

የብሮኪንግስ የፖሊሲ ጥናት ተቋም ምክትል ፕሬዝዳንት ዳረል ዌስት ባቀረቡት ጥናት በቅርብ ዓመታት ተጠቃሚዎች የሚገለገሉባቸውን የተወሰኑ አፕልኬሽኖች፤ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት አሊያም መላውን የኢንተርኔት አገልግሎት መንግስታት ማቋረጥ እና መዝጋት እየተለመደ የመጣ ክስተት መሆኑን አትተዋል። ከእነዚህ አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ነች። ከሰኔ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት ለ30 ቀናት በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ይኸው ጥናት ጠቁሟል። 
«መንግስታት ብሔራዊ እና የሕብረተሰብ ደሕንነት፤ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮች» የኢንተርኔት አገልግሎትን ለመዝጋት እንደ ምክንያት የሚያቀርቧቸው ምክንያቶች መሆናቸውን የሚናገሩት ብሮኪንግስ የፖሊሲ ጥናት ተቋም ምክትል ፕሬዝዳንት ዳረል ዌስት የመንግስት እርምጃ በውጭ ባለሐብቶች ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ይናገራሉ።


«በእርግጠኝነት በውጭ ባለወረቶች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። እንዲህ አይነት የአገልግሎት መስተጓጎል ከተመለከቱ ገንዘባቸውን በአገሪቱ በሥራ ላይ ከማዋል ሊታቀቡ ይችላሉ። የኢንተርኔት አገልግሎትን መዝጋቱ የሚያስከፍለው ኤኮኖሚያዊ ዋጋ የከፋ ነው። ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን ያዳክመዋል። የገቢ ግብር ይቀንሳል። በንግዱ ሕብረተሰብ እና በመንግስት መካከል ያለውን መተማመንም ይጎዳዋል። ከዚህ በተጨማሪ በሸማቾች ላይም ተፅዕኖ አለው። ምክንያቱ በርካታ ሰዎች በሞባይል ገንዘብ ያንቀሳቅሳሉ።»

Infografik / Karte Protests and violence in Ethiopia,  2016


በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ከገጠመው ተከታታይ ህዝባዊ ተቃውሞ በኋላ የኢንተርኔት አገልግሎቱን መገደብ ብሎም ማቋረጥን መርጧል። የአገልግሎቱ መቋረጥ በቅርብ ጊዜ መልስ የሚያገኝ አይመስልም። በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር የሆኑት ሜቴ ታይጌሰን በትዊተር የማሕበራዊ ድረ-ገፃቸው እንዳሰፈሩት የኢትዮጵያ መንግስት የሞባይል ኢንተርኔት እና የማሕበራዊ ድረ-ገፆች አገልግሎት መልሰው ግልጋሎት የሚጀምሩበትን ተጨባጭ ጊዜ ማስታወቅ አልቻለም። የመንግስት የኮምዩንኬሽን ፅ/ቤት በአዲስ አበባ የሚገኙ ዲፕሎማቶችን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጠው ማብራሪያ ነበር ይህን ያስታወቀው። 


በኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች እንደ ዋትስአፕ እና ቫይበር ያሉ አገልግሎቶች ከተቋረጡ ሰነባብተዋል። ፌስቡክ እና ትዊተርን የመሳሰሉ የማሕበራዊ-ድረ-ገፆችም አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች አገልግሎታቸው ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል አሊያም ከፍተኛ ገደብ ተጥሎበታል። ዳረል ዌስት እንደሚሉት አብዛኞቹ መንግስታት የኢንተርኔት አገልግሎትን ሲያቋርጡ የሚያስከትለውን ጣጣ ከግንዛቤ ውስጥ አያስገቡም። ዳረል በጥናቱ የተዘጋው ኢንተርኔት ከአገሪቱ ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጋር ያለውን ትስስር ለመፈተሽ ሞክረናል ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።


«በጥናቱ መረጃውን ለማጠናቀር የተጠቀምኩበትን ሥሌት ይፋ በፅሁፉ አካትቼዋለሁ። በዋናኛነት የአገሪቱ አመታዊ የምርት መጠን፤ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ የሚቆይበትን ጊዜ ርዝመት፤የዲጅታል ኤኮኖሚውን ስፋት በኢትዮጵያ ያለውን የሞባይል ተጠቃሚ ብዛት እና ኢንተርኔት መዘጋት የሚፈጠረውን ተደራራቢ ተፅዕኖ ፈትሸናል።»
ቀድሞም እጅግ ደካማ የቴሌኮምዩንኬሽን መሰረተ ልማት እና ከአጠቃላይ የአገሪቱ የህዝብ ቁጥር አኳያ ውስን የኢንተርኔት ተጠቃሚ የሚገኝባት የኢትዮጵያ መንግስት አገልግሎቱን ሳንሱር ያደርጋል እየተባለ ወቀሳ ይቀርብበታል። የኢትዮጵያ መንግስት ከጎርጎሮሳዊው 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ውስብስብ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተጠቃሚዎችን የማሕበራዊ ድረ-ገፆች ይበረብራል መረጃዎችንም ያግዳል ሲል የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ፍሪደም ሐውስ ይተቻል። ከኢትዮጵያ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ዘንድ እንዳይደርሱ ገደብ የሚጣልባቸው ድረ-ገፆች መንግስትን የሚተቹ መረጃዎች እና የግለሰቦችን አስተያየቶች የሚያሰፍሩ መቀመጫቸውን በውጭ አገራት ያደረጉ ናቸው። 


በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መልእክት ኢንተርኔትን ጨምሮ  በሞባይል፣ በፅሁፍ፣ በቴሌቭዥን፣ በፌድዮ፣ በማህበራዊ ሚድያ የሚደረጉ የመረጃ ልውውጦችን አግዷል። የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ውሳኔ ከመድረሱ በፊት ተመሳሳይ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ጥቆማ ሰጥቶ ነበር። 
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት 71ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የታደሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ ባደረጉት ንግግር ካነሷቸው ርዕሰ-ጉዳዮች መካከል የማሕበራዊ ድረ-ገፆች አጠቃቀም አንዱ ነበር። አቶ ሐይለማርያም በማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚሰራጭ መረጃ በቀላሉ እንዴት እንደሚዛመት እና ሰዎችን በተለይም ወጣቶችን እንደሚያሳስት እየታዘብን ነው ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች እውነተኛ ጥያቄ ያላቸው ሰዎችን ለፅንፈኞች መጠቀሚያ እያደረገ ነው። ጥላቻን ለማስፋፋት እየተጠቀሙበትም ነው ብለው ነበር። በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ ኩባንያዎችም ይሁን ሥራ ፈጣሪዎች እድሉ የላቸውም። የአገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በኢትዮቴሌኮም ቁጥጥር ሥር ነው። የአገሪቱ መንግሥት ዘርፉን ለውጭ ባለሐብቶች እንዲከፍት የቀረቡለትን ጥሪዎች ሁሉ ውድቅ አድርጓል። 

Ethiopia State of Emergency Merkel (picture alliance / AP Photo)
ምስል picture-alliance/AP Photo


የኢትዮጵያ ባንኮች፤ አገር አስጎብኚ ድርጅቶች እና የገንዘብ ዝውውር ተቋማት ግልጋሎታቸውን ከኢንተርኔት ጋር በማቆራኘት ለማፋጠን ሲያደርጉ የከረሙት ጥረት በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ፈተና ይገጥማዋል።  «በኢንተርኔት የሚሰጡ አገልግሎቶች በሁሉም አገሮች የአመታዊ የምርት መጠን ላይ እድገት እንዲፈጠር እያደረጉ ነው። ሰዎች በኢንተርኔት የሚያገኟቸው ግልጋሎቶች እና የሚያደርጓቸው ግብይቶችን እየወደዷቸው መጥተዋል።ብዙ ሰዎች ለመሰረታዊ ሸቀጦች ግብይት እና አገልግሎቶች ኢንተርኔትን መምረጥ ጀምረዋል። መንግስታት የኢንተርኔት አገልግሎትን ሲያቋርጡ ራሳቸውን በዚያ ቦታ ላይ አድርገው መመልከት አለባቸው። ምክንያቱም የራሳቸውን የንግድ ሥራ እና ኤኮኖሚ እየጎዱ ነው።» ይላሉ ዳረል ዌስት

ብሮኪንግስ የፖሊሲ ጥናት ተቋም ዘገባ መሰረት ባለፈው ዓመት በ19 አገሮች የተከሰተ የኢንተርኔት መቋረጥ የ2.4 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ማድረሱን አትቷል። የዘገባው ጸኃፊ ዳረል ዌስት የኢንተርኔት መቋረጥ ወይም እንደ ዋትስአፕ እና ቫይበር ያሉ ማንቀሳቀሻዎች መታገድ ቤተሰብ፤ጓደኛሞች ያላቸውን ግንኙነት ላይም የከፋ ጫና እንደሚያሳድር ገልጠዋል። በአነስተኛ የገንዘብ አቅም አዳዲስ የሥራ ኃሳብ ይዘው ገበያውን ለሚቀላቀሉ ጀማሪ ኩባንያዎች የኤኮኖሚ እንቅስቃሴውን በማዘግየት አሊያም ጨርሶ በማቆም የሚያሳድረው ጫና አለ። በዳረል ዌስት ዘገባ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ የኢንተርኔት መዘጋት ወይም መቋረጥ ከሚከሰትባቸው እንደ ሕንድ እና ሳዑዲ አረቢያ ተርታ ተቀምጣለች። 
የኢንተርኔት አገልግሎት በተቋረጠባቸው አገራት የደረሰው ኤኮኖሚያዊ ጫና በሕንድ ከፍተኛ ነው። አገልግሎቱ በመቋረጡ ሕንድ 968 ሚሊዮን ዶላር፤ ሳዑዲ አረቢያ 465 ሚሊዮን ዶላር፤ ሞሮኮ 320 ሚሊዮን ዶላር፤ ኢራቅ 209 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ገጥሟቸዋል። የኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የሚዘልቅ በመሆኑ የኢንተርኔት ግልጋሎቱ ወደ ነበረበት መቼ እንደሚመለስ ማወቅ ይቸግራል። በዚሁ ከቀጠለ ግን ኪሳራው ከፍ ማለቱ አይቀርም።


እሸቴ በቀለ 
ሒሩት መለሰ