1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤቦላ በምዕራብ አፍሪቃ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 8 2006

በኤቦላ ቫይረስ ወይም ተህዋሲ ከሚያዙ ሰዎች 90 በመቶዉ እንደማይተርፉ ነዉ መረጃዎች የሚያመለክቱት። ተህዋሲዉን የሚከላከልም ሆነ የሚያድን ክትባትም ሆነ መድሃኒት እስካሁን አልተገኘም። ኤቦላ ከዚህ ቀደም በዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፣ ሱዳን፣ ጋቦን፣ አይቮሪኮስትና ዩጋንዳ በተደጋጋሚ ተከስቷል።

https://p.dw.com/p/1Cdcu
Ebola-Virus Guinea
ምስል picture alliance/AP Photo

በኤቦላ ቫይረስ ወይም ተህዋሲ አማካኝነት የሚመጣዉ ህመም ወይም ከባድ ትኩሳት ሰዎችን የሚያጠቃ አደገኛ በሽታ ነዉ። አንድ ሰዉ በዚህ ተህዋሲ ከተያዘ ከሁለት ቀን እስከ ሶስት ሳምንታት ከፍተኛ ትኩሳት የጉሮሮ እና የጡንቻ ሕመም እንዲሁም የራስ ምታት ያሰቃዩታል። ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስና ማስቀመጥ ይከተላል። በእነዚህ ምክንያትም ኩላሊትና ጉበት ተግባራቸዉ ይስተጓጎላል ያኔም ከሰዉነት ደም መፍሰስ ይጀምራል። ከመነሻዉ የኤቦላ ተህዋሲ ወደሰዎች የተጋባዉ ቫይረሱ ከተያዙ ዝንጀሮዎችና የሌሊት ወፎች የወጣ ፈሳሽ አማካኝነት እንደሆነ ነዉ መረጃዎች የሚጠቁሙት።

Ebola-Virus in Guinea
ምስል Seyllou/AFP/Getty Images

ከሶስት ወራት በፊት ጊኒ ዉስጥ በሽታዉ ተቀንስሶ ወደ60 የሚሆኑ ሰዎችን በወቅቱ ቀጥፏል። በሽታዉ እንዲህ በርካታ ሰዉ ሲፈጅም ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነዉ የተገለጸዉ። ከሁሉም ቀዳሚዉና ተህዋሲዉንም ወደዚያዉ ሳያመጣ እንዳልቀረ የሚገመተዉ የበሽታዉ ሰለባ በሀገሪቱ ገጠራማና በደን የተከበበ ስፍራ ነበር የተገኘዉ። ቀደም ሲል እንደተገለፀዉ ሰዎች ትኩሳትም ስለነበረዉ ልማደኛዋ ወባ ህይወቱን ቀማችዉ ብለዉ ነዉ የገመቱት እናም ለቀብር በማዘጋጀቱ ሂደት አካሉን ለመንካት አልተጠነቀቁም አልፈሩምም። ኤቦላ እንደወባ አይደለምና ሟቹን በመንካት ብቻ በርካቶች ለአደገኛዉ ተህዋሲ ተጋለጡ። በርካቶችም ግራ በመጋባት የታመሙ የቤተሰብ አባላቶቻቸዉን ለተሻለ ህክምና እያሉ ወደዋና ከተማዋ ወሰዱ። እዚያ ነዉ እንግዲህ በገዳይነቱ የሚታወቀዉ የኤቦላ ተህዋሲ መንሰራፋቱ የተደረሰበት። በጣም ከፍተኛ ትኩሳት አስከትሎ በአፍንጫና በጆሮ ደም እንዲፈስ የሚያደርገዉ የኤቦላ ተህዋሲ በዚህኛዉ የአፍሪቃ ሃገራት ከዚህ ቀደም አጋጥሞ የማይታወቅ በሽታ መሆኑን ነዉ ዘገባዎች የሚያመለክቱት። ከቅርብ ወራት ወዲህ ግን በምዕራብ አፍሪቃዋ ሀገር ጊኒ ዉስጥ ሲገኝ በዚያ ብቻ አልተገደበም ወደላይቤሪያና ሴራልዮንም ተዛምቷል እንጂ። እስከትናንት ድረስም የ539 ሰዎች ህይወት በዚህ ምክንያት መጥፋቱ ተመዝግቧል።

