1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢጋድና የደቡብ ሱዳን ህዝበ ውሳኔ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 25 2003

በደቡብ ሱዳን ህዝበ ውሳኔ ዙሪያ ለመነጋገር ናይሮቢ ላይ የታቀደው የኢጋድ አባል ሀገራት ውይይት ወደ አዲስ አበባ ተዛውሯል። ኢጋድ አጠቃላይ የሰላም ስምምነቱ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ገቢራዊ እንዲሆን ይፈልጋል ተባለ።

https://p.dw.com/p/PyTT
ምስል AP

ናይሮቢ ያለፈው ሳምንት የታቀደው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት ኢጋድ አባል ሀገራት ስብሰባ ወደ አዲስ አበባ የተዛወረው በፕሬዝዳንት አልበሽር ምክንያት እንደሆነ ዘገባዎች ያመላክታሉ። ዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድቤት የክስ ወረቀት የቆረጠባቸው አልበሽር የፍርድ ቤቱ አባል ሀገር በሆነችው ኬኒያ ለኢጋድ ስብሰባ ቢመጡ ተላልፈው ሊሰጡ ይችላሉ የሚለው ጥርጣሬ ብዙዎች ዘንድ ነበረ። ኬኒያ ባለፈው ያሻሻለችውን ህገመንግስቷን ባጸደቀች ጊዜ በተዘጋጀው በዓል ላይ የተገኙትን ፕሬዝዳንት አልበሽርን አሳልፋ አለመስጠቷ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጠንከር ያለ ነቀፌታ ገጥሟታል። የሆኖ ሆኖ የኢጋዱ ስብሰባ ከናይሮቢ ወደ አዲስ አበባ ተዛውሯል። ምናልባትም በያዝነው ሳምንት መጨረሻ ላይ ሊካሄድ ይችላል። ኢጋድ በደቡብ ሱዳን በሚካሄደው ህዘበ ውሳኔ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል። ለህዝበ ውሳኔው መሰረት የሆነውና ሲፒኤ በሚል የሚጠራው አጠቃላይ የሰላም ስምምነት በመንግስትና በደቡብ ሱዳን ህዝብ የነጻነት ንቅናቄ መሃል እንዲደረስ ቁልፉን ሚና የተጫወተው ኢጋድ ነው። የዓለም ዓቀፉ የግጭት አጥኚ ቡድን የአፍሪካ ህብረትና የሱዳን ጉዳይ ከፍተኛ አማካሪ ፉአድ ሂክማት፤ የኢጋድ አባል ሀገራት የሱዳን ጎረቤት በመሆናቸው የህዘበ ውሳኔው በሰላም መጠናቀቅ ይመለከታቸዋል ይላሉ።

ድምጽ

ምስራቅ አፍሪካ ተጨማሪ አንዲት አዲስ ሀገር ልታገኝ እንድትችል የሚደርጋት የደቡብ ሱዳኑ ህዝበ ውሳኔ የካሄድ የቀረው 10 ሳምንታት ብቻ ነው። የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት በገባ በዘጠነኛው ቀን ደቡቦቹ ከሰሜኖች ጋር አብሮ ለመቀጠል አልያም ለመለያየት ይወስናሉ። ይህ ህዝበ ውሳኔ ከወዲሁ በውዝግቦች ታጥሯል። በተለይም አቤይ የተሰኘችው በነዳች የበለጸገችውን አከባቢ በተመለከተ ሁለቱም ወገኖች ከስምምነት ላይ አልደረሱም። ኢጋድ ለህዘበ ውሳኔው መሰናክል በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሁለቱ ወገኖች በተገኙበት ውይይት ለማድረግ እየተዘጋጀ ነው። ፉአድ ሂክማት

ድምጽ

የሱዳን መንግስትና የደቡቡ አስተዳደር ያልተስማሙባቸው ጉዳዮች በርካታ መሆናቸው ሳይሆን አጭር ጊዜ ከቀረው ህዘበ ውሳኔ አንጻር በአንዱም ላይ ስምምነት አለመደረሱ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በጽኑ አሳስቦታል። በተለያዩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሁለቱም ወገኖች ማዶ ለማዶ ናቸው።ከአወዛጋቢዋ የአቤይ ጉዳይ ሌላ ድንበር ያለመካለሉ የህዝበ ውሳኔው ትልቅ መሰናክል ሆኗል። እስከአሁን 20 በመቶ በሚሆነው ሁለቱን ክፍሎች በሚያገናኘው ድንበር ጉዳይ ላይ ከስምምነት መድረስ አልቻሉም። በሚጋርዋቸው ድንበሮች ያለውን ሀብት እንዴት መጠቀም እንዳለባቸውም አልተስማሙም። ከነዳጅ የሚገኘውን ቀረጥና በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ ልዩነታቸው የሰፋ ነው። ሱዳን ያለባትን ዕዳ በተመለከተ የሚጠበቅባቸው ድርሻም ሌላው አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኗል። ሱዳን በአጠቃላይ የ38 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ እንዳለባት ዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ አስታውቋል። ኢጋድ በእርግጥ በየትኞቹ አጨቃጫቂ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ስብስባ እንደጠራ አልታወቀም። የዓለም ዓቀፉ የግጭት አጥኚ ቡድን የአፍሪካ ህብረትና የሱዳን ጉዳይ ከፍተኛ አማካሪ ፉአድ ሂክማት የኢጋድ ስብሰባ የሚጠብቀው ውጤት አጠቃላይ የሰላም ስምምነቱን በሰላም መጠናቀቁን ማረጋገጥ ነው ይላሉ።

ድምጽ

የደቡብ ሱዳን ህዝበ ውሳኔ እየተቃረበና በርካታ መፍትሄ ያላገኙ ጉዳዮች እያጨቃጨቁ ባሉበት በዚህን ወቅት አሜሪካ በሱዳን ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ማራዘሟ የበህዝበ ውሳኔው ሂደት ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ማነጋገር ይዟል። የሱዳን መንግስት በህዝበ ውሳኔው መካሄድ ላይ ዋስትና የሚሰጥ የተባለለት የአሜሪካ ማዕቀብ የማራዘም ውሳኔ እንደ ዓለም ዓቀፉ የግጭት አጥኚ ቡድን ከፍተኛ አማካሪ ፍአድ ሂክማት እይታ አዲስ አይደለም። የነበረና ህዝበ ውሳኔው እስኪጠናቀቅም የሚቀጥል ነው።

መሳይ መኮንን

ነጋሽ መሐመድ