Ebola Virus
ምስል AP

ኤቦላ እንዳይዛመት ማድረግ የሚቻለዉ እንደህክምና ባለሙያዎች ገለፃ ታማሚዉን ከጤናማ ሰዎች መካከል ለይቶ በማኖር ነዉ። ያ ማለትም ህክምና ወደሚያገኝበት ስፍራ ወስዶ በጥንቃቄ ሊረዱት በሚችሉ የህክምና ባለሙያዎች እጅ መተዉ ማለት ነዉ። በሽታዉ የታማሚዉን አካል በመንካት እንጂ በአየር የሚተላለፍ እንዳልሆነ ነዉ እንስካሁን የተደረሰበት መረጃ የሚጠቁመዉ። ለዚህ ማሳያዉም በሃኪም ቤት ሳይቀር በተህዋሲዉ የተያዙ ሰዎችን የሚያስታምሙና የሚያገላብጡ ሰዎች እጃቸዉን በጓንት እስካልከለሉ ድረስ ከበሽታዉ እንደማያመልጡ መታየቱ ነዉ። ከአንድ ዓመት በፊት ምሥራቅ አፍሪቃ ዩጋንዳ ዉስጥ የኤቦላ ተህዋሲ የሚያስከትለዉን መሰል ትኩሳት በተስፋፋበት ወቅት በሽታዉ በመነካካት ሊተላለፍ እንደሚችል ለማስገንዘብ፤ የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ሕዝቡ ከታመሙ ሰዎች ጋ ለሚኖረዉ የአካል ለአካል ንክኪ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዉ ነበር።

Ebola Uganda 2007
ምስል Getty Images

«ኤቦላ ተገቢዉን መከላከያ በሚያደርጉ የህክምና ባለሙያዎች ብቻ ነዉ መያዝ ያለበት። ስለዚህ እጅ መጨባበጥን እንድታስወግዱ፣ የበሽታዉ ምልክት የታየበት ሰዉ ቢሞትም እናንት ሳትሆኑ ለቀብር እንዲያዘጋጁ የህክምና ሠራተኞችን እንድትጠሩና እነሱ እንዲያከናዉኑ ለማድረግ በጥንቃቄ እንድትንቀሳቀሱ ጥሪዬን አቀርባለሁ። በተጨማሪም ይህ በሽታ በወሲብም ሊተላለፍ ይችላልና ከዘማዊነትም ታቀቡ።»

በወቅቱ ሁለት ሰዎች ዋና ከተማ ካማፓላ ዉስጥ በሚገኝ ሃኪም ቤት የበሽታዉ ምልክት እንደታየባቸዉ ተመዝግቧል። እንዲያም ሆኖ የዩጋንዳ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይህን ያህል ወረርሽኙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የነፍስ አድን አዋጅ ሊያስነግረን አያበቃም በሚል ስጋቱን ለማርገብ ሞክሯል። አሁን ግን ምዕራብ አፍሪቃ ዉስጥ የኤቦላ ተህዋሲ ነፍስ መቅጠፍና ከከተማ ከተማ እየተዛመተ ሰዎችንም ማስተኛት ከጀመረ ወራት አስቆጥሯል ። በስፍራዉ ከተሰማሩት መካከል የድንበር የለሽ ሃኪሞች ባልደረባ ታንከረድ ሽቱይበ አደገኛዉ ተህዋሲ እንዴት እየተዛመተ እንደሚገኝና ስላደረሰዉ ጉዳት እንዲህ ያስረዳሉ፤

Isolierstation
ምስል picture-alliance/dpa

«በምዕራብ አፍሪቃ የተመለክተነዉ ተህዋሲ መድሃኒት የሌለዉ ነዉ። ያም ማለትም በእሱ ከተያዙ ሰዎች አብዛኞቹ አይተርፉም። ሌላዉ ለዚህ መስፋፋት ምክንያት የሆነዉ በምዕራብ አፍሪቃ የሚታየዉ የሰዎች ከቦታ ወደቦታ የመዘዋወር ባህሪ ከፍተኛ መሆን ነዉ። አካባቢዉን አልፈዉ እና ድንበር ተሻግረዉ ስለሚጓዙ ለመድረስ ወደሚያዳግት ስፍራ ሳይቀር የታመሙት ሰዎች ተህዋሲዉን ወደሌላ ይዘዉት ይሄዳሉ። በዚህ ምክንያትም የጤና ባለሙያዎች እነሱን ተከታትለዉ መሄድ ስለማይችሉ ታማሚዎችን በማግኘት ለማከም በጣም አዳጋች ነዉ።»

ባለሙያዉ እንደገለጹት በገጠራማዎቹ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ክፍል የታመሙ ሰዎችን አግኝቶ የህክምና ርዳታ መስጠት ራሱ ዋነኛ ችግር እንደሆነ ነዉ። ተህዋሲዉን ሰዎች ብቻ ይሆኑ እንስሳትም ታማሚዉን ሰዉ የሚተሻሹ ከሆነ ሌላዉ አደገኛ የማስተላለፊያ መንገድ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነዉ በማስጠንቀቂ መልክ ለህዝቡ የተነገረዉ። ሽቱይበ ከምንም በላይ ከታመመዉ ግለሰብ የሚወጣ ማንኛዉም ፈሳሽ የኤቦላ ተህዋሲ ማዛመቻ ዋነኛ መንገድ መሆኑ ነዉ ያረጋግጣሉ፤

«ዋነኛዉ ተህዋሲዉን የሚሸከመዉ ከሰዉነት የሚወጣ ፈሳሽ ነዉ። በተለይ ሰዎች በበሽታዉ ከሞቱ በኋላ በአካባቢዉ ልማድ መሠረት ከቀብር በፊት የሚከናወኑ ነገሮችን አጥብ,ቀን ነዉ የምናስገነዝበዉ፤ ለስንብት ማቀፍ እና አስከሬን እንደማጠብ የመሳሰለዉን ማለት ነዉ፤ ያኔ ነዉ በተህዋሲዉ የመያዝ አጋጣሚ ሊመጣ የሚችለዉ።»

Die Grenze des Buruntuma, zwischen Guinea-Bissau und Guinea Konacry
ምስል DW/Braima Darame

የኤቦላ ተህዋሲ በተለይ በጊኒ፣ ሴራሊዮንና ላይቤሪያ የህክምና አገልግሎት ካልመስፋፋቱ ጋ ተዳምሮ ብዙዎችን ለጉዳት እንደዳረገ ነዉ የሚነገረዉ። በበሽታዉ እንዳይያዙ ሰዎች ማድረግ የሚገባቸዉ ጥንቃቄ መኖሩ ቢታወቀም አስቸጋሪዉ ያንን ለአካባቢዉ ኅብረተሰብ በሚረዳዉና በባህሉ መሠረት የማግባባቱ ነገር መሆኑን ነዉ የሚያመለክቱት የህክምና ባለሙያዉ፤

«ይህ ነዉ አስቸጋሪዉ ጉዳይ። ለዚህም አንድ መረጃ የማዳረስ ዘመቻ እጅግ አስፈላጊ ነዉ፤ ነገር ሰዎች ተደናግጠዉ እና ስለተህዋሲዉ የሌለ የፈጠራ ተረት እንዳይዙ ማድረግ ሳይሆን፤ ስለችግሩ ገብቷቸዉ ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸዉ በወጉ ማስገንዘብ ያስፈልጋል። እርግጥ ነዉ አንድ የቤተሰብ አባል ሲለይ ተገቢዉን ስንብት ማድረግ ያስፈልጋል ግን የአካል ለአካል ንክኪ እንዳይኖር ጥንቃቄ በማድረግ ማለት ነዉ። በዚያ ላይ ለታማሚዎችም ሆነ ለጤና ባለሙያዎች ተገቢዉ የንፅህናና የጥንቃቄ ሁኔታ ሊሻሻል ይገባል። አንዳንዴ በጣም ተራ የሚባለዉ የንፅህና መጠበቂያ እንኳ ተህዋሲዉ በተስፋፋባቸዉ በእነዚህ ሃገራት የለም።»

Versuchsaffe im New Iberia Research Center SPERRFRIST 26.05.2014 21:00
ምስል Jeremy Breaux/New Iberia Research Council

ችግሩ መኖሩ ቢታወቅም ኤቦላ ተህዋሲም ገዳይነቱ ቢነገርም በተጠቀሱት ሃገራት ያለዉ የንቃት እና ትምህርት ሁኔታ እጅግ ኋላ ቀር በመሆኑ ለእርዳታ እዚያ የተሰማሩትን ወገኖች እንዳዳገተ ነዉ ከእሳቸዉ መረዳት የሚቻለዉ። እንዲህ ያለዉን ችግር በአግባቡ ለሚመለከታቸዉ ከገለፁ በኋላ ሰሚዎቹ ሁኔታዉን መረዳታቸዉ ባይቀርም ችግሩን ተረድተዉ እንዲጠነቀቁ ለማድረግ ገና ብዙ ሥራ መሠራት እንዳለበት ነዉ የሚያመለክቱት፤

«የተወሰኑት በጥሩ ሁኔታ ይተባበራሉ። ሆኖም አብዛኞቹ የእኛ ባልደረቦች አፍ አፍንጫቸዉን በመከላከያ ጭንብል ሸፍነዉ፤ እጆቻቸዉን በጓንት ከልለዉ ሲያይዋቸዉ ይደናገጣሉ። ይህም እንዲህ ያለ ሁኔታ አንዳንዶቹ ጭራሽ አይተዉ እንደማያዉቁ ነዉ የሚያመላክተዉ። በተለይ ደግሞ አንዳንድ የታመሙ ሰዎች ወደእኛ ማዕከል መጥተዉ የጤና ይዞታቸዉ መሻሻሉ ቀርቶ ያርፉና አስከሬናቸዉ ሲመለስ እኛ ማዳን የማንችል እንደዉም የምናባብስ አድርገዉም ያዩናል። ለዚህ ደግሞ ትምህርት በስፋት መስጠት ነዉ መድሃኒቱ። ምክንያቱም ከዚህ በፊት ኤቦላ በተከሰተባቸዉ በሌላዉ የአፍሪቃ ክፍል የከፍተኛ ትምህርት በመዳረሱ ሰዎች በቀላሉ ችግሩን ተረድተዉ ራሳቸዉን ለመከላከል አይከብዳቸዉ። ነገር ግን ተህዋሲዉ አሁን በተስፋፋባቸዉ በምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ከፍተኛ ያለማወቅ ችግር ይታያል እናም በጎሳ መሪዎች እና በአካባቢዉ የጤና ማዕከላት መካከል ሳይቀር ብዙ ትምህርት ያስፈልጋል። ይህ ተህዋሲ መኖሩን፣ የታመመ የቤተሰብ አባል ካለ ራስን እንዴት መከላከል እንደሚቻል ማለት ነዉ። »

በዚህ ምክንያትም ተገቢዉን የመከላከል ርዳታ ለመስጠት አዳጋች እንደሆነ ነዉ ከአባባላቸዉ መረዳት የሚቻለዉ፤ በስፍራዉ የሰዎችን ህይወት ለመታደግ የሚያከናዉኑት ተግባርም ቀላል እንዳልሆነ ነዉ የሚያስረዱት።

Guinea Conacry Ebola Virus
ምስል picture-alliance/AP

«አስቸጋሪ ነዉ። ባልደረቦቻችን ለእርዳታ በሄዱበት መልካም አቀባበል አይደረግላቸዉም ጥርጣሬ ያለበት ሁኔታ ነዉ የሚታየዉ። በዚያ ላይ ለእነሱም ቢሆን የንፅህናዉ ነገር በጣም ወሳኝ ነዉ። በዚህ ምክንያትም በዚያ ሙቀት ፕላስቲክ ልብሶችን ከላይ ለብሰዉ ነዉ የሚንቀሳቀሱት የሚሠሩት፤ ያ ደግሞ በጣም አስጨናቂ ነዉ። እናም እንዲያም ሆኖ በዚያ ሁሉ መሃል የምናደርገዉ የመከላከል ጥረት እያለ ተህዋሲዉ መዛመቱን ስንመለከት እኛም ብንሆን ተስፋ አስቆራጭ ነዉ የሚሆንብን።»

አንዳንዶች መድሃኒት የላቸዉም የሚባሉ አደገኛና ገዳይ ተህዋስያን በምርምሩና በኤኮኖሚ አቅሙም ቢሆን ጠንከር ወዳሉት ሃገራት ቢዛመቱ ምናልባት መፍትሄዉ እንደሰማይ አይርቅም ነበር ሲሉ ይደመጣል። ለምሳሌ ኤቦላ። መነሻዉም ሆነ ደጋግሞ የሚከሰተዉ አፍሪቃ ዉስጥ ከመሆኑ ጋ ተያይዞ ለሚቀጠፈዉ ጎስቋላ ህይወት አብነት ጠፍቶለት ቆይቷል። ስሙም የሚነሳዉና የመገናኛ ብዙሃኑን የአየር ሰዓት የሚያገኘዉ ሰዎችን ሲገድል ብቻ ነዉ። በቅርቡ ከጀርመን ወደምዕራብ አፍሪቃ ሀገር ለማየት የተጓዙ ፈረንጆቹ አድቬንቸረር የሚሏቸዉ ጓዛቸዉን በሻንጣ አጭቀዉ ወደማያዉቁት አካባቢ በመሄድ የሄዱበት ሀገር አኗኗር ኖረዉ የሚመለሱ ወጣቶች አንዱ ወደሀገሩ ከተመለሰ በኋላ ከፍተኛ ትኩሳት ይይዘዋል፤ ጉንፋን ነዉ ብሎ ሲገምትም ዉሎ ያድራል ከዚያም በተለያዩ የሰዉነቱ ክፍሎች ደም ይቀጣ ይጀመር። ጓደኛዉ ተደናግጣ አምቡላንስ ጠራች ሃኪም ቤትም ገባ። ታማሚዉ ከቆየበት አካባቢ ጋ ተገናኝቶም ብዙዎች ኢቦላ ጀርመን ገባ እንዲሉ ቢያስደፍራቸዉም የሃምበርግ ዩኒቨርሲቲ የሞቃት አካባቢ በሽታዎች ምርምር ባልደረባ ዮናስ ሽሚድት እስካሁን በሽታዉ ጀርመን ዉስጥ እንዳልተከሰተ ተናግረዋል። ያ ማለት ግን ሰዎችን አዘናግቶ በሽታዉ የሚያስከትላቸዉ ምልክቶች ሲታዩ ችላ ማለት እንደማይገባ ግን አሳስበዋል። ዘገባዎች ከአራት ዓመታት በፊት ኤቦላን መሰል ማርቡርግ የተሰኘ በተዋህሲ አማካኝነት የሚመጣ ትኩሳት የሚያስከትል በሽታ 31 ሰዎችን መግደሉን ያስታዉሳሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